ተመራማሪዎች በሞቃታማውና በአሲዳማው የአፋር ክፍል ህይወት ያለው ነገር አገኙ

ዳናክል ዲፕሬሽን

የፎቶው ባለመብት, Colbeck, Martyn

ባቢው በተለያዩ ቀለማት ቢያሸበርቅም የቢጫና የአረንጓዴ ቀለማት ተጽእኖ አለው። አየሩም በመርዛማው ክሎሪን ሰልፈር ጋዝ ተሞልቷል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው ዳናክል ዲፕሬሽን ከዓለማችን ሞቃታማ እና ለኑሮ ምቹ ካልሆኑ አካባቢዎች አንደኛው ነው። ሆኖም በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት በአካባቢው ህይወት ያላቸው ነገሮች እንደሚኖሩ አረጋግጧል።

ዳናክል ዲፕሬሽን አነስተኛ ጥናት ከተካሄደባቸው የዓለም አካባቢዎች አንዱ ነው። ከኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት በአፋር ክልል ከባህር ጠለል በታች በ100 ሜትር ላይ በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ይገኛል። አካባቢው ሶስት አህጉራትን በመክፈል አዲስ ምድር ይፈጥራል ተብሎ በሚገመተው በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ያልረጋ የመሬት አቀማማጥ ያለው ይህ አካባቢ እጅግ ደረቅ በመሆንም ይታወቃል። ብዙም ዝናብ የማያውቀው አካባቢው ሙቀቱ በአብዛኛው 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል። ሁሌም የሚፍለቀለቁ ሁለት እሳተ ገሞራዎች የሚገኙ ሲሆን አንደኛው ኤርታ-አሌ ነው። ኤርታ-አሌ አሲድ የቀላቀለ በመሆኑም ይታውቃል።

የባህሩ ጨዋማ ውሃ እሳተገሞራ ውስጥ ከሚገኘው ማዕድን ጋር ሲዋሃድ የተለያየ ቀለም ይፈጥራል። በአካባቢው ሰልፈርና ጨው ተዋህደው ደማቅ ቢጫ ቀለም ሲፈጥሩ መዳብና ጨው ውሃ ሰማያዊ ቀለም ይፈጥራሉ።

የዚህ አካባቢ እጅግ ሞቃታማ አየር አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ዕፅዋትና እንስሳት ብቻ እንዲኖሩ የሚፈቅድ ነው። ዳሎል ለኑሮ አመቺ ባይሆንም በቅርብ ርቀት 'ሃማዴላ' የሚባሉ ጊዜያዊ መኖሪያቸውን ቀልሰው የሚኖሩ ሰዎች አሉ።

የሎውስቶን ከሚባለው የአሜሪካው አካባቢ ጋር ቢቀራረብም ዳናክል በጣም ሞቃታማና ውሃው አሲድ የበዛበት ነው። የአካባቢው ውሃ የአሲድ መጠን ከፍተኛ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እአአ ከ2013 ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጥናት ለዳናክል ትኩረት አሰጥቶታል። ዩሮ ፕላኔት የሚባለው የምርምር ተቋማት ኅብረት ሳይንቲስቶች ከማርስ ጋር ተቀራራቢ ይሆናል የሚሏቸውን የዓለማችን ክፍሎችን እያጠኑ ይገኛሉ።

ከ2013 ጀምሮ በአካባቢው ጥናት ከሚያደርጉት ባለሙያዎች መካከል የጣሊያኑ ቦሎኛ ዩንቨርሲቲ ባልደረባ ባርባራ ካቫላዚ ትገኝበታለች። "ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ ነው። በምሳ ሰዓት እስከ 48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል። በአንድ ወቅት 55 ዲግሪ ሴንቲግሬድም ሆኖ ያውቃል" ብላለች።

ዳሎል አካባቢ ያለው ውሃ ሙቀት መጠን 100 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው። ሳይንቲስቶቹ ከመርዛማው ሰልፋይድ ጋዝም ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ንፋሱ ውስጥ ያለው የክሎሪን ብናኝ ደግሞ ሳንባቸው ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ ሁሌም የጋዝ ጭንብል ማጥለቅ ይጠበቅባቸዋል።

"የጨው ግግሩ በቀላሉ ሊሰበር ስለሚችል ለመራመድ ጥንቃቄ ይፈልጋል" ትላለች ካቫላዚ። "100 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚፈላ እና መርዛማ በሆነ ውሃ ውስጥ ከተወደቀ በኋላ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ህክምና ለማግኘት በቅርብ የሚገኘው ሆስፒታል መቀሌ በመሆኑ እዛ ለመድረስም ሰዓታትን ይፈጃል። በአካባቢው ስንቀሳቀስ ሁሌም የአካባቢውን ሰው ይዤ ነው። እነሱ የት መሄድ እንዳለብኝና የቱን መርገጥ እንዳለብኝ ይነግሩኛል" ትላለች።

ጥናቱ በ2013 ሲጀምር እንዴት በአካባቢው መስራት ይቻላል በሚለው ላይ ያተኮረ ነበር። "ማቀዝቀዣም ሆነ ሌላ ናሙናዎችን ለማቆየት የሚረዳ ኬሚካል ማምጣት ስለማይቻል እንዴት መስራት እንዳለብን በደንብ ማቀድ አስፈላጊ ነበር" ብላለች ካቫላዚ።

በ2016 ግን ባለሙያዎቹ በአካባቢው ህይወት ሊኖር ይችላል በሚል ተስፋ ናሙናዎችን መሰብሰብ፥ በአካባቢው የሚገኘውንም የውሃ ሙቀት እና መርዛማነት መጠን መለካት ጀመሩ። በድጋሚ ጥር 2017 ናሙናዎችን ወሰዱ። ከሶስት ወር በኋላ የነካቫላዚ ቤተሙከራ ከባክቴሪያ ላይ ዲ ኤን ኤ በመለየት በዳናክል ህይወት ያለው ነገር እንደሚኖር አረጋግጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተገኙት ፖሊኤክስትሬሞፊሊክ የሚባሉት ባክቴሪዎች አሲዳማ፣ ሞቃታማና ጨዋማ በሆነ አካባቢ መኖር የሚችሉ ናቸው። ይህም በዳናክል ህይወት እንደሚኖር የመጀመሪያው ማረጋገጫ ሆኗል።

እስካሁን ባልታተመው የምርምር ውጤት ሳይቲስቶቹ በሁለት አካባቢዎች ህይወት ያላቸው ሁለት ዓይነት ባክቴሪያዎችን አግኝተዋል። ይህም በቀለማት ባሸበረቀው የዳሎል አካባቢና በአቅራቢያው በሚገኘው አነስተኛ ሃይቅ ነው።

ሃይቁ እንደ ጨዋማው አካባቢው ውሃ ባይሞቅም ሙቀቱ እስከ 55 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል። ጨዋማ ቢሆንም አሲድነቱ ግን አነስተኛ ነው። ከሥሩ ባለው እሳተ ገሞራ የተነሳም ውሃው ከፍተኛ ካርቦንዳዮክሳይድ አለው።

"ሃይቁ በተለያዩ ስሞች ይጠራል። የአካባቢው ሰዎች 'ጋት-አሌ' ወይም 'አራት' ይሉታል። ሌሎች ደግሞ 'ዘይታማው' ወይም 'ቢጫው' ሃይቅ ሲሉ ይጠሩታል። በአካባቢው አነስተኛ ነፍሳትና ወፎች ሞተው ስለሚገኙ ሌሎች ደግሞ 'ገዳዩ' ሃይቅ ይሉታል። ነፍሳቶቹና ወፎቹ ወደ ውሃው ቀርበው ሊጠጡ ሲሉ በከፍተኛው ካርቦንዳዮክሳይድ ምክንያት የሞቱ ናቸው" ትላለች ካቫላዚ።

ካርቦንዳዮክሳይድ ከመደበኛው አየር ስለሚከብድ ወደ መሬት ይገባል። በዚህም አነስተኛ ፍጥረቶች ይህን አየር ሲስቡ ይበከላሉ። ረዘም ለሚሉ ሰዎች ይህ አደገኛ አይደለም። ሆኖም ከሃይቁ እስከ 30 ሴንቲሜትር ብቻ ርቆ ለሚተነፍስ ህይወት ያለው ነገር ብዙ ካርቦንዳዮክሳይድ በመሳብ ለሞት ይዳርጋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንዱ የተመራማሪዎቹ ስራ አዲስ ክብረ ወሰን ለመስበር ከጫፍ ደርሷል። ቡድኑ የመርዛማነት መጠኑ ፒ ኤች ዜሮ በሆነ ቦታ ላይ ህይወት አግኝቷል። (ፒ ኤች የመርዛማነት መጠን መለኪያ ሲሆን መጠኑ ወደ ዜሮ በተጠጋ ቁጠር መርዛማነቱ እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። ሰባት ሲሆን ግን መርዛማ አይደለም ማለት ነው።) አካባቢው በከፍተኛ መጠን መርዛማ ሆኖ ህይወት የተገኘበት ነው። ከዚህ ቀደም ክብረ ወሰን የያዘው በስፔን ሪዮ ቲንቶ የተገኘውና በፒ ኤች 2 መርዛመነት መጠን የተገኘው ህይወት ነው።

"ማርስ ላይ ከዳናክል ጋር ተመሳሳይ የሆነ የሰልፌትና የማዕድኖች ክምችት ሊኖር ይችላል። ተመሳሳይ ጨዋማ ውሃም ሊኖር ይችላል" ስትል ካቫላዚ ትገልጻለች። ስለዚህ በዳናክል ህይወት እንደሚቀጥልና እንዴት መቀጠል እንደተቻለ በማጥናት የትኛው የማርስ ክፍል ለመኖር አመቺ እንደሚሆን ይጠናል።