የአፍሪካውያን ድንቅ የፈጠራ ውጤቶች

የኤሌክትሪክ ኃይል ለገጠር መንደሮች

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የኤሌክትሪክ ኃይል

መፍትሄ የሚሻ ችግር፡ ያል ኢንቫይሮመንት 360 እንደሚለው ከዓለማችን ህዝብ 1.3 ቢሊዮን የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም። የገጠር ነዋሪዎችን ከትላልቅ የኃይል ማሰራጫዎች ተጠቃሚ ለማድረግ አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ የተለመዱት የፀሃይ ኃይል ማመንጫዎች ደግሞ ውስን ሃይል ብቻ ነው የሚያመነጩት።

መፍትሄ፡ ሙሉ መንደርን ከፀሃይና ከባትሪ ሃይል በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያገለግል የሚችል አነስተኛ የኃይል ማከፋፈያ ስቲማኮን የተባለው ድርጅት ሰርቷል።

እንዴት ይሰራል፡ አነስተኛ የኃይል ማከፋፈያ አዲስ ነገር ባይሆንም፤ የስቲማኮን ቴክኖሎጂን ልዩ የሚያደርገው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ሥርዓት ያለው መሆኑ ነው።

ስለዚህም፤ አገልግሎት በሚሰጥበት አካባቢ የኃይል ፍላጎት በድንገት ከፍ በሚልበት ወይም ደግሞ ፀሃይ በምትጠልቅበትና በቂ ኃይል ለማመንጨት በማይቻልበት ጊዜ፤ የኃይል ማከፋፈያው ኤሌክትሪክ ቢቋረጥባቸው ብዙም የማይጉዱ ተጠቃሚዎችን የኃይል አቅረቦት ወዲያውኑ እንዲቋረጥ ያደርጋል።

ይህም ሲሆን እንዲሁ በደፈናው ሳይሆን በሃይል እጥረት ምክነያት ሃኪም ቤትን የመሳሰሉ ጠቃሚ የህዝብ ተቋማት አገልግሎት እንዳይስተጓጎል የመኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማቋረጥ እንዳስፈለገ የሚገልፅ አጭር የፅሁፍ የማስጠንቀቂያ መልዕክትን ለተጠቃሚዎቹ ይልካል።

የሳምባ ምችን የሚመረምር ጃኬት

Image copyright BRETT ELOFF
አጭር የምስል መግለጫ የሳምባ ምች መመርመሪያ

መፍትሄ የሚሻ ችግር፡ በየዓመቱ ኡጋንዳ ውስጥ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 27 ሺህ ህፃናት በሳምባ ምች ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የሚከሰቱት የሳምባ ምች የወባ በሽታ እንደሆነ ተደርጎ በተሳሳተ የምርመራ ውጤት ምክንያት ነው።

መፍትሄ፡ ኡጋንዳዊው መሃንዲስ ብሪያን ቱርያባግዬ የሳምባ ምችን በፍጥነትና በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል የመመርመሪያ ጃኬት ሰርቷል። ማሞፕ የተባለው ይህ ጃኬት የታመሙ ህፃናትን የሰውነት ሙቀትና የአተነፋፈስ ሁኔታን ይለካል። የሳምባ ምችን አንድ ሃኪም ለመለየት ከሚወስድበት ጊዜ ከሶስት እስከ አራት እጥፍ በሚደርስ ፍጥነት ለማወቅ ከማስቻሉ በተጨማሪ በምርመራ ጊዜ ሊያጋጥም የሚችልን የሰው ስህተት ያስወግዳል።

እንዴት ይሰራል፡ የሃኪሞች ማዳመጫ በተለይ ተሰርቶ ከጃኬቱ ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ከሞባይል መተግበሪያ ፕሮግራም ጋር በማገናኘት ከህመምተኛው ደረት ጋር በሚነካካበት ጊዜ የሚወጣው ድምፅ ይቀረፃል። በዚህም ከሳምባ የሚወጣውን ድምፅ መሰረት አድርጎ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤት ላይ ለመድረስ ይቻላል።

ከርቀት የልብ ምርመራን በቀላሉ ለማድረግ

አጭር የምስል መግለጫ የልብ መመርመሪያ

መፍትሄ የሚሻ ችግር፡ በተለይ በገጠር የሚኖሩ ሰዎች የልብ ምርመራና ህክምና ለማግኘት ወደ ከተሞች ለመሄድ ይገደዳሉ፤ ይህ ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ ነው። 20 ሚሊዮን ህዝብ ላላት ካሜሮን 50 የልብ ሃኪሞች ብቻ አገልግሎት ይሰጣሉ።

መፍትሄ፡ አርተር ዛንግ ይህንን ችግር ለማቅለል በገጠር የሚገኙ የጤና ሰራተኞች፤ በቀላሉ በእጃቸው ይዘው የልብ ምርመራ ውጤቶችን በከተሞች ለሚገኙ የልብ ሃኪሞች በሞባይል ስልኮቻቸው አማካይነት ለመላክ የሚያስችላቸውን ካርዲዮፓድ የተባለ መሳሪያ ፈልስፏል።

እንዴት ይሰራል፡ ይህ መሳሪያ ካለምንም ክፍያ ካሜሮን ውስጥ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ተከፋፍሏ። መሳሪያው የህሙማኑን የልብ ተግባር መዝግቦ የሚይዝ ሲሆን በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ የልብ ምርመራ ውጤቱም ዋና ከተማዋ ውስጥ ወደሚገኙ ልዩ የልብ ክሊኒኮች ይላካል።

ተያያዥ ርዕሶች