ቴሌፖርቴሽን: ዛሬ የፎቶን ቅንጣት ካጓጓዝን ነገ ሰው ልናጓጉዝ ይሆን?

ማንም ሄዶ ወደማያውቀው ልንጓዝ ይሆን? Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ማንም ሄዶ ወደማያውቀው ልንጓዝ ይሆን?

ቻይናዊ ሳይንቲስቶች አንድን መረጃ በብርሃን ቅንጣት (ፎቶን) ምድርን በ1400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትዞራት ሳተላይት ልከዋል።

ሂደቱን ''ቴሌፖርቴሽን'' ይሉታል - አንድን ቁስ አካል ወይንም ኃይል አካላዊ ግፊት ሳይደረግ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወርን የሚጠይቅ ፅንሠ-ሐሳብ ነው።

ብዙ ሰዎች ቴሌፖርቴሽን እጅግ አስደናቂና ከተሰጠን የተፈጥሮ ችሎታ ወጣ ያለ ክስተት እንደሆነ ነው የሚያስቡት። ከዚህ ቀደም በሳይንስ ልቦለዶች ተወስኖ የነበረው ይህ ኃሳብ ግን እውን ይሆን?

ጥናቱን በመከተል ሊሆን እንደሚቻል አያጠራጥርም። ይህ ማለት ግን ራሳችንን ወደ ቢሮ ወይንም ወደ ባህር ዳርቻ እንደ ብርሃን ጨረር በቅጽበት መላክ እንችላለን ማለት አይደለም።

እንደዚህ ካልሆነ እንዴት ይሆን የሚሠራው?

በቀላሉ ለማስረዳት ያህል ''ቴሌፖርቴሽን'' ማለት የአንድን ነገር መረጃ ማሰራጨት እንጂ ራሱን ቁስ አካሉን መላክ አይደለም።

ይህን ይበልጥ ለማስረዳት የፊዚክስ ጠበብቶች የፋክስ ማሽን የሚሰራበትን መንገድ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

ፋክስ ማሽን ወረቀቱ ላይ ያለዉን መረጃ ነዉ እንጂ ራሱን ወረቀቱን አይልክም።

ብዙዎች እንደሚያስቡት ቴሌፖርቴሽን ማለት በ "ስታር ትሬክ" ና በ"ስፔስ ናይንቲን ናይንቲ ናይን"ና በሌሎች መሰል ሳይንሳዊ ፊልሞች ውስጥ እንደሚታየው በቅፅበት አንድን ነገር ወይም ቁስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ የሚያስችል ችሎታ አይደለም።

ከዚህ ይልቅ በፊዚክስ ጠበብቶች ቋንቋ "ኳንተም ኢንታንግልመንት" ወይም ትስስር በመባል የሚታወቅ ዘዴ ላይ የተመረኮዘ ነው።

Image copyright AFP/Getty
አጭር የምስል መግለጫ ልዩ የፎቶን መቀበያ ያለው የቻይና ሳተላይት

ኳንተም ኢንታንግልመንት (ትስስር) ምንድን ነው?

ይህ ክስተት ሁለት ቅንጣቶች በአንድ አይነት ጊዜና ቦታ ላይ ያለ ምንም ልዩነት በሚፈጠሩበት ጊዜ የሚሆን ነው።

ቅንጣቶቹ ቢለያዩም ትስስራቸው አይቋረጥም።

ይህም ማለት ደግሞ አንዱ ፎቶ በአንድ ቦታ ላይ ሆኖ ቢቀየር በዛኛው ቦታ ላይም ያለውም ፎቶ በተመሳሳይ መልኩ ይቀየራል ማለት ነው።

እ.አ.አ ከ1990ዎቹ አንስቶ የብሪስተል ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ሳንዱ ፖፔስኩ በ''ኳንተም ትስስር'' ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል።

"ይህ ነገር ሲሰማ ብዙዎች "ስታር ትሬክ" ፊልም ላይ እንዳለዉ አይነት ክስተት ነበር የጠበቁት። በተቃራኒዉ ያልተገነዘቡት ነገር ግን ያንድን ሰው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ቅንጣቶችን ሳይሆን አንዲት ቅንጣትን ብቻ ማጓጓዝ መቻላችንን ነው፤ ለምሳሌ ተነጥላ ያለችን ፕላኔት ብናስብ ማጓጓዝ የሚኖርብን በቢሊዮን የሚቆጠሩ በጥንድ የተሳሰሩ ቅንጣቶችንና ሌሎችም አስፈላጊ መረጃዎችን ነው፤ ይህ ደግሞ ቀላል ባለመሆኑ ብዙም የሚያስደስት አይደለም" በማለት ያስረዳሉ።

Image copyright Science Photo Library
አጭር የምስል መግለጫ የኳንተም ኮምዩተር መሥመሮች የተሻለ የመረጃ ደህንነት አላቸው

ቅንጣት እንዴት ይጓዛል?

ቀደም ብለን እንደ ምሳሌ የወሰድናቸዉን ሁለት የተሳሰሩ ቅንጣቶችን ብንወስድና ሶስተኛ ቅንጣት ከአንደኛው ጋር እንዲገናኘ ብናደርግ ሁለተኛው ቅንጣት ለውጡን ከመንታው መቀበሉ አይቀርም።

ምንም ሳይጓደል መንታው ቅንጣት ስለ ሦስተኛው ቅንጣት መረጃ ይኖረዋል ማለት ነው።

ይህም ማለት ለውጡ በሶስተኛው ላይ ይንፀባረቃል።

አስደሳች ነው ችግር ምን ይሆን?

ረዥም ርቀት መጓዝ የሚችል የተሳሰሩ ቅንጣቶች መፍጠር በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም አንድን የፎቶ ቅንጣት ከ150 ኪ.ሜ በላይ ሳይጠፋ በፋይበር ኦፕቲክ መጓዝ አይችልም።ተመራማሪዎችም "ፎቶኖች"ከሳተላይት ጋር ትስስር ያላቸው ሲሆን በጠፈር ውስጥ የበለጠ ፍጥነት እንደሚኖራቸውና ረዥም ርቀት መጓዝ እንደሚችሉ ደርሰውበታል። ነገር ግን ከምድር ከባቢ አየር ለማለፍ እጅግ ይቸገራሉ፤ ምክንያቱም ቅንጣቶቹን ትንሹ የአየር ለውጥ አቅጣጫ ስለሚያስቀይራቸዉ ነው።

ቻይናዎቹ ታድያ ምን አገኙ?

በየሰከንዱ የተሳሰሩ 4000 በኳንተም የተሳሰሩ ጥንድ "ፎቶኖች" በላቦራቶሪያቸው ከፈጠሩ በሗላ አንዷን ፎቶን ሚኪዩስ ወደተሰኘች ሳተላይት ላኩ።

ይህም ሙከራ ተሳክቶላቸዋል።

" ይህ ሙከራ አስደሳች ነው፤ በንደዚህ አይነት ፍጥነትና እክል ሳይገጥመው ይሳካል ብየ አልጠበኩም። " በማለት ግኝቱን የመሩትን ቻይናዊው ፕሮፌሰር ፓን ጅላንዌይን ያስተማሩት ፕሮፌሰር አንቶን ዜሊንገር በደስታ ይናገራሉ።

ሰዎችን ማጓጓዝ ካልተቻለ ቴሌፖርቴሽን ለምን ያስደስታል?

በአሁኑ ወቅት የኳንተም መጓጓዝ ዋና አላማ የማይጠለፉ ግንኙነቶችን ለመዘርጋት መጥቀሙ ነው።

በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ በመመሥረት ጂናን በተባለቸው የቻይና ከተማ ላይ መገናኛ መስመሮችን መዘርጋት ጀምረዋል።ይህ ግኝት ለምሳሌ ሚስጥራዊ ለሆኑ ገንዘብ ነክ የሆኑ ወይንም የምርጫ መረጃዎችን ለመሰወር ይጠቅማል።

መስተካከል ያለባቸው መሰናክሎች ቢኖሩም ቀስ በቀስ ግን ለውጥ እንደሚመጣም እየተነገረ ነው።