በጥቅም ላይ የዋሉ የጥንታዊ ግብፅ የህክምና ጥበባት

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በአምስት ሴቶች እርዳታ የማዋለድ ሥርዓት

በጥንታዊ ግብፅ ህክምና ከጥንቆላ ጋር ከመተሳሰሩ በተጨማሪ ሳይንስና ሀይማኖትም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ነበራቸዉ።

በሽታ የሚመጣዉ በአማልክት ቁጣ እንዲሁም በሰዉ ልጅ ዉስጥ ያለዉ መጥፎ መንፈስ ተብሎ ነዉ ስለሚታመን መንፈሱን ለማራቅ የተለያዩ ስርኣቶች ይፈፅሙ ነበር።

ከነዚህም ዉስጥ ጠልሰም፤ የተለያዩ ድጋሞች፤ መነባንብና ምልክቶች ይገኙበታል።

እነዚህ ጥበባት መንፈስን ከማራቅ በተጨማሪ በሳይንሳዊ ምርምር ላይ ያተኮሩና አሁን ህከምና ለደረሰበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉና ዘመንንም ተሻግረዉ ኣሁንም በአገልግሎት ላይ ያሉ ናቸዉ።

ምንም እንኳን በአሳዛኝ ሁኔታ ከኣሌክሳንድሪያ ሮያል መፃህፍት ቤት መዉደም ጋር ተያይዞ የጠለቀ መረጃ ባይገኝም ከክርስትና መምጣት 3000 ኣመት በፊት ምን ያህል የሰለጠነና የበለፀገ ባሕል እንደነበር የሚጠቁሙ ብዙ መረጃዎች ተገኝቷል።

እነዚህ መረጃዎች ከሺዎች አመታት በፊት ለነበሩ የህክምና ጥበባት የረቀቁ እንደነበሩ ጠቋሚ ናቸዉ።

ዘመናትን ተራምደዉ እዚህ ከደረሱ የረቀቁ ህክምና ልምዶች ዉስጥ የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸዉ።

ቀዶ ጥገና

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጥንታዉያን ግብፆች ስለሠዉ ልጅ የተለያዩ አካላትና ተግባራት ጠለቅ ያለ እዉቀት የነበራቸዉ ሲሆን ይሄም ከመግነዝ ባህላቸዉ ጋር ተያይዞ የመጣ ነዉ።

የሞተን ሰዉ በሚገንዙበት ወቅት አካሎቹን ለያይተዉ የታመመዉን ለይተዉ በማየት የበሽታዉን ሁኔታ ምን እንደነበር ይመራመሩ ነበር።

ይሄም ሁኔታ በቀላሉ ቀዶጥገና እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸዉና የጭንቅላት እጢንም ቆርጠዉ የሚያወጡበትንም ቴክኒክ ማዳበር ችለዉ እንደነበር በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ የቁፋሮ ምርምሮች ያሳያሉ።

የጥርስ መሙላትና ማስተካከል ስራ

Image copyright Getty Images

የምግብ አዘገጃጀት በከፍተኛ ጉልበትና በእጅ እንደመሰራቱ መጠን ምንም ያህል የተለያዩ ጥራጥሬዎችን አድቅቀዉ ወደ ዱቄት ለመለወጥ ለመፍጨት ቢሞክሩም ምግብ ዉስጥ ሳይፈጩ ያመለጡ ጠጠሮች ወይም አሸዋ ማግኘት የተለመደ ነዉ።

ይሄም ሁኔታ በጥርስና በጥርስ መካከል ከፍተኛ ክፍተትን እንዲሁም በድድ አካባቢ ቁስለትን ይፈጥር ነበር።

ለዚህም መፍትሄ ለማግኘት እንዲሁም በተጨማሪ የጥርስ መጠዝጠዝን ለመቀነስ፥ የተቦረቦረ ጥርስን ለመሙላት መድሐኒቶችንና ቅባትን ይጠቀሙ እንደነበር በህክምናዉ ዘርፍ ጥልቅ ምርምር የተደረገበት 'ኢበርስ' የተባለዉ የፅሁፍ ዉጤት ያስረዳል።

ለነዚህ ህመሞች የራሳቸዉን ያሉትንም መፍትሄ ትተዋል።

ለምሳሌም ለሚጠዘጥዝ ድድ ፈዉስ ይሆናል ብለዉ ያስቀመጡት የከሙን፤ዕጣን፤የፍራፍሬዎች ዉህድ ነዉ።

አንዳንድ ዉህዶች ማር የሚጨመርባቸዉ ሲሆኑ በሽታን ከመፈወስ በተጨማሪ በዋናነትም በሽታን ለመከላከል ይጠቀሙበታል፤ ከዚህም በተጨማሪ ክፍተቶች ሲኖሩ በላይነን ጨርቅ ይሸፍኑት ነበር።

ፕሮስተሲስ (በሰዉ ሰራሽ ኣካል መተካት)

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በጥንታዉያን ግብፅ በሌዘር አማካኝነት ከእግር ጋር የተያያዘ ከእንጨት የተሰራ ሰዉሰራሽ ጣት

የጥንት ግብፃዉያን በህይወት ላሉም ሆነ ለሞቱትም ሰዉ ሰራሽ አካል መተካት የቆየ ልምድ ነዉ።

የሰዉን ልጅ የቀን ተቀን የዕለት ተግባር ቀለል እንዲልም በሚል የተቆረጠዉን አካል በሰው ሰራሽ አካል መተካት የተለመደ ነዉ።

በተለይም ከሞት በኋላ ላለዉ ህይወት የሰዉ ልጅ ከሙሉ አካል ጋር ሊሆን ይገባል ብለዉ ስለሚያምኑ የተቆረጠዉን አካል በግንዛት ወቅት ይተኩታል።

የወንድ ልጅ ግርዛት

Image copyright Getty Images

በታሪክ ዉስጥ ለዘመናት ግርዛት ይፈፀም የነበረዉ ከህከምና ፋይዳዉ እንዲሁም ከሀይማኖት ግልጋሎቱ ጋር ተያይዞ ነበር።

በጥንታዊ ግብፅም ይህ ልምድ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋ በመሆኑ ያልተገረዙ ወንዶች እንዳልተለመደ ወይም እንደ ነዉር ነበር የሚታዩት።

የተለያዩ መረጃዎችም እንደሚያሳዩት ጥንታዉያን ግብፆች በጦርነት ተሸንፈዉ የማረኩዋቸዉንም የሊብያ ዜግነት ያላቸዉን ወታደሮችም ለዘመድ አዝማዱ ብልታቸዉን ማሳየታቸዉም ከብልት ጋር የነበራቸዉን ከፍተኛ ቁርኝት ማሳያ ነዉ።

በመንግስት ቁጥጥር ዉስጥ ያለ የህክምና ሥርአት

Image copyright Getty Images

በጥንታውያን ግብፅ ለህዝቡ ህከምና እንዲዳረስ በበላይነት ሆኖ የሚቆጣጠረዉ መንግስት ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ በህክምና ዘርፍ ስርአተ-ትምህርት ተቀርፆ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ይደረጉባቸዉ የነበሩ ተቋሞችም ነበሯቸዉ።

እነዚህም ተቋሞች ከማስተማርም በተጨማሪ ህመምተኞችንም ያክሙ ነበር።

በህክምናዉ ዘርፍ እንዴት ልቀዉ እንደነበር ከሚያሳዩ መረጃዎችም መካከል 'ኢበርስ' የተባለዉ ፅሁፍ እንደሚያሳየዉ የተለያዩ በሽታዎችና መድሃኒቶቻቸዉ በዝርዝር ማስቀመጣቸዉ ህክምናን በተጠናከረና ስርአት ባለዉ መንገድ ይመሩ እንደነበር ያሳያል።

አለም በህክምና መጥቋል በሚባልበት በአሁኑ ሰአት እንኳን በብዙ አካባቢዎች ያልተለመዱ ተግባራት ይከናወኑ ነበር።

አንዳንዶቹን ለመጥቀስም ያህል በግንባታ አካባቢዎች አደጋዎች ቢደርሱ በፍጥነት የሚታከሙባቸዉ የህከምና ማዕከላት ተዘርግተዉ ነበር።

አደጋ የደረሰበት ሰራተኛም መስራት የማይችልበት ሁኔታ ከሆነ ደሞዝ እየተከፈላችዉ ያርፉ ነበር።