ታሪክ ብዙም እውቅና ያልሰጠው የዓለማችን ቱጃር

ጄኮብ ፉገር Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ "ጄኮብ ፉገር በታሪክ ከታዩ ሁሉ በጣም ጠንካራው የባንክ ባለቤት ነው"

በግሪጎሪሳውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1459-1525 ዓመተ ምህረት የኖረው ጄኮብ ፉገር ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ቢል ጌትስ፥ ዋረን ቡፌት እንዲሁም ማርክ ዙከርብረግ አንድ ላይ ተደምሮ ከሚኖራቸው በላይ ሀብት ይኖረው ነበር።

የፉገር የሕይወት ታሪክ ጸኃፊ የሆነው ግሬግ ስቴይንሜትዝ እንደሚናገረው በቅጽል ስሙ 'ሀብታሙ ሰው' በመባል የሚታወቀው ጀርመናዊው የባንክ ባለቤት እና ነጋዴ ፉገር በሕይወት በነበረበት ወቅት በዚህ ዘመን የአራት መቶ ቢሊዮን ዶላር ሊጠጋ የሚችል ሀብት አካብቶ ነበር።

የቀድሞው የዋል ስትሪት ጋዜጣ አርታኢ እና ታሪክ ጸሃፊው ስቴይንሜትዝ እንደሚገልጸው ጄኮብ ፉገር በዓለም ታሪክ ከታዩ ባለጸጋዎች ቁጥር አንድ መሆኑን ነው። ስቴይንሜትዝ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የፉገርን የሕይወት ታሪክ "የዓለማችን ቱጃሩ ሰው "በሚል ርዕስ በመጽሃፍ ጠርዞ ለአንባቢያን አብቅቷል።

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገው ታሪክ ጸሃፊው ስቴይንሜትዝ ሀብትን እና ጊዜ እያነጻጸሩ ትችት ለሚሰነዝሩበት ሰዎች ምላሽ ሲሰጥ ሌላው ቢቀር በአንድ ነገር በጣም እርግጠኛ እንደሆነ ይናገራል።

"ጄኮብ ፉገር በታሪክ ከታዩ ሁሉ በጣም ጠንካራው የባንክ ባለሙያ ነው" በማለት ይናገራል

ሀሳቡን ሲያስረግጥም በኣውሮፓውያን የሕዳሴ ዘመን ጠንካራ ለነበሩት የሮም ገ እንዲሁም የካቶሊክ ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስን ገንዘብ ይሰጥ እንደነበረ ይመሰክራል።

እንደ ታሪክ ጸኃፊውም አባባል ማንም የባንክ ሰው በዓለም ፖሊቲካዊ ሚዛን ላይ የፉገርን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ አያውቅም።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፉገር በሕይወት በነበረበት ወቅት ወደ አራት መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት አካብቶ ነበር

የፉር አለመታወቅ ጉዳይ

በሱ ዘመን የነበሩትን እነ ሜዲሲ፥ ቄሳር፥ እንዲሁም የሉክሬዚያ ወንድማማቾችን እና ማኪያቬሊን ታሪክ ሲዘክራቸው እንዴት ይህን ሰው ታሪክ ሳያውቀው ቀረ? ትንታኔ የሚያሻው ጉዳይ ነው።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ስቴይንሜትዝ የፉገር ጀርመናዊ መሆን እና በእንግሊዝኛ ተናጋሪው ማህብረሰብ አለመታወቅ ትልቁን ሚና ይጫወታል ይላል። ይህም እውነት ስቴይንሜትዝን ስለ ጄኮብ ፉገር ብዙ እንዲጠይቅ እንዳደረገው ይናገራል።

"የዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ የጀርመን ቢሮ ኃላፊ በነበርኩበት ወቅት ነው ስለ ፉገር ጥቂት መስማት የጀመርኩት፤ ነገር ግን ስለሱ በእንግሊዛኛ የተጻፈ ነገር ማግኘት አልቻልኩም።" ይላል ስቴይንሜትዝ።

ሌላኛው ፉገር በዓለም ያለመታወቅ ምክንያት ሰውየው ያን ያህል የጎላ ገፀባህርይ ወይም ህይወት ስላልነረው ሊሆን ይችላል ሲል ያክላል ።

"ሊቀ ጳጳስ ለመሆን ወይም የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ አልሞከረም፤ ከየትኛውም የህዳሴ ዘመን አርቲስት ጋር ግንኙነት አልነበረውም፥ ቤተ-መንግስት ወይም ካቴድራል አልገነባም " ይላል ታሪክ ጸኃፊው ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፉገር የተሰኘው በጀርመን ኦግዝበርግ የሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤት

ከፉገር ስራዎች ውስጥ ትልቅ እውቅና ያስገኘለት በስሙ የሚጠራውና በጀርመን ኦግዝበርግ የሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ሲሆን በነዚህ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች በዓመት የሚከፍሉት አንድ ዶላር ብቻ መሆኑ ሌላው ቦታውን ታዋቂ ያደረገው እውነታ ነው።

ፉገር ከካፒታሊዝም ስርዓት ፈጣሪዎች አንዱ እንደሆነም ይነገርለታል፤ ዘመናዊው የቁጠባ ስርዓት እንዲስፋፋም ከፍተኛ ሚናም ተወጥቷል።

ተያያዥ ርዕሶች