መነሻ ሀሳብ ወይስ የሙዚቃ ቅጂ መብት ጥሰት?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ 'ብለርድ ላይንስ' የተሰኘው ሮቢን ቲኬ ከፋረል ዊሊያምስ ጋር የተጫወቱት ሙዚቃ ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል።

በአሁኑ ወቅት አርቲስቶች ሙዚቃ ሲሰሩ መነሻ ሀሳቡን ከሌላ ቀደምት አርቲስት መውሰዳቸውን እንዳይናገሩ ይመከራሉ። ምክንያቱም የሙዚቃ ኮፒ መብት ሕግን ተጠቅመው የዋናው ዜማ ባለቤቶች እንዳይከሷቸው። ይህ ነገር ለሙዚቀኞች ፈጠራ መፈናፈኛ ያሳጣቸዉ ይሆን?

"በሙዚቃ ጥበብ ውስጥ ዋና ወይም አዲስ የፈጠራ ስራ የሚባል ነገር የለም" የሚለዉ የሙዚቃ አቀናባሪው እና ዜማ ቀማሪው ናይል ሮጀርስ "ሙዚቃን ምንማረው በልምምድ ነው. . . ምንድነው የምንለማመደው? ንድፍ እና መለኪያውን ነው። ሙዚቃን መስራት ማለት እነዚህ የተማርናቸውን ህጎች ተግባር ላይ ማዋል ማለት ነው።'' በማለት ጨምሮ ያስረዳል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ የሙዚቃ ሰንጠረዦቸን ብናጠና ሙዚቃ ሰሪዎች ከሚያደንቋቸው እና እንደ አርኣያ ከሚያይዋቸው ቀደምት እና ዘመናዊ ሙዚቀኞች መነሻ ሀሳብ ያልወሰደ ማግኘት ይከብዳል። በአሁኑ ወቅት ግን ሙዚቀኞቹ መነሻ ሀሳብ የወሰዱበትን ቀደምት አርቲስት ስም እንዳይናገሩ ይበረታታሉ።

ይህም ሁኔታ ሮቢን ቲክ እና ፋረል ዊሊያምስ 'ብለርድ ላይንስ' ብለው ለተጫወቱት ሙዚቃ መነሻ ዜማውን ከማርቪን ጌይ 'ጋ ቱ ጊቭ ኢት አፕ' ወስዳችሗል በሚል ለማርቪን ጌይ ቤተሰቦቹ 7.3 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መክፈል ግድ ሆኖባቸዋል። ምንም እንኳን ፍርድ ቤት አሁንም ጉዳዩ በይግባኝ ምክንያት እንደተጠለንጠለ ቢሆንም።

ይህ ክስተት ለብዙ ሙዚቀኞች ትልቅ መልዕክት ትቶ ያለፈ እንደሆነ ይነገራል። ፋረል ዊሊያምስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ስለ ጉዳዩ አስተያየት ሲሰጥ የማርቪን ጌይ 'ጋ ቱ ጊቭ ኢት አፕ' እና ሌሎች ሙዚቃዎችን እየሰማ ያደገ በመሆኑ የ70ዎቹን ሙዚቃ መልሶ ወደ ገበያው ለማምጣት ያደረገው ጥረት እንጂ ኮፒ ለማድረግ አስቦ እንዳልነበረ አሳውቋል።

እንደ ሙዚቃ ባለሙያው ፒተር ኦክሰንዴል አባባል "መነሻ ሀሳብ አሁን አሁን ከኮፒ መብት ሕግ ጥሰት ጋር እየተያያዘ ስለሆነ ነገሩ ለሙዚቃ ሰሪዎች አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።" ፒተር አክሎም "ሙዚቃ አምራች ኩባንያዎች አንድ አዲስ ሙዚቃ ቀደም ካለ ሙዚቃ ጋር በሆነ መልኩ ግንኙነት ካለው ጉዳዩ ያስጨንቃቸዋል'' ይላል።

Image copyright Getty Images

የፉጨት መብት

ከማርቪን ጌይ ቤተሰቦች ጋር የሚሰራው ጠበቃው ሪቻርድ ቡስክ እንደሚለው ከሆነ ግን 'ከብለርድ ላይንስ' ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ማለትም ክሱ በስሜት ላይ ተሞርኩዞ ነው የተመሰረተው የሚባለው ሀሰት እንደሆነ ይናገራል። ''ሰማዩ ሊደፋ ነው። ሙዚቀኞች መስራት እየቻሉ አይደለም። በአደባባይ ሟፏጨት እንኳን ያስከስሳል እየተባለ የሚወራው ከነ ፋረል ዊሊያምስ እና ሮብን ቲኬ ሰፈር የተነዛ አሉባልታ ነው" ሲል ያጣጥለዋል።

"እንደውም እንደ እውነታው ከሆነ ጉዳዩ መረን ለቋል። ለምሳሌ በ 'ብለርድ ላይንስ' እና በ 'ጋ ቱ ጊቭ ኢት አፕ' መካከል ወደ 15 የሚሆኑ ቅንብራዊ መመሳሰሎች አሉ።" በማለት ሪቻርድ ይናገራል

ያም ሆኖ ለእነ ኤድ ሺረን፥ ኤልተን ጆን፥ እንዲሁም ሮሊንግ ስቶን ጠበቃ ሆነው ከሚያገልግሉት አንዱ የሆነው እንግሊዛዊው ሳይመን ዲክሰን ሲናገር በሙዚቃ ኮፒ መብት እና በመነሻ ሀሳብ መካከል ባለው ግጭት ብዙ የሙዚቃ ባለሙያዎች እየተማረሩ ነው።

"ተመሳሳይ ጉዳየች እዚህ እንግሊዝ ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ቢሄዱ ጉዳዩ ከአሜሪካ በተለየ ሁኔታ ነው የሚዳኘው" ይላል ዲከሰን።

ሙዚቃ

እንግሊዛዊቷ ዘፋኝ እና የግጥም-ወዜማ ደራሲ ሎውራ ምቩላ ግን "ሙዚቀኞች የራሳቸውን የፈጠራ ስራ መስራት ከቻሉ ሌሎች ነገሮች የሚያሳስቡ አይደሉም" ትላለች። "ሁላችንም የሆነ የሚያነሳሳን ነገር ይኖራል። ተጽዕኖ የሚፈጥርብንም ነገር አይጠፋም። ነገር ግን የሙዚቀኛው ትልቁ ፈተና ሁሌም አዲስ ነገር ይዞ በመምጣት ወደፊት መጓዝ ነው" በማለት ጨምራ ትናገራለች።

ሌላኛው ዘፋኝ እና ግጥም-ወዜማ ደራሲ ጌሪ ኑማንም በሎውራ ሀሳብ ይስማማል። "ሁላችንም ሀሳብ የምናመነጨው ካለ ነገር ነው። ብልጠቱ የሚሆነው ይሄንን ሀሳብ ተጠቅሞ አዲስ ነገር መፍጠሩ ላይ ነው" ይላል።

ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የ'ብለርድ ላይንስ' ጉዳይ በይግባኝ ጥያቄ መሰረት እንደገና ወደፍርድ ቤት ይቀርባል። በአሁኑ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የ'ብለርድ ላይንስ' ዘፋኞች እንደሚሳካላቸው ተስፋ ያደርጋሉ። ወጤቱ ምንም ይሁን ምን ግን የሙዚቃ ኢንዱስትሪው በኮፒ መብት ሕግ ላይ ያለው አቋም አወዛጋቢ እንደሆነ ይቀጥላል።

ተያያዥ ርዕሶች