''ለብዙ ሰዎች ቦክስ ድብድብ ነው ፤ ለእኔ ግን ሳይንስ ነው''

መስከረም ስታሰለጥን
የምስሉ መግለጫ,

መስከረም ሴት ቦክሰኞችን በሳምንት ለሶስት ቀናት ታሰለጥናለች

በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ ተወልዳ ያደገችው መስከረም ጩሩ ገና በልጅነቷ ኑሮን ለማሸነፍ ብዙ ታግላለች፤ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ለእርሷ እንደክፍል ጓደኞቿ የመጫወቻ ጊዜ አልነበራትም ።

ከትምህርት ቤት ስትመለስ እዛው በአካባቢዋ መንገድ ዳር ሊስትሮ ሆና ትሰራ ነበር። መሸትሸት ሲል ደግሞ ቤቷ ገብታ ሽመና የሚሰሩትን አባቷን በድውር ታግዛለች።

አሁን መስከረም 26 ዓመቷ ነው፤ ዛሬም ቢሆን በትግል ውስጥ ናት ፤ ውድድሯ ግን ከኑሮ ጋር ብቻ ሳይሆን እሷ ሳይንስ ነው ከምትለው ቦክስ ጋር ነው።

በእንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነበር ወንድ ተማሪዎች ቦክሰ ሲለማመዱ አይታ ምን እያደረጉ እንዳሉ ብዙ ባይገባትም ቀረብ ብላ መላላክ የጀመረቸው።

''ያኔ ስለስፖርቱ ምንም አላውቅም ነበር፤ በኋላ ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ውድድር ወደሚደረግበት ስታዲየም ይዘውኝ ሲሄዱ በቃ ልቤ እዛው ቀረ፤ በጣም ወደድኩት ፤ እኔም መሰልጠን እንዳለብኝ ወሰንኩና ከ 20 ወንዶች ብቸኛዋ ሴት ሆኜ ተቀላቀልኳቸው'' ትላለች መስከረም።

ወንዶቹም ብዙም ስላልተለመደ በውሳኔዋ ቢገረሙም በደስታ ተቀብለው የቡድናቸው አባል አደረጓት፤ ውጤታማ ለመሆንም ቢሆን ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም፤ በየጊዜው ባለድል መሆኗን ተያያዘችው።

መስከረም ለተከታታይ አስር ዓመታትም ሻምፒዮን ሆናለች። ያኔ ሀገርን ወክሎ የመወዳደሩ እድል ብዙም አልነበረምና ነገን ተስፋ በማድረግ ገና ቦክስን የሚቀላቀሉ ልጆችን ማገዝ እንዳለባት ወስና ለዚህ የሚያበቃትን ዓለማቀፍ ስልጠና በመውሰድ ፊቷን ወደአሰልጣኝነት አዞረች።

ታዲያ እርሷ በውሳኔዋ እርግጠኛ ብትሆንም ስለስፖርቱ ያውም ስለሴቶች ቦክስ የብዙ ሰዎች አመለካከት ጥሩ አልነበረምና አረ ተይ የሚላት ብዙ ነበር።

'' ለብዙ ሰዎች ቦክስ ማለት ድብድብ ነው፤ ለእኔ ግን ሳይንስም ጥበብም ነው፤ ቴክኒኩንና ታክቲኩን ለማወቅ በጣም ድካም አለው፤ በትክክል ለመረዳትም ብዙ የመማሪያ ጊዜ ያስፈልጋል'' ባይ ናት መስከረም።

ይህ የሌሎች ኃሳብ ሰልጣኞችም ጋር ሊኖር እንደሚችል በመገመት ሁልጊዜም የሚቀላቀሏትን ልጆች በመጀመሪያ ቦክስን እንደጥበብ እንዲቀበሉና የስነልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ታስተምራቸዋለች።

የምስሉ መግለጫ,

ከመስከረም ሰልጣኞች ብዙዎቹ ሴቶች ናቸው

ከዚህ በኋላም ቢሆን በቀጥታ ወደስንዘራ አይገቡም ፤ ለቦክሱ የሚያስፈልገውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይሰራሉ።

ሰውነታቸው በስፖርት መዳበሩን ወይም መጠንከሩን ካረጋገጠች በኋላ መሰረታዊ የቦክስ አቋቋምና የእጅ እንቅስቃሴዎች ስልጠና ይቀጥላል።

ይህን ሲጨርሱ ደግሞ የቦክስ አሰነዛዘር ቴክኒክ ፣ታክቲክና ትንፋሽ አወሳሰድ ተምረው አቅማቸው ሲያድግ በፕሮጀክት ውስጥ መወዳደር ይጀምራሉ ።

ከፍ ሲሉ ደግሞ የውድድር ሂደቶችን ተከትለው እስከሃገር አቀፍ ውድድሮች ድረስ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ።

መስከረም 30 የሚሆኑ ወንድና ሴት ቦክሰኞችን በሳምንት ለሶስት ቀናት በዚህ ሂደት መሰረት ታሰለጥናለች ።

ከሰልጣኞችም አራት ሴቶች በአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ ሲታቀፉ የኒያላና ማረሚያ ቤቶችን የቦክስ ክለቦች የተቀላቀሉ ወንዶችም አሉ።

በኦሎምፒክ ወደማሳተፍ ህልሟ የተጠጉላትን ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ቦክሰኛም ለብሄራዊ ቡድን አስመርጣለች።

ሴት ቦክሰኞች ብዙም ባልተለመደባት ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ጉለሌና ኮልፌ አካባቢ ብዙ ሴቶች እነመስከረምን እያዩ ቤተሰቦቻቸውን እንድታግባባላቸው ይለምኗታል ። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች እርሷንም በኃሳብ ወደ ኋላ ይመልሷታል።

''የኔ ቤተሰቦችም ገና ስጀምር አካባቢ በጣም ተቃውመውኝ ነበር። በኋላ ግን በኔ ተገርመው ሳይጨርሱ ሁለት እህቶቼም ቦክሰⶉች ሲሆኑ ሃሳባቸውን ከማንሳት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም'' ትላለች።

መስከረም በሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው የወጣቶች ማሰልጠኛ ውስጥ በአንድ ጊዜ እስከ 50 የሚደርሱ ወጣቶችን በፕሮጀክት ስታሰለጥን የምታገኘው ገቢ ለሳሙና በሚል በወር የሚከፈላትን 1000 ብር ብቻ ነው።

ቤተሰቧንም ለመደጎም ይሕ ገንዘብ በቂ አይደለምና ከዚህ ሁሉ ልፋት በኋላም ቤቷ ደግሞ ሌላ አድካሚ ስራ ይጠብቃታል።

በሽመና ስራ ባህላዊ አልባሳትን እያመረተች ለገበያ ታቀርባለች፤ ግን ሁለቱን ማወዳደር አይታሰብም ትላለች ።

''የምሰራው ለገንዘብ ቢሆን ቦክሱን ድሮ ነበር የምተወው ፤ ግን ብሞክርም አይሆንልኝም፤ ምክንያቱም ያለቦክስ መኖር አልችልም'' በማለት ትናገራለች።

የምስሉ መግለጫ,

የ18 ዓመቷ ገነት በ54 ኪሎ ግራም የቀላል ሚዛን ተወዳዳሪ ናት

ገነት ጸጋዬ ሴቶች የሚበዙበትን የመስከረም የቦክስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ከተቀላቀለች ሶስት ዓመት ሆኗታል።

አብሮ አደጎቿ የሚያውቋት 'ወንደወሰን' በሚለው ቅጽል ስሟ ነው፤ ልጅ እያለች ጸጉሯ መቆረጡን እግርኳስንም ማዘውተሯን የተመለከተ ጎረቤቷ ነበር ይህን ስያሜ የሰጣት።

ገና የ15 ዓመት ልጅ እያለች እንደወትሮ ሁሉ በአካባቢዋ ስትጫወት ያየ አንድ ሰው ለምን ቦክስ አትሞክሪም? ብሎ መስከረም ወደምታሰለጥንበት ቦታ ይዟት መጣ።

ያኔ ገነት ቦክስ ምን እንደሆነ እንኳን አታውቀውም ነበር፤ ሆኖም ገና በ 15 ዓመቷ ከፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ማሊያ ሲሰጣት የልጅነት ሞቅታ ተሰማት፤ ቦክሱንም ትምህርቷንም ጎን ለጎን ማሰኬድ ፈለገች።

''መስከረም ስታሰራ አቋሟ ይመቸኛል፤ በጣም ትስበኛለች'' የምትለው ገነት ቀሰ በቀስ እርሷም ከቦክስ ጋር ተወዳጀች ። ጠዋትና ማታ ቢያንስ ለአራት ሰዓታት በትጋት መሰልጠን ጀመረች።

ከአንድ ዓመት በኋላ ስትፈልገው የነበረውን እድል አገኘች፤መስከረም ጋር ስትለሰለጥን አቋሟን ያዩ አስልጣኞች በክለብ ከታቀፉ ቦክሰⶉች ጋር እንድትወዳደር ጠየቋት።

''ያኔ ብዙ አቅም እንዳለኝ የተሻለም መስራት እንደምችል አውቅኩ፤ ምክንያቱም ከብዙዎቹ የተሻልኩ ነበርኩኝ'' ትላለች።

በ2008 በአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ ታቅፋለች ፤ ትጥቆች ጓንቶችና የ 3000 ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ታጘኛለች። የወደፊት ህልሟ ደግሞ በብሄራዊ ቡድን ሃገሯን ወክሎ መወዳደር ነው።

በክለብ ብትትቃፍም አሁንም መሰከረም ጋር መሰልጠኗን አላቋረጠችም። በሳምንት ለሶስት ቀናት ትሰለጥናለች፤ ከእርሷ ያነሱትን በማሰልጠንም ታግዛለች ።

''ለቦክሰኛ አመጋገቡ አቋሙንም ክብደቱንም በጣም ይወስነዋል ፤እኔ ኪሎዬ ጥሩ ከሆነ እንዳይጨምርም እንዳይቀንስም ፓስታ እበላለሁ፤ ኪሎዬ ከቀነሰ ግን በቃ ያገኘሁትን ሁሉ ነው የምበላው ፤ይሄኔ ካሽካ የሚባለውን በበቆሎ የሚሰራ የዶርዜ ባህላዊ ምግብ እመርጣለሁ"ትላለች ገነት።

ገነት በራሷ ትጋት እዚህ ደረሰች እንጂ ቤተሰቦቿ ቦክሰኛ የመሆን ሃሷቧን እንድትቀይር ስልጠናውንም እንድታቆም ጫና ያደርጉባት ነበር።

'' በተለይ ደግሞ አባቴ የሆነ ጊዜ ላይ ጫወታውን ሊያይ መጥቶ በውድድሩ ላይ ስደባደብ ሲያየኝ ሆዱ ባብቶ አረ ተይ ይለኝ ነበር ግን የኋላ ኃላ ሳሸንፍ ሜዳሊያም ሳመጣ ግፊቱ እየቀነሰ መጣ" ሴት ቦክሰኞችን ለመቀበል ሌሎች ሰዎችም ይቸገራሉ ትላለች ገነት።

'' ብዙዎች ለሴቶች ቦክስ ምን ያደርጋል እያሉ ያንቋሽሹናል ፤እኔ ደግሞ ለምን እንዲህ ትላላችሁ ከወንዶቹ በምን እንለያለን እላቸዋለሁ?'' በማለት ትጠይቃለች።

ከንግግርም አልፎ እሷንም ሆኑ ሴት ጓደኞቿን የሚፈታተናቸው ወንድ አልጠፋም ፤ያኔ ስፖርቱም እንደሚጠይቀው ትዕግስትን መላበስ ግድ ይላታል ፤ ግን ይሄ ሁልጊዜ በቂ ላይሆን ይችላል።

''አንድ ቀን አንዱ ጎረምሳ ጓደኛዬን ተተናኮላት፤ አረ ተው ብንለው እምቢ አለ፤ እኔም እባክህን በናትህ ተዋት እያልኩ ልመና ገባሁ፤ ቢሳደብ ቢቆጣ ዝም አልኩት፤ ድንገት መጥቶ በጥፊ ሲመታኝ ግን ትእግስቴ አልቆ አንድ ጊዜ አቀመስኩት፤ ከውድድር ውጪ ለቦክስ እጄን ዘረጋሁት ያን ጊዜ ብቻ ነው'' በማለት ትናገራለች።