ቡናን መጠጣት ካሉት ሌሎች ጠቀሜታዎች በተጨማሪ እድሜን ያረዝማል ይባላል

በቡና እና በዕድሜ መካካል ያለው ግንኙነት ብዙዎችን እያወዛገበ ነው

በእንግሊዝ አገር የሚገኝ አንድ የጥናት አሳታሚ ተቋም አዲስ የወጣ ጥናት መሰረት አድርጎ እንደጠቆመው በቀን ውስጥ ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት የጠጪውን እድሜ ላይ ለውጥ ያመጣል ይላል። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ግን ጥናቱ አላስደሰታቸውም። የአንድ ግለሰብን ሌላ የህይወት ልምምድ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ፤ በቀን ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት ብቻውን እድሜን ያራዝማል ብሎ መደምደሙ ተቺዎቹ ጥናቱን በጥርጣሬ እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።

ጥናቱ ምን አለ?

በኢንተርናሽናል የካንሰር ምርምር ኤጀንሲና በኢምፔሪያል ለንደን ኮሌጅ ጥምረት የተሰራው ይህ አዲስ ጥናት እንደገለጸው በቀን ውስጥ ቡናን በርከት አድርጎ መጠጣት በተለይ ከልብ እና ከአንጀት ጋር ተያይዞ የሚመጣን ሞት በእጅጉ ለመቀነስ ያስችላል። እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እድሜያቸው ከሰላሳ አምስት ዓመት በላይ በሆኑ ከአስር የተለያዩ የአወሮፓ ሃገሮች የተወጣጡ ሰዎችን እንደናሙና መውሰድ አስፈልጓል። ተመራማሪዎቹ በጥናቱ ጅማሬ ላይ ለናሙና የተወሰዱትን ሰዎች የቡና አወሳሰድ መጠን ካጠኑ በኋላ በ16 ዓመት ሂደት አማካኝ የሞት መጠኑን ተከታትለዋል።

አንድ ስኒ ቡና ምን ያህል እድሜ ይጨምራል?

በዚህ አዲስ ጥናት ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ዴቪድ ስፒጌልሃልተር ሲያስረዱ በቀን አንድ ተጨማሪ ስኒ ቡና የሚጠጣ ወንድ እድሜው ላይ በአማካኝ በሶስት ወራት ያህል ሲጨምር ሴት ደግሞ በአንድ ወር ታራዝማለች። ምንም እንኳን ይህ አዲስ ጥናት በርካታ ባለሙያዎችን ያሳተፈና ዓመታት ፈጅቶ የተሰራ ቢሆንም ቡና እድሜን ማስረዘም አለማስረዘሙ ግን ሁሉንም ተመራማሪዎች እንዲስማሙበት አድርጎ አላቀረበም።

እርስዎ የቡና አፍቃሪ ከሆኑ ከዚህ የሚቀጥለው ላያስደስቶት ይችላል።

ጥናቱ አሻሚ መሆኑና ሌሎችን ከግምት ውስጥ መግባት የነበረባቸውን ማህበራዊና የጤና ጉዳዮችን ከግንዛቤ አለማስገባቱ የቡና ወዳጆችን ማደናገሩ አልቀረም። ለምሳሌ፤ ቡናን አብዝተው የሚጠጡ ሰዎች ገቢ ቡና ከማያዘወትሩት አንጻር ከፍተኛ ከሆነና የገቢያቸው ከፍ ማለት ለእድሜያቸው መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከት አለማበርከቱ ጥናቱ ከግንዛቤ ያለመውሰዱ አንዱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በቀን አንድ ስኒ ተጨማሪ ቡና መጠጣት አድሜን በሶት ወር ያስረዝማል

ሌላው ደግሞ ምናልባት ቡና አብዝተው የሚጠጡ በርካታዎች ጊዜያቸውን ከሰዎች ጋር በማሳለፋቸው ምክንያት ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት ፈጥረው እድሜያቸውን ረዝሞ መሆን አለመሆኑን ጥናቱ ከግንዛቤ አላስገባም። በተጨማሪም ቡና እድሜን ከመጨመሩ ባሻገር ተጓዳኝ የጤና እክሎችን መፍጠር አለመፍጠሩ ጥናቱ አለማካተቱ ተቀባይነቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

ምክንያቱም በቅርቡ ሌሎች ተመራማሪዎች ቡና መጠጣትን ከሴቶች የማህፀን ካንሰር ጋር አያይዘውት እንደነበር አይዘነጋም። ከሁሉ በላይ ደግሞ የጥናት ወረቀቱ የስኳር እና የልብ ህመምተኞችን በናሙናነት አለመጠቀሙ፤ ቡና በመጠጣት ብቻውን እድሜ ይጨምራል ብሎ ለመደምደም እንዳንችል ያደርገናል ተብሏል።

እው ቡና ጠቃሚ ነው?

ከዚህ ጥናት በፊት በቡና መጠጣት ላይ የተሰሩ ጥናቶች በሙሉ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው። የቡና የማነቃቃት ሃይል የብዙ ቡና አፍቃሪዎች ልክፍተኛ መሆን ምክንያት እንደሆነ እሙን ነው። ነገር ግን በቡና ውስጥ ያለው ካፌይን የተባለው ንጥረ ነገር የማናቃቃት ሃይሉ ከሰው ሰው ይለያያል።

የእንግሊዝ የጤና ባለሙያዎች ለአጠቃላይ ቡና ተጠቃሚዎች ቡና የመጠጣት ልኬት ባያወጡም ለነፍሰ ጡር ሴት ግን በቀን ከ200 ሚሊ ግራም በላይ የካፌይን መጠን በቀን እንዳትወስድ ያስጠነቅቃሉ። ምክንያቱንም ሲያስረዱ የሚወለደው ጨቅላ የክብደት መጠን ከሚጠበቀው በታች ከማድረግ አልፎ አንዳንዴም ጭንገፋን ሊያስከትል ይችላል ይላሉ።

ካፌይን የተባለው ንጥረ ነገር ግን ከቡና አልፎ በሌሎችን መጠጦች ውስጥ መገኘቱ ጉዳዩን አከራካሪ ያደርገዋል። ለምሳሌ 200 ሚ.ግ ካፌይንን በሁለት ማግ የሻይ ብርጭቆ ውስጥ እና አንድ ጠርሙስ ኮላ መጠጥ ውስጥ በቀላሉ ይገኛል። አሜካዊቷ ታዳጊ በተከታታይ የካፌይን ንጥረ ነገር ያለውን መጠጥ በመውሰዷ ህይወቷ ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ታዲያ ቡና እድሜ እንደሚጨምር በምን እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ቡና እድሜ መጨመር አለመጨመሩን በሳይናሳዊ ምርምር እርግጠኛ ለመሆን የናሙና መጠኑን ማብዛት ጥሩ አማራጭ ነው።

ይህም ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የተወጣጡ በሚሊዩን የሚቆጠሩ ሰዎችን በናሙናነት በማሳተፍ እያንዳንዷን የህይወታቸው ክፍል ማጥናት የግድ ይላል። ይህም የሚበሉትና የሚጠጡትን፥ የገቢያቸውን ሁኔታ እንዲሁም ስፖርታዊ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እና አለማድረጋቸውን ሁሉ ግምት ውስጥ አስገብቶ ማጥናት ማለት ነው።እንደዚህ አይነት ጥናት አይታሰብ ከተባለ ደግሞ አዋጭ እና ሁሉም ተመራማሪወች የተስማሙበት እድሜን መጨመሪያ ዘዴ መፈጸም ግድ ይልል። በቀን ለ20 ደቂቃ ያህል የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ።