ቆጠራ እንዴት ተጀመረ ?

Image copyright Science Photo Library
አጭር የምስል መግለጫ ይህ የሸክላ ጡብ በሱሜሪያ "ኩኒፎረም" የአናብርት ሽያጭ ተመዝግቦበታል

በጥንታዊ ስልጣኔ ዘመን ጽሁፍ ለምን ተፈጠረ? የሚለው ጥያቄ ለበርካታ አመታት ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል ፤ ለኃይማኖታዊ ወይስ ለኪነጥበባዊ እሴቶች ? በርቀት ከሚገኙ የጦር አባላት ጋር መረጃ ለመለዋዋጥስ ሊሆን ይችላል?

በተለይም በጎርጎሮሳውያን የጊዜ ቀመር በ 1929 ጀርመናዊው የቅሪተ አካል ተመራማሪ ጁሊየስ ጆርዳን የ5000 ዓመታት እድሜ ያላቸውን ለመጻፊያነት የሚገለገሉ የሸክላ ጡቦችን ካገኘ በኋላ ምስጢራዊነቱም ጉጉቱም እየጨመረ መጣ።

ምክኒያቱም ጡቦቹ በቻይና በግብጽና በአሜሪካ ከተገኙት የጽሁፍ ናሙናዎች የበለጠ እድሜ ያላቸውና "ኩኒፎርም" በተሰኘው ረቂቅ አጻጻፍ የሰፈሩ ናቸው።

ሸክላዎቹ በአሁኗ ኢራቅ በጥንታውያኑ ሜሶፖታሚያውያን በኤፍራጠስ ወንዝ ዙሪያ ከሰፈሩባት ዩሩክ ከተማ የመጡ ናቸው።

ዩሩክ ለአሁኑ የከተሞች መመዘኛ አንሰተኛ ብትሆንም ለዛ ዘመን ግን ትልቅና በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የነበሩባት ስፍራ ናት።

የዚች ታላቅ ከተማ ነዋሪዎች ዘመናዊ ሊቃውንትም ሊረዷቸውም ሊተርጉሟቸውም ያልቻሏቸውን ጽሁፎች ያዘጋጁ ነበር፤ ነገሩ ለቅሪተ አካል ተመራማሪዎችም እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው፤

ጁሊየስ ጆርዳን ግን ነገሩን በሌላ እይታ ነበር የተመለከተው፤ ሸክላዎቹ ለእለት እለት ተግባራት የምንጠቀምባቸውን በብልቃጥ በምግብና በእንስሳት ቅርጽ የተሰሩ መሆናቸውን አስተውሏል፤ ግን ጥቅማቸው ምን ነበር? የሚለውን ጥያቄ ማንም መመለስ አልቻለም ።

የፈረንሳዊው የቅሪተ አካል ተመራማሪ ዴኒስ ቤሰራ መላምት ግን ሸክላዎቹ በቅርጻቸው መሰረት ለቆጠራ እንደቦኖ ያገለግሉ ነበር የሚል ነው፤ በዳቦ ቀርጽ የተሰሩት የዳቦ ቆጠራ፣ በብልቃጥ መልክ የተሰሩት ደግሞ ምለብልቃጥ ቆጠራ ይውላሉ ።

ይህ ደግሞ ከዩሩክ መመስረት በፊትም የነበረ ቴክኒክ ነው።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ በናይል አቅራቢያም የ20ሺህ ዓመት እድሜ ባለው የኢሻንጎ አጥንት ለቆጠራ እንዲመች ምልክት የተደረገበት የጭን አጥንት ተገኝቷል።

Image copyright ROYAL BELGIAN INSTITUTE OF NATURAL SCIENCES/THIER
አጭር የምስል መግለጫ አጥንቶቹ ለቆጠራ የሚያገለግሉ መስመሮች ተጭረውባቸዋል

የዩሩክ ግኝቶች ደግሞ ምርምሩን ወደፊት አሻግረውታል- በሽክላ በተሰሩ ቦኖዎች የተለያ መጠን ያላቸውን ቁሶች ለመቁጠር ፣ ለመደመርና ለመቀነስ ይጠቀሙባቸው ነበር።

የከተማ ምጣኔ ኃብት

ዩሩክ ታላቅ ከተማ ነበረች ፤ የከተማ ምጣኔ ኃብት ደግሞ ፣ ንግድ እቅድ እና የታክስ ስርዓት ያስፈልገዋል። እስኪ የዓለማችንን ቀደምት የሂሳብ ባለሙያዎች መጋዘን በር ላይ ሆነው የማዳበሪያ እህልን በሸክላ ቦኖዎች ሲቆጥሩ አስቧቸው።

ዴኒስ ቤሳር ሌላ ያስተዋለው ነገር ጽሁፉ በሚሰፍርባቸው የሸክላ ጡቦች ላይ ያሉት ረቂቅ ምልክቶችም ከሸክላ ቦኖዎች ጋር እንደሚመሳሰሉ ነው።

ጡቦቹ የቦኖዎቹን የንግድ እንቅስቃሴ ሲመዘግቡ መቆጠሪ ቦኖዎች ደግሞ የበጎችን ፣ የእህሉንና የማር ገበያውን እንደሚመዘግቡም ተረዳ።

እንዲያውም የመጀመሪያዎቹ ጡቦች ከጠንካራ የሸክላ ጌጦች ጽሁፍ ሊሰፍርባቸው ወደሚችሉ ለስላሳ ሸክላዎች የመለወጡን ሂደት ስለሚወክሉ የመቁጠሪያዎቹ ተምሳሌት ሊሆኑ ይችላሉ።

ከዚህ በኋላ ቀደምት የሂሳብ ባለሙያዎች ጽሁፎቹን በቀላሉ ለማስፈር ብዕር እንደሚያስልግ ተረዱና የ "ኩኒፎርም" አጻጻፍን ፈጠሩ።"ኩኒፎርም" በአንድ አቅጣጫ እየቀጠነ ከጫፉ እየተሳለ የሚሄድ ቅርጽ እንደማለት ነው፤ ጽሁፉም የሚወክለው ይህንኑ ነው።

የማረጋገጫ መንገዶች

እነዚህ የሸክላ ጡቦች የተሰሩት ለስነ ግጥምም ሆነ ሩቅ ካሉት ጋር ለመግባባት አይደለም ፤ ይልቁንም የዓለማችንን የመጀመሪያ የሂሳብ አያያዝ ጥበብ ለመፍጠርና የመጀመሪያውን የተጻፈ ስምምነት ለማስፈር ነው ።

በወቅቱ በተፈጸሙ ክፍያዎችና አስቀድመው በሚሰፍሩ የገንዘብ ግዴታዎች መካከል የሚኖረው ልዩነትም በጣም አነስተኛ ነበረ።

በጊዜ ሂደት ደግሞ እነዚህ የሸክላ ቦኖዎችና የ "ኩኒፎርም" ጡቦች ለአስደናቂ የማረጋገጫ ዘዴም ምልከታ ሰጡ-'' ቡላ" የተሰኘ የሸክላ ሳጥን።

Image copyright Alamy
አጭር የምስል መግለጫ እነዚህ ከኢራቅ የተገኙ ቡላዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ8ኛው ሺህ ዘመን የተፈጸሙ የግብርና ግብይቶች ተመዝግበውባቸዋል

''ቡላ'' በውጪ በኩል ስምምነቱን የፈጸሙት አካላት የሚጠበቁ ክፍያዎችን ጨምሮ ዝርዝር ግዴታዎቻቸውን ያሰፍሩበታል ።

በውስጡ ደግሞ ስምምነቱን የሚወክሉ የሸክላ ቦኖዎች ተጨምረውበት ይታሸጋል፤ ስለዚህ በውጭ የተቀመጡ ግዴታዎችና በውስጥ ያሉት የመቁጠሪያ ቦኖዎች አንዳቸው ለሌላኛው እንደማመሳከሪያ ይጠቅማሉ ማለት ነው።

ስምምነቱን የሚፈጽሙት አካላት ለቤተክርስቲያን አስራት የሚያወጡ ምዕመናን ፡ ታክስ ከፋዮች ወይም ግለሰብ ተበዳሪዎች ይሁኑ የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም ስምምነቱ የግዢ ትዕዛዞችንና የመቀበያ መንገዶችን በማስተዋወቅ የተወሳሰበውን የከተማ ኑሮ ያቅልላቸው ነበር።

ይህ ደግሞ በጣም ትልቅ ነገር ነው፤ ኣሁን የገንዘብ ዝውውሮች ፣ ዋስትናዎች ፣ የባንክ ደብተሮች ፣ የመንግስት ቦንዶች ፣ የድርሻ ውሎች ፣ የቤት ብድሮች ሁሉ የሚፈጸሙት በጽሁፍ ስምምነቶች ነው። የሜሶፖታሚያው "ቡላ" ደግሞ የጽሁፍ ስምምነቶች እንደነበሩ ያረጋገጠ የመጀመሪያው የቅርስ ጥናት ማስረጃ ነው።

የዩሩክ የሂሳብ ባለሙያዎች የሌላ ፈጠራም ባለቤቶች ናቸው።

በቅድሚያ አምስት በጎችን ለመመዝገብ አምስት በግን የሚወክሉ የሸክላ ቦኖዎች ያስፈልጉ ነበር፤ ይህ ዘዴ ግን አድካሚ ነበር። እናም የተለያዩ ቁጥሮችን በምልክቶች የመወከልን ስልት ቀየሱ፤ አምስት ጭረቶች ለአምስት ቁጥር ፣ክብ ለአስር ቁጥር ፣ ሁለት ክቦችና ሶስት ጭረቶች ለ 23 ቁጥርና ሌሎች መሰል ምልክቶችን ፈጠሩ።

ይህን የመቁጠሪያ ስርዓት በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ቁጥሮችንም ለመያዝ ይጠቀሙበት ነበር።

በአጠቃላይ የዩሩኮች ስኬት ብዙ ነው፤ ግን ትልቅ ችግርም ነበረባቸው።

የዘመናዊ ኢኮኖሚ መገለጫ የሆነው በርካታ አካባቢዎችን የሚያማክሉ እቅዶችንና ኃላፊነቶችን እርስ በእርስ ለማይተዋወቁ ሰዎች ማጋራት አስቸጋሪ ነበር።

ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ ተከታታይ ምጡቅ ግኝቶችን ይጠይቅ ነበር-የመጀመሪያዎቹን የሂሳብ መዝገብ አያያዝና የጽሁፍ ስምምነቶች ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያውን የሂሳብ ሳይንስና የመጀመሪያው ጽሁፍን መፍጠር ያስፈልጋል።

እናም ጽሁፍ ገና ከጅማሬው ለኪነጥበባዊ ሳይሆን ለምጣኔ ኃብታዊ ጥቅሙ ሲል የተፈጠረ ነው።