ስለ ኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምን ያህል ያውቃሉ?

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂን የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ

ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት የትኛውም ቃለ መጠይቅ ምንም አይነት ነገር ስለ ግለ ህይወታቸው አውርተው የማያውቁት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ጥቂት የሚባሉ ሰዎች ብቻ ስለ ግል ህይወታቸው ያውቃሉ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ማን ናቸው?

ኢሳያስ አፈወርቂ በ1936 ዓ.ም በአስመራ ከተማ ነው የተወለዱት። የሁለተኛ ደርጃ ትምህርታቸውን በልዑል መኮንን ሁለተኛ ደርጃ ት/ቤት ተከታትለዋል።

ያስመዘገቡት ከፍተኛ ነጥብ የቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአሁኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ትምህርት እንዲከታተሉ ቢያስችላቸውም በ1958 ዓ.ም ትምህርታቸውን አቋርጠው የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባርን ለመቀላቀል ወደ ሱዳን ተጓዙ።

ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር አባል ከነበሩት ሳባ ሃይሌ ጋር ትዳር መስርተው በአሁኑ ጊዜ የሁለት ወንዶችና የአንድ ሴት ልጅ አባት ናቸው።

ሃይማኖታቸው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከዓለማችን በቁመት ረጅም ከሚባሉት የሃገር መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

በአፍሪካ ለረጅም ዓመታት በሃገር መሪነት በስልጣን ላይ ከቆዩ ፕሬዝዳንቶች መካከልም ይመደባሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የትግል ህይወት

የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባርን ከተቀላቀሉ በኋላ የትግል ስልቱ ስላልተስማማቸው ከጥቂት ጓዶቻቸው ጋር በመሆን የራሳቸውን ሚስጥራዊ ቡድን አቋቋሙ።

በመቀጠልም አቶ ኢሳያስና ጓደኞቻቸው በኤርትራ ለሚያደረጉት ትግል የውትድርና ስልጠና ለመውሰድ ወደ ቻይና አቀኑ። በቻይና የሁለት ዓመት ቆይታቸው ስለ ተለያዩ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞችና የደፈጣ ውጊያ ስልቶች ስልጠና ወስደዋል።

በ1960 ዓ.ም ከቻይና መልስ የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር አመራር ሆነው አገልግለዋል።

በ1962 ዓ.ም የኤርትራ ነጻነት ግንባር ውስጡ በተፈጠረ አለመስማማት በሦስት ቦታ ተከፈል። ከ10 ያልበለጡ አባላት ነበሩት የኢሳያስ አፈወርቂ ቡድን ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ ኤርትራ በመሄድ ትግሉን ጀመረ።

በ1963 ኢሳያስ አፈወርቂ የብሄርና የኃይማኖት ልዩነቶችን ስለማጥበብና የተቀናጀ ትግል ስለማካሄድ የሚያትት ''ትግላችንና ግቡ'' የተሰኘ ማኒፌስቶ ጽፈው ነበር።

በ1967 የተበተነውን ግንባር እንደገና በማሰባሰብ ኢሳያስ አፈወርቂን የወታደራዊ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር አድርጎ መረጠ። በ1969 ደግሞ ኢሳያስ የግንባሩ ምክትል ዋና ጸሃፊ ሆነው የተመረጡ ሲሆን በ1979 የግንባሩን ዋና ጸሃፊ ሆነው ተመረጡ።

ከነጻነት በኋላ

የ1985ቱን ህዝበ-ውሳኔን ተከትሎ ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት እና የብሔራዊ ምክር ቤቱ ዋና ጸሀፊ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ ይህም የመንግሥትን የሥራ አስፈጻሚ እና የፍትህ አካሉን በቁጥጥራቸው ስር እንዲሆን አስችሏቸዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት ህዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በሃገሪቱ የሚገኘው ብቸኛው የፖለቲካ ፓርቲ ሲሆን ከመስራቾቹ መካከልም አንዱ ናቸው።

በ1989 ዓ.ም ጸድቆ የነበርው ሕገ-መንግሥትም ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቷል።

በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና በሃገሪቱ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ኣላመጣም ተብሎ በተደጋጋሚ ይወቀሳል።

በ1990 ኢትዮጵያና ኤርትራ በድንበር ምክንያት ወደ ጦርነት ገቡ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ለሁለት አስርት ዓመታት ተፋጠው የነበሩት ኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዟቸው ምን ይመስላል?