ዓለማችን በወረቀት እንዴት ተቀየረች?

የወረቀት ጥቅም ብዛት Image copyright Alamy

ለወረቀት ያሉንን በሺህ የሚቆጠሩትን የተለያዩ አጠቃቀሞችን እስቲ ለአፍታ እናስብ።

ወረቀትን ለህትመት መጠቀም ደግሞ ከጥቅሞቹ እንዱ ብቻ ነው ምክንያቱም ግድግዳዎችን በምስሎችም ሆነ በሥዕሎች እናስውባለን፣ ወተትና የፍራፍሬ ጭማቂ እናሽጋለን ተለቅ ያሉዕቃዎችንም ለማሸግ ስንል ካርቶኖችን እንጠቀማለን።

ወረቀት ዓለምን እንዴት እነደቀየረ ለማወቅ ደግሞ 2000 ዓመታት ወደኋላ ተጉዘን ቻይናውያንን መመልከት ይኖርብናል። መጀመሪያ ላይ ልዩ ዕቃዎችን ለመጠቅለል ይጠቀሙበት ነበር ከጊዜ በኋላ ግን ከሸምበቆ የሚቀልና ከሐር ይረክስ ስለነበር ይጽፉበት ጀመር።

በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአጻጻፍ ዘዴውን አረቦችም መጠቀም ጀመሩ። ከአሥርት ዓመታት በኋላ አውሮፓውያንም ወደ ወረቀት ፊታቸውን አዞሩ። ይህን ሁሉ ጊዜ የፈጀውም እስከዛ ጊዜ ድረስ አውሮፓውያንረ የእንሰሳት ቆዳን ይጠቀሙ ስለነበር ነው። ነገርግ በቆዳ ላይ መጻፍ በጣም ውድ ነበረ። አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ለመጠረዝ በትንሹ የ250 በጎች ቆዳ ቢያስፈልግም በወቅቱ ጥቂት ሰዎች ብቻ ያነቡ ስለነበር ብዙም አሳሳቢ አልነበረም።

ንግድ እየተጧጧፈ ሲመጣ ግን ውልና የሂሳብ ሳጥኖች እያስፈለጉ ሲመጡ ውድ ያልሆኑ መፍትሔዎች ተመራጭ እየሆኑ መጡ። ወረቀትም የወቅቱ ተፈላጊ ዕቃ ሆነ።

የጊዜው ተፈላጊ ዕቃ

ረከስ ያለው የወረቀት አማራጭም ደግሞ የብዙ ነጋዴዎችን ትኩረት እየሳበ መጣ። ምክንያቱም ለረጅም ጽሑፍ በሚልዮን የሚቆጠሩ በጎችን ቆዳ መጠቀም አዋጪ አልነበረምና።

ሕትመትም ወረቀት ለመጠቀም ከመጀመሪያዎቹ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ለግድግዳ ማሳመሪያ፣ ለማስታወቂያ፣ ለማሸግያና ለተለያዩ ጥቅሞች መዋል ጀመረ።

እ.አ.አ በ1870ዎቹ ስልክና አምፖል በተፈጠሩበት ዘመን፤ በእንግሊዝ ሃገር ያለ ድርጅት ስስ ሆኖ ጠንካራ ከዚያም በተጨማሪ ፈሳሽ የሚመጥ ወረቀት ሠራ።

ይህም ማለት የዓለማችንን የመጀመሪያ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት ተመረተ ማለት ነው። በዚህም ግኝት የአውሮፓን የመጀመሪያው ግዙፍ ኢንዱስትሪ እውን ሆነ።

Image copyright Getty Images

የማያቋርጥ መሻሻል

በመጀመሪያ ላይ ወረቀት ከጥጥ ይሠራ ነበር። ጥሬ ዕቃውን ለመፍጨት ኬሚካል መጠቀም ያስፈልግ ስለነበረ ለዚህ ደግሞ ከሰው ሽንት የሚገኘው አሞኒያ ጥቅም ላይ ውሏል። ስለዚህም ለዘመናት ወረቀት ማምረቻዎች ከሰዎች የሚወገደውን ቆሻሻ ይገለገሉ ነበር።

ወረቀትን ለመሥራት እጅግ ከፍተኛ ኃይልም ያስፈልግ ነበረ። ቀዳሚ ከሆኑት የወረቀት ማምረቻዎች አንዱ የነበረው ጣሊያኑ ፋብሪኣኖ፤ በፏፏቴ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ መዶሻዎችን ፈጠረ። ጥሬ ዕቃው በመዶሻው ተፈጭቶ በስሱ ከተዘጋጀ በኋላ እንዲደርቅ ተደርጎ ወረቀት ይሆናል።

በጊዜ ሂደት ወረቀት የማምረቱ ሂደት ማቆሚያ በሌላቸው ፈጠራዎች ውስጥ አልፏል። እ.አ.አ በ1702 ወረቀት በጣም ርካሽ ከመሆኑ የተነሳ የዓለማችን የመጀመሪያው ዕለታዊ ጋዜጣና ሌሎች የወረቀት ምርቶች ጥቅም ላይ በዋሉ በ24 ሰዓታት ውስጥ ይጣሉ ነበር።

ከዚያም ባልታሰበ ሁኔታ አውሮፓንና አሜሪካ በወረቀት ድርቅ ተመተው ያላቸው የወረቀት ጥሬ ዕቃ ክምችት ተሟጠጠ።

ዕጥረቱ ከባድ ከመሆኑም የተነሳ በጦርነት ላይ የወደቁ ወታደሮችን ልብስ በመግፈፍ ለወረቀት ፋብሪካዎች የሚሸጡ ሰዎችም ብቅ።

ብዙም ሳይቆይ ጥጥ ሊተካ የሚችል አማራጭ ተገኘ፤ እሱም እንጨት ሆነ። ይህን ዘዴ ቻይናውያን ወረቀት ለመሥራት እንጨትን ይጠቀሙ እንደነበር ቢታወቅም፤ አውሮፓውያኑ ችግር ግፍቷቸው ዘግይተው ነበር የደረሱበት።

ፈረንሳዊው ባዮሎጂስት ረኔ አንቷን ፌርሾ ደሬሙር እ.አ.አ በ1709 በፃፈው ሳይንሳዊ ጥናት ላይ፤ ተርቦች እንጨትን አኝከው የሚኖሩበትን የወረቀትቤት መሥራት ከቻሉ ሰዎችስ በዚሁ መልክ መሥራት እንዴት ያቅታቸዋል በማለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ከዓመታት በኋላ ያቀረበው ሐሳብ ሲፈተሽ፤ ወረቀት አምራቾች እንጨት የጥጥን ያህል ቀላል ጥሬ ዕቃ እንዳልሆነ ተገነዘቡ።

በምዕራቡ ዓለም በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ እንጨት ለወረቀት መሥሪያ ዋነኛ ጥሬ ዕቃ ሆነ ።

ባለንበት ዘመን በአግባቡ ተመልሶ ጥቅም ላይ እነዲውል ታስቦ ስለሚሰራ ቻይና ውስጥ በአብዛኛው ወረቀት የሚመረተው ከራሱ ነው ከወረቀት።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቻይናውያን ከ2000 ዓመታት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ዘዴዎች በመጠቀም እስከዛሬ ወረቀት ይሠራሉ

ለመጻፊያነት ከምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ኮምፕዩተር እየተስፋፋ ሲመጣ የወረቀት ጠቀሜታ እየቀነሰ ይመጣል ተብሎ ይታሰብ ነበር። በ1970ዎቹ ኮምፕዩተሮች ወደ ሥራ ገበታችን በመጡ ጊዜም እውን እየመሰለ ቢመጣም እስከ ዛሬ ግን ወረቀትን እንጠቀማለን። ኮምፕዩተር ሰነዶችን በቀላሉና ያለወረቀት መቀባበል ቢያስችልም ፕሪንተሮች ደግሞ ሰነዶችን በወረቀት ላይ ለማስፈር ቀላል አደረጉት።

የዓለማችን ወረቀት ፍጆታ በ2013 እ.አ.አ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደረሰ።

ዘንድሮም ብዙዎቻችን በኮምፒውተር መስኮት ላይ ከማንበብ ከመቀይር ይልቅ የወረቀት ገጽ መግለጥ እንመርጣለን። ነገር ግን ካለወረቀት የሚከናወነው የዲጂታል ህትመት ዋጋ በጣም ቅናሸ ስለሆነ ተፈላጊነቱ በመጨመር ላይ ነው።

ወረቀት በቆየው ዘመን የነበረውን ከብራና በልጦ ከስርጭት እንዳስወጣ ሁሉ፤ በጥራት ሳይሆን በዋጋው ርካሽነት ምክንያት ዲጂታልም ወረቀትን ሊያስወጣ ይችላል።

የወረቀት ጥቅም ላይ መዋል እየቀነሰ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮችና በመፀዳጃ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በቢሮዎች ውስጥም አገልግሎት እየሰጠ መቀጠሉ አይቀርም።