ሰዓትን በትክክል የመቁጠር ጠቀሜታ

ሰከንዶች ይቆጠራሉ Image copyright Getty Images

ከጥንት ጀምሮስለዜ ያለን ግንዛቤ በፕላኔቶች እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘ ነው። ምድር ፀሐይን እንደምትዞር ከማወቃችን በፊት ስለቀናትና ዓመታት እናወራ ነበር።

የጨረቃ ድምቀት መጨመርና መቀነስን እየተመለከትንም የወራትን እሳቤ ለየን። ምንም እንኳን የፀሐይን እንቅስቃሴ ለመረዳት ባለንበት ቦታ የሚወሰን ቢሆንም፤ ፀሐይ ሰማይን አቋርጣ ስትጓዝ እኩለ ቀንንና አመሻሽን መገንዘብ ግን እንችላለን።

በተለምዶ ሰዎች በብዛት ሰዓታቸውን የሚያስተካክሉት በሚኖሩበት አካባቢ ሰማይ ላይ በሚታዩ ምልክቶች ላይ በመመርኮዝ ነው። ይህንንም በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ እንዲሆን ለማድረግ ከቻሉ ብዙም ችግር አይፈጥርም ነበር። ነገር ግን ሁለት ሰዎች በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ ሆነው ሰዓት ቢመለከቱ የተለያየ ስለሚሆን ትክክለኛው ሰዓት ይህ ነው ለማለት ያስቸግራል።

ይህንን የሰዓት መለያየት ለማስቀረት የአንዳንድ ከተሞች ባለሥልጣናት በሃገር ደረጃ የሚያገለግል ተመሳሳይ የሰዓት አቆጣጠር ቢኖር ጥቅሙ የጎላ እንደሚሆን ተገነዘቡ። ሌሎች ግን በሃሳቡ ደስተኛ አልነበሩም።

በእርግጥም 'ትክክለኛ' የሚባል የሰዓት አቆጣጠር የለም። ለዚህም ነው ልክ ለገንዘብ እንደሚሰጠው ተመን ጥቅሙ በብዙሃኑ ዘንድ ባለው ተቀባይነት ላይ የተመሠረተ የሚሆነው።

ያጋጠመ ችግር

ቀደም ባለው ዘመን ሰዓትን በተመለከተ ትክክል የሚባል የአቆጣጠር ዘዴ ግን ነበረ። ይህም የሰዓት አቆጣጠር ከ1656 (እ.አ.አ) ጀምሮ የነበረ ሲሆን የዳች ዜጋ በሆነው በክርስቲያን ሃይገንዝ ነው የተተዋወቀው።

ከጥንት ግብፃውያን ጊዜ አንስቶ እስከ መካከለኛው የፋርሶች ዘመን ድረስ ውሃን በመጠቀም ሰዓት ይቆጠር ነበረ። ሌሎች ደግሞ ሻማ ላይ በሚፈጠሩት ምልክቶች አማካይነት ጊዜን ይለያሉ። ሆኖም ግን እጅግ የላቀ የተባለለት የሰዓት አቆጣጠርም ቢሆን እኳን በቀን የ15 ደቂቃዎች ልዩነት ሊያሳይ ቢችልም፤ የፀሎት ሰዓትን ለማወቅ ለፈልጉ መነኮሳት ግን ይህ ብዙም ለውጥ አያመጣም።

ነገር ግን ሰዓትን በትክክል ለመቁጠር አለመቻል እጅግ ጠቃሚ በሆነው የባህር ጉዞ ላይ ግዙፍ የሆነ ኢኮኖሚያዊ አድምታ አለው።

Image copyright Getty Images

መርከበኞች የፀሐይን መዓዘን በመመልከት ከሰሜን ወደ ደቡብ የትኛው ስፍራ ላይ እንደሚገኙ ያሉበትን አቅጣጫ ያሰሉ ነበር። ነገር ግን ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ያሉበትን ሥፍራ ለመለየት ከግምት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም።

ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ ለስህተት ክፍት የነበረ ሲሆን፤ መርከበኞቹ ሳያውቁ መድረስ ከነበረባቸው ቦታ በሺህ በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በመጓዝ ከመሬት አካል ጋር እስከመጋጨት ድረስ ችግር ይገጥማቸው ነበር።

ታድያ ሰዓትን በትክክል መቁጠሩ እንዴት ይረዳ ይሆን? ከግሪንዊች የሰዓት መከታተያ ወይንም ከማንኛዉም ሌላ ቦታ ላይ እኩለ ቀን መሆኑ ከታወቀ፤ የፀሐይን አቀማመጥን ተመልክቶ የጊዜ ልዩነትን በማስላት ርቀትን ለማወቅ ይቻላል።

Image copyright Alamy

የሃይግንዝ የፔንዱለም ሰዓት ቀድመው በጊዜው ከነበሩት የሰዓት መቁጠሪያዎች አንፃር ከ60 ጊዜ ያህል በላቀ ሁኔታ ትክክለኛ የነበረ ሲሆን፤ በየዕለቱ የሚገጥመው የ15 ሰከንዶች ልዩነት ግን ሲደማመር ትልቅ ልዩነት ያስከትላል። ፔንዱለሞች ደግሞ በማዕበል በሚናጡ መርከቦች ላይ በአግባቡ መወዛወዝ አይችሉም ነበር።

የባህር ግዛቶችን የሚያስተዳድሩ መንግሥታትም በሰዓት አቆጣጠር በኩል ያለውን ጉድለት ተረድተውት ነበረ። ለዚህም የስፔን ንጉስ ሃይግንዝ ሥራውን ከማቅረቡ አንድ ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ ለሚያቀርብ ሰው ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብቶ ነበር። ከዚህም በኋላ የብሪታኒያ መንግሥት ያቀረበውን ሽልማት ተከትሎ በ 1700 (እአአ) በእንግሊዛዊው ጆን ሃሪሰን የተሰራውና በቀን የጥቂት ሰከንዶችን ልዩነት ያለው መቁጠሪያ ዕውን ሆነ።

ይህ የዓለማችንን የሰዓት ቀጠናዎችን የሚያስታርቀው ትክክለኛው የሰዓት አቆጣጠር መላውን ዓለም አስማማ። ይህም ሁሉን አቀፍ የሰዓት አቆጣጠር ዩቲሲ (UTC) በመባል ይታወቅ ጀመር።

በአብዛኛው የተለያዩ የሰዓት አቆጣጠር አይነቶች እኩለ ቀን የሚሆነው ፀሐይ አናት ላይ ስትሆን ነው በሚል ሐሳብ ይስማማሉ። ነገር ግን ሁልጊዜ እንደዛ ላይሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል።

ለምሳሌ ሊቀመንበር ማኦ ቻይናን በአምስት የሰዓት ቀጠናዎች የሚከፍለውን የጊዜ አቆጣጠር አስቀርተው የቤይጂንግ ሰዓት በመላ ሃገሪቱ እንዲሰራ ሲወስኑ በምዕራባዊ የቻይና ግዛት ፀሐይ ስትወጣ ሰዓቱ ግን እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ያመለክታል።

ሰከንድ ሽርፍራፊዎች ለምን ይጠቅሙ ይሆን?

የሃይግንዝና ሃሪስን ሥራ ተከትሎ ሰዓቶች ይበልጥ ትክክለኛ ጊዜን እያመለከቱ መጥተዋል። ሁሉን አቀፍ የሰዓት አቆጣጠር (ዩቲሲ) የአቶሚክ ሰዓቶችን ተጠቅሞ ኤሌክትሮኖች ውስጥ ያለውን የኃይል መጠን ስለሚመዘግብ በመቶ ሺህ ዓመታት ውስጥ ሰዓቱ በሰከንድ ሽርፍራፊዎች ውስጥ ሳይቀር መዘባት አይገጥመውም።

እንዲህ አይነቱ ትክክለኛ የሰዓት አቆጣጠር አስፈላጊ ነውን? የዕለት ተለት ሥራዎቻችንን የሰከንድ ሽርፍራፊዎቸን ግምት ውስጥ በማስገባት አናቅድም፤ እንዲያውም ብዙውን ሰዎች የእጅ ሰዓቶችን የሚያደርጉት ከሚሰጡት ጊዜን የመቁጠር አገልግሎት ይልቅ ከክብር ጋር ለተያያዘ ትርጉም ነው።

ይህ ዕውነት ቢሆንም እንኳን የሰከንድ ሽርፍራፊዎቸ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ የሉም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም የሩጫ ውድድሮች ላይ አሸናፊ ሊኖር የሚችለው አንድ ብቻ ሲሆን እሱም ደግሞ በአንድ በሽራፊ ሰከንድ ልዩነት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት አያስፈልግም።

Image copyright Getty Images

ትክክለኛና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የሰዓት አቆጣጠር ለኮምፕዩተርና ለሌሎች የግንኙነት መገልገያዎች መዘርጋት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። የአቶሚክ ሰዓት አቆጣጠር እንደቀደመው ዘመን ሁሉ ለባህር ላይና ለባቡር ጉዞዎች የበለጠ አስተዋጽዎ አበርክቷል። ባለንበት ዘመን የፀሐይን ማዕዘን እየተመለከቱ መጓዝ ቀርቷል፤ ምክንያቱም ጂፒኤስ (አቅጣጫ ጠቋሚ) ቴክኖሎጂ በመስፋፋቱ።

እንዲያውም ዘመናዊ የሞባይል ስልኮች ሳይቀሩ ባላቸው የኔትወርክ ትስስር ሳተላይቶችን ተጠቅመው በምድር ላይ የት ቦታ ላይ እንዳለን በቀላሉ እንድናውቅ ያግዙናል።

ይህ ቴክኖሎጂ ከአየር እስከ ባህር ጉዞና በተራራማ ስፍራዎች ጭምር አገልግሎት በመስጠት ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ነገር ግን ይህ የሚሠራው ሳተላይቶቹ በሚጠቀሙት ሰዓት ላይ የሚስማሙ ከሆነ ብቻ ነው።

አሁንም ድረስ የሰዓት አቆጣጠር እድገትና መሻሻልን ከማስተናገድ አልተገታም።

በቅርቡም ሳይንቲስቶች ይተርቢየም የተሰኘ ንጥረ ነገር በመጠቀም አዲስ የሰዓት መቁጠሪያ ሰርተዋል። ይህ ሰዓት በትክክለኝነቱ ወደር የለሽ የሚባል ነው። ምክነያቱም በአምስት ቢሊዮን ዓመታት ውስጥ የሰከንድ አንድ መቶኛ የማይሞላ መዘግየት ብቻ ስለሚገጥመው ነው።

ይህ እጅግ በጣም አስተማማኝ የሰዓት አቆጣጠር በቀደመውና በአሁኑ ዘመን መካከል ምን አይነት ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ያመጣ ይሆን? ሰዓቱ ሲደርስ የምናየው ይሆናል።

ተያያዥ ርዕሶች