ተመራማሪዎች፡ ትዳር "ጤናን ይጠብቃል"

ትዳር ለጤና ይበጃል Image copyright Getty Images

ትዳር ለጤና እንደሚበጅ እና ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠንን የመሰለ ለከባድ የልብ ሕመም የሚያጋልጥ የጤና እክል በሚያጋጥም ወቅት ይህንን ተቋቁሞ የመዳን ዕድልን ከፍ እንደሚያደርግ ተመራማሪዎች ገልፀዋል።

የሚያፈቅሯቸው የትዳር አጋር ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን በሚገባ እንዲንከባከቡ ሊያበረታቱዋቸው እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

ተመራማሪዎቹ ውጤቱ ላይ የደረሱት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ በእንግሊዝ ነዋሪ የሆኑ አዋቂ ሰዎችን በማካተት በተሰራ ጥናት ላይ ተመርኩዘው ሲሆን የገለፁትም የልብ ጤና አጠባበቅ ማህበር ላይ በተደረገ ጉባኤ ነዉ ።

በጥናቱ የተካተቱት ሰዎች ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ኮሌስትሮል ወይንም የስኳር በሽታ ያለባቸው ናቸው።

የጥናቱም ውጤት እንደሚያሳየው በሽታን በመቋቋም ረገድ ባለትዳሮቹ ከላጤዎቹ የበለጠ ወውጤትን አሳይተዋል።

የትዳር በረከት?

ጥናቱን ያከናወኑት ዶክተር ፖል ካርተርና የአስተን ሜዲካል ትምህርት ቤት አጋሮቻቸው ከዚህ ቀደምም ትዳር ከልብ ህመም ለማገገም ጋር ከፍተኛ አስተዋፅኡ እንዳለው አሳይተው ነበር።

በብሪታንያ የልብ ጤና አጠባበቅ ማህበር ጉባኤ ላይ የቀረበው የቅርብ ጊዜው ምርምራቸውም ይህ ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ የሚጠቁም ነው።

ትዳር ኮሌስትሮል እና ከፍተኛ የደም ግፊትን የመሳሰሉ አደገኛ የልብ ሕመም አጋላጭ ሁኔታዎች እንደ መከላከያ እንደሚሆን መላ ምት አላቸው።

በተጨማሪ ጥናቱ የልብ ህመምን ጨምሮ በሁሉም መንስኤዎች ያጋጠሙ ሞቶችን አጢኗል።

14 ዓመት በፈጀው ጥናት መጠናቀቂያ ላይ በ50ዎቹ፣ በ60ዎቹ እና በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ባለትዳሮች በህይወት የመቆየት ዕድላቸው ላጤ ከሆኑት በ16 በመቶ ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህ እውነታ ለስኳር በሽታ እና ለከፍተኛ የደም ግፊትም የሚሰራ ሲሆን ባለትዳሮችም በከፍተኛ ፍጥነት ማገገምን አሳይተዋል።

ከትዳር ውጪ አብረው የሚኖሩ፣ የተለያዩ፣ የደተፋቱ ወይንም የትዳር አጋራቸውን በሞት ወዳጡ ሰዎች ሲመጣ ግን ቁልጭ ያለ ምስልን ማግኘት ጥናቱ አዳግቶታል።

ከዚህ በተጨማሪም ጥናት አድራጊዎቹ ባለትዳሮቹ በደስተኛ ትዳር መገኘት ያለመገኘታቸውን ጉዳይ ከግምት ውስጥ አላስገቡም።

የጥናቱ ማጠቃለያ ግን ማግባትን እንደ ግዴታ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ አጋር መኖሩ በጤና ላይ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ነው።

"ምክንያቶቹ ላይ የበለጠ ጥናት ቢያስፈልገውም ባለትዳርነት ከልብ በሽታ ህመምም ሆነ ለልብ ሕመም ሊያጋልጡ ከሚችሉ ጉዳዮች እንደሚጠብቅ ጥናቱ ያሳያል።" በማለት ዶክተር ካርተር የሚያስረዱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም

"ሁሉም ሰው ትዳር መመስረት አለበት እያልን ግን አይደለም፤ የትዳርን አዎንታዊ ፋይዳዎችን ኮርጀን በጓደኞች፣ በቤተሰብ አባላት እና በማህበራዊ የድጋፍ መረቦችም ልንተገብረው ያስፈልገናል።"

የብሪታንያ የልብ ፋውንዴሽን ሃላፊው ዶክተር ማይክ ናፕተን በበኩላቸው "ከዚህ የምንወስደው መልዕክት ማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ከፍተኛ የደም ግፊትን ከመሳሰሉ በሽታዎች ጋር ትስስር እንዳላቸውና ለጤናችንም ሆነ ለደህንነታችን ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ነው" ብለዋል።

የልብ ሕመም አጋላጮች ናቸዉ ተብለው በተመራማሪዎቹ ከተጠቀሱት መካከል ማጨስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን፣ የስኳር በሽታ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ያለማድረግ፣ በቤተሰብ ውስጥ ያለ የልብ ሕመም ታሪክ ይገኙበታል።

"ባለትዳር ሆናችሁም አልሆናችሁ፣ ከልብ ሕመም አጋላጮች መካከል አንዱም ካለባችሁ፣ እነርሱን ለመቆጣጠር ወደምትወዷቸው ሰዎች ፊታችሁን ማዞርና ድጋፍ መሻት ትችላላችሁ" ሲሉም አክለዋል።