የሚጣሉ ልብሶች መጨረሻ ምን ይሆን?

ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶች

ብዙዎቻችን ያረጁ ወይም የማንፈልጋቸውን ልብሶቻችንን እንሸጣቸዋለን ወይም በዕቃ እንለውጣቸዋለን። አንዳንዴም በዕርዳታ መልክ ለሌሎች እንሰጣቸዋለን።

ከእነዚህ ልብሶች ውስጥ ወሳጅ ያጡት፣ የተሸጡት ወይንም ተቀዳደው የተጣሉት መጨረሻ ምን ይሆን?

የአብዛኛዎቹ ልብሶች መዳረሻ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አሮጌ ልብሶች በሚገዙበትና በሚሸጡበት የህንድ ገበያ ነው። በተለይ ደግሞ የአሮጌ ልብሶች መናገሻ ወደ ሆነችው የሰሜን ህንዷ ፓኒፓት ያቀናሉ።

ከአሜሪካና ከእንግሊዝ በተጨማሪ ከተለያዩ የዓለም አገራት በመቶዎች ቶን የሚመዘን ልብስ በየቀኑ ወደ ህንድ ይጓጓዛል።

ከመላው ዓለም የተሰበሰቡት እና በምዕራባዊ የህንድ የወደብ ከተማ ካንዳላ የሚገቡት ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶች በጭነት መኪና ወደ ፓኒፓት ይጓጓዛሉ። እነዚህን ልብሶች የጫኑት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች ወደ ከተማዋ ለመግባት ሰልፍ ይዘው ይታያሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ፋብሪካዎቹ ልብሶቹን በየቀለማቱ ይለዩዋቸዋል

በቅርቡ ይፋ እንደሆነ መረጃ ከሆነ ህንድ ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሩሲያ እና ፓኪስታንን በመብለጥ ቀዳሚ ሆናለች።

በህንድ ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶች በሁለት ይከፈላሉ። የተቀዳዱና ልባሽ ልብሶች በሚል። በህንድ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾችን መብት ለመጠበቅ ሲባል መለበስ የሚችሉ ልብሶችን ለማስገባት ፈቃድ ማውጣት ያስፈልጋል።

ገዢዎች ልብሶቹን ከህንድ ውጭ ብቻ እንደሚሸጡ ሲያረጋግጡ ነው ፈቃዱ የሚሰጣቸው።

ሆኖም ወደ ህንድ ከሚገባው ጥቅም ላይ የዋለ ልብስ አብዛኛው የተቀዳደደ ስለሆነ ይህንን ለማስገባት ምንም ፈቃድ አያስፈልግም።

ሻንካር ዎለን ሚልስ በሚባለው አንድ የልብስ ማደሻ ፋብሪካ መሬት ላይ የተለያየ ቀለም ያላቸው በመቶዎቸው የሚቆጠሩ የልብስ ቁልፎች ይታያሉ።

ወቅቱ በጋ ከመሆኑ በተጨማሪ የፋብሪካው ወበቅ እና የልብሶቹ ክምር አካባቢውን ይበልጥ ሞቃታማ አድርገውታል።

በየቦታው ጃኬቶች፣ ቀሚሶች፣ ሹራቦች፣ የተለያዩ ኮፍያዎችና የትምህርት ቤት ዩኒፎርሞች ፋብሪካው ውስጥ የልብስ ተራራ እንዲፈጠር አድርገዋል።

ከፋሽን እስከ ውድ ልብሶች ድረስ መዳረሻቸው በዚሁ ፋብሪካ ነው። ልባሽ እና የተቀዳደዱ ልብሶች በብዛት እዚሁ ይደርሳሉ።

ፋብሪካ ውስጥ ሠራተኞች ትልልቅ ቢላዋዎችን በመጠቀም ልብሶቹን ሲቀዱ ይታያሉ። በዚህም ከዚፖች፣ ቁልፎችና የንግድ ምልክቶች ውጭ ያሉ ነገሮች በሙሉ ይቀደዳሉ።

የተቀዳደዱት ልብሶች እንደየቀለማቸው አይነት በተለያዩ ትልልቅ ማስቀመጫዎች ውስጥ ይጠራቀማሉ። ይህም ልብሶቹ ወደ ክር ተቀይረው ወደ ሚያማምሩ ጨርቆች የሚሸመኑበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው።

ከዚህ በመቀጠልም በተመሳሳይ ቀለም ካላቸው ልብሶች ጋር ተቀላቅለው ስራው ይቀጥላል።

"የሰው ጉልበት የማይሰራቸውን ማሽን በመጠቀም ወደ አነስተኛ ቁርጥራጮች ይቀይራሉ። ቁርጥራጮቹን ወደ ትልቅ ማሽን በማስገባት የተለያዩ የጨርቅ አይነቶች በማቀናጀት ቀጫጭን ጨርቆችን ይሰራል" ሲል የሻንካር ዉለን ሚልስ የስራ ሃላፊ አሽዊን ኩማር ይገልጻል።

ከእያንዳንዱ ሶስት ቶን ልብስ አንድ ነጥብ አምስት ቶን አዲስ የጨርቅ ክር የሚመረት ሲሆን ይህም የጨርቅ ጥጥ ለመስራት ያግዛል። የጨርቁ ጥጥ ደግሞ ብርድ ልብስ ለመስራት የሚውል ነው።

እንደ ኩማር ገለጻ ከሆነ ብርድ ልብሶቹ በተለይም እንደ ሱናሚ፣ ሳይክሎን ወይንም የመሬት መንቀጥቀጥ ባሉ አደጋዎች ወቅት በመላው ዓለም የሚሰራጩ ይሆናል። ካልሆነም እስከ ሁለት ዶላር በሚሆን ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ይሸጣል።

አጭር የምስል መግለጫ ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶች ብርድ ልብሶችን ለመስራት ያግዛሉ

ከሚመረቱት ብርድ ልብሶች የአብዛኛዎቹ መዳረሻ አፍሪካ ነው።

አብዛኛዎቹ የብርድ ልብስ አምራቾች ተጨማሪ ገበያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ አፍሪካ ያቀናሉ። ብርድ ልብሶቹ በህንድ ገበያም የሚሸጡ ሲሆን ቁጥራቸው ግን አነስተኛ ነው።

ጥቅም ላይ የዋሉትን ልብሶች ከውጭ ለማስገባት አነስተኛ ገንዘብ ቢያስፈልግም፤ በአንድ ወቅት ውጤታማ የነበረው ሥራ አሁን ውድ እየሆነ መምጣቱን ኩማር ይናገራል።

"ጥቅም ላይ የዋሉት ልብሶች ህንድ ሲደርሱ ለጉምሩክ፣ለትራንስፖርት፣ ለመጋዘን፣ ለመብራትና ለሰው ጉልበት የሚፈጸመው ክፍያ መሸጫ ዋጋውን ያንረዋል። በዚህም በአፍሪካ የሚገኙ ገዢዎች የሚፈልጉትን አይነት ርካሽ ብርድ ልብስ ለማቅረብ ያዳግተናል።"

ከዚህ በተጨማሪ ኢንዱስትሪው እንደፖሊስተር ካሉ ሰው ሰራሽ እና አነስተኛ ዋጋ ካላቸው ጨርቆች ፉክክር እየገጠመው ይገኛል።

እንደ ኦል ኢንዲያን ዉለን ኤንድ ሾዲ ሚልስ ፕሬዝዳንት ፓዋን ጋርግ ችግሩ እንዱስትሪዎቹን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ነው።

"ቀደም ሲል 400 የሚሆኑ ፋብሪካዎች የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ቁጥራቸው ከ100 በታች ሆኗል። ይህም ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ያሳያል። ኢንዱስትሪዎቹ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ አይደለም። በየቀኑ አንድ ፋብሪካ ምርቱን ይቀንሳል ወይም ይዘጋል። ቀደም ሲል ሳምንቱን ሙሉ 24 ሰዓት ይሰራ ነበር። አሁን ግን ስራው በፈረቃ ሆኗል" ሲል ያለውን ችግር ይገልጻል።

ኢንዱስትሪው ስራውን እየቀነሰ መምጣቱ ችግሩ በህንድ ብቻ የሚያበቃ አይደለም ይላል ኩማር። ስለዚህ ምዕራባዊያንም ኢንዱስትሪውን እንዲረዱት ሃሳብ ያቀርባል።

"እዚህ የምንሰራው ስራ በጣም ጠቃሚ ነው። ጥቅም ላይ የዋሉ ልብሶችን መልሰን መጠቀም ካልቻልን የቆሻሻ ክምር በመፍጠር አካባቢንም ይጎዳሉ።"

"ህንድ ውስጥ ምንም ቆሻሻ ተብሎ የሚጣል ነገር የለም። ልብሶቻችንን ለሚፈልጉ ሰዎች እንሰጣቸዋለን። ከዛ በኋላም ልብሶቹን የምንጠቀምበትን ዘዴ እንፈልጋለን። በዚህ ምክንያትም የትኛውንም የማልጠቀመውን ልብስ ወደ ቆሻሻ መጣያ አልጥልም" ሰል ሃሳቡን ያጠቃልላል።