ያለሙዚቃም ውዝዋዜ አለ- መስማት የተሳናቸው ተወዛዋዦች ቡድን በአዲስ አበባ

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
መስማት የተሳናቸው ተወዛዋዦች ቡድን

ሙዚቃና ውዝዋዜን ነጣጥሎ ማሰብ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ለብዙዎች የዳንሱን እንቅስቃሴ የሚወስነው ሙዚቃው ነው።

እርሶስ ከሚሰሙት ሙዚቃ ጋር በጥቂቱም ቢሆን እየተወዛወዙ ሳለ ድንገት ሙዚቃው ቢቆም ዳንሱን ይቀጥላሉ?

መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ግን ሙዚቃው በራሱ ትርጉም አልባ ነው፤ ስለማይሰሙት ምንም ስሜት አይፈጥርባቸውም ። ይልቅስ ውዝዋዜያቸውን የሚወስነው የሙዚቃው ምት ነው።

አጭር የምስል መግለጫ እነዚህ መስማት የተሳናቸው ተወዛዋዞች ያለሙዚቃም እንዳሻቸው መወዛወዝ ይችላሉ

የሙዚቃውን ምት እንዴት ይረዱታል ?

በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ የሚገኘው መስማት የተሳናቸው የውዝዋዜና የቲያትር ቡድን አባላት እንደሚሉት የሙዚቃውን ምት የሚረዱበት ሁለት መንገድ አላቸው።

ለውዝዋዜ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን የሚያደርጉትን ትከሻ ቆጠራን ነው፤ ይህ ሂደት ትካሻቸውን እያወዛወዙ አንድ ሁለት ሶስት እያሉ የትከሻ ምት የሚቆጥሩበት ነው ።

ይሕ መስማት የሚችሉት ተወዛዋዦችም የሚጠቀሙበት ሂደት ቢሆንም ለእነርሱ የውዝዋዜ መነሻ ሲሆን እነርሱ ግን በመድረክ ሲጫወቱም የሚጠቀሙበት ስልት ነው።

አንድ ምት ሁለት ምት ሶስት ወይም ከዚያ በላይ የሚያስፈልጋቸውን ሙዚቃ ለይተው በቁጥሩ መሰረት ትከሻቸውን እየወዘወዙ እስክስታ ይመታሉ።

Image copyright kidus Abebe/facebook

''በፊት ዳንሰኞችን ሳይ በጣም እቀና ነበር ፤ እኔ ይህን ለማድረግ አልችልም ብዬ ብዙ ሳዝን ቆየሁ፤ በኋላ ግን ካልሆነም ይቀራል ለምን አልሞክርም ብዬ ሰዎችን ሳማክር 'መስማት ለማይችል ሰው ውዝዋዜ የማይታሰብ ነገር ነው አሉኝ' ይላል በቴሌቪዥን ባያቸው ዳንሶች ወደ ውዝዋዜ የተሳበው ቅዱስ።

''ብዙ ቦታ ሞክርኩ ግን የሁሉም ኃሳብ አንድ አይነት ነበር። ግን በመጨረሻ ተስፋ ሳልቆርጥ ብጠይቅ ስለዚህ ቡድን የሚያውቅ ሰው አገኘሁና ይዞኝ መጣ''

ቅዱስ ቡድኑን ቢቀላቀልም በእርግጥም ውዝዋዜውን እንደሚችል ራሱን ለማሳመን ብዙ ጊዜ ፈጅቶበታል፤ ሂደቱንም ቴክኒኩንም በድንብ እስኪረዳው ድረስ ያለመታከት በቤትም በልምምድ ቦታውም ብዙ ሰርቷል ።

''የሙዚቃውን ስሜት ለመረዳት ማጫወቻውን ወለል ላይ ስናስቀምጠው እግራቸን ላይ ንዝረቱ ይሰማናል። ከታች ተነስቶ በመላ አካሌ ላይ እንዲሰማኝ ሙዚቃው በደንብ መከፈት አለበት፤ ያኔ ንዝረቱ ሌላ አለም ውስጥ ይከተኛል ፤ እወነትም መወዛወዝ እንደምችል ያወቅኩ ጊዜ በራሴ በጣም ኮራሁ፤ አሁንም አላቆምም ገና ብዙ እሰራለሁ'' ብሏል ቅዱስ።

ቡድኑን ገና እንደተቀላቀሉ ብዙዎቹ ሂደቱን መረዳት ይከብዳቸዋል፤ የ19 ዓመቷ ስምረትም ለዳንስ ልዩ ፍቅር ቢኖራትም ትክኒኩን ለመረዳት ተቸግራ ነበር።

'' መጀመሪያ አካባቢ በጣም ያስቸግረኝ ነበር ፤ ደጋግሜ ድምጹን ከፍ አድርገው ነበር ። በተለይ አማርኛ ሲሆን ምቱን መረዳት ስልላቻልኩ 'ድገሙልኝ ድገሙልኝ ' እል ነበር'" ትላለች ።

ከተወዛዋኞቹ ብዙሃኑ የትግርኛ ሙዚቃዎችን ይመርጣሉ፤ ምክኒያቱም የዜማው አጣጣልና የከበሮው ድምጽ የሚፈጥረው ምት ጥርት ያለና ከፍተኛ ንዝረት የሚፈጥር ነው።

ለተቀናጀ የዳንስ እንቅስቃሴ (ኬሮግራፊ)መድረክ ላይ እንዴት ይግባባሉ?

መስማት የሚችሉ ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስና ቦታ ለመቀያየር ብዙ ጊዜ የዜማውን ለውጥ እንደምልክት ይጠቀማሉ፤ ለዚህም አስቀድመው በንግግር ይግባባሉ።

''እኛ ደግሞ የምንግባባው በእይታ ነው'' ይላል ቅዱስ " ከፊት ያለው ተወዛዋዥ ከኋላ ያሉትን የመምራት ኃላፊነት ይጣልበታል ምክኒያቱም መጀመሪያ የሚቀይረው እርሱ ነው ከዛ ሌሎቹን እሱን ይከተላሉ ፤ ስለዚህ ከሌሎቹ የሚጠበቀው የሚደረጉ የእንቅስቃሴና የቦታ ለውጦችን በቅድመ ተከተል መያዝ ብቻ ነው ፤ አንዳንዴ ደግሞ የምት ቆጠራው ብዙም በማይወሳሰብበት ሙዚቃ ከስንት ምት በኋላ እንደምንንቀሳቀስ ቀድመን ተነጋግረን የጋራ ውዝዋዜዎችን እንሰራለን"

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው የወረዳ 3 ወጣቶች ማዕከል ልምምዱን የሚሰራውና በሚያዝያ 2008 የተቋቋመው ይህ ቡድን በ 14 አባላት ውዝዋዜና ቲያትሮችን በተለያዩ መድረኮች ያቀርባል።

ሲሳይ ተሰማ የዚህ የውዝዋዜና የቲያትር ቡድን ዋና ስራ አስኪያጅና አሰልጣኝ ነው፤ በሳምንት ሶስት ቀናት ከ 8 እስከ 11 ከ 30 ስልጠና ይሰጣቸዋል።

ቡድኑ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ መስማት በተሳናቸው ብሄራዊ ማህበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ የልዩ ፍላጎት ትምህርትና፡ መስማት በተሳናቸው ስፖርት ፌዴሬሽን ድጋፍ እንደሚደረግለት ይናገራል።

ሆኖም ብዙ እቅዶቹ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከዳር አይደርሱም ባይ ነው።

"እኛ ብዙ እያሰብን እቅድ ብናወጣም ለባለሙያ የምንከፍለው ገንዘብ የለንም፤ ግን አሁንም ተስፋ አልቆርጥም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚሆን ቲያትር ቤትና የቴሌቪዥን ውድድር የማዘጋጀት ህልም አለኝ። "