የሙዚቃ ክዋክብት ምጣኔ ኃብት፡ የሸክላ ማጫወቻ ለሙዚቃ ምን አበርክቷል?

Image copyright Getty Images

የዓለማችን ከፍተኛ ተከፋዩ አቀንቃኝ ማነው? እንደፎርብስ መጽሔት በአውሮውያኑ 2015 ዓ.ም 100 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት ኤልተን ጆንን የሚስተካከለው አልተገኘም።

በእርግጥ ዩ ቱ የተሰኙት ዘፋኞች ከእርሱ በሁለት በእጥፍ የሚበልጥ ገቢ አግኝተዋል ግን እነርሱ አራት ሲሆኑ ኤልተን ጆን ብቻውን ነው።

ይህ ጥያቄ ከ 215 ዓመታተ በፊት ተጠይቆ ቢሆን ኖሮ ግን መልሱ ኤልዛቤት ቢሊንግተን የሚል ይሆን ነበር።

ለብዙዎች እስካሁን አቻ ያልተገኘላት "ሶፕራኖ" የተባለው የሙዚቃ ስልት አቀንቃኝ ነበረች።

በጣም ዝነኛና በመድረክ ላይ ለማዜም ብዙዎች በከፍተኛ ዋጋ የሚጫረቱባት ተወዳጅ ሙዚቀኛም ነበረች።

በወቅቱ የለንደን የታዋቂ ኦፔራ ቤቶች ሥራ አስኪያጆች የነበሩት ኮቨናንት ጋርደንና ድሩሪ ሌን እሷ በመድረክ ላይ እንድታዜምላቸው ለማግባባት ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ገበተው ነበር፤ በኋላም በሁለቱም መድረኮች ላይ ተጫውታ በአውሮፓውያኑ 1801 ገቢዋ 15 ሺህ ዶላር ደርሶ ነበር። ይህ ገንዘብ ደግሞ በወቅቱ በጣም ከፍተኛ የሚባል ነው።

በአሁኑ ጊዜ የሚኖረው ዋጋ ግን ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነው። ከኤልተን ጆን ገቢ 1 በመቶውን ብቻ ማለት ነው።

Image copyright Getty Images

አሁን ኤልሳቤጥ ቢሊንግተን ከሞተች ከ60 ዓመታት በኋላ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አልፍሬድ ማርሻል በወቅቱ አሜሪካ፣ ብሪታኒያና አውስትራሊያን አስተሳስሮ የነበረውን የኤሌክትሪክ ቴሌግራፍ ተጽዕኖን ገምግሟል።

ለእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ምስጋና ይግባቸውና "የማዘዝ ስልጣናቸውን ያረጋገጡ ወንዶች ከመቼውም ጊዜ በላይ የንድፈ ሃሳብም ሆነ የተግባር ችሎታቸውን ወደ ሰፋፊ ቦታዎች እንዲያዳርሱ አስችሏቸዋል" ይላል ማርሻል።

የዓለማችን በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ግንባር ቀደም ሃገራትም በፍጥነት እያደጉ ነበር። በእነርሱና ያነሰ የሥራ ፈጠራ በነበራቸው መካከል የነበረውም ክፍተት እየሰፋ ሄደ።

ነገር ግን ማርሻል እንደሚለው የሁሉም ሙያዎች ምርጦች ስኬታማ አልነበሩም።

ለምሳሌ በመድረክ ላይ በሚቀርቡ የጥበብ ስራዎች "የሰዎችን ድምፅ ያለምንም ማጉያ መሳሪያ መስማት የሚችሉ ሰዎች ብዛት በጣም ውሱን ነበር፤ የድምጻውያኑ ገቢም እንደዚያው።''

ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1877 ግን ቶማስ ኤዲሰን የመጀመሪያውን የሰዎችን ድምጽ መቅረጽና በድጋሚ ማሰማት የሚችለውን መሳሪያ ፈጠረ።

Image copyright Getty Images

መቅረጸ ድምጹ በጠንካራ ፕላስቲክ ውስጣቸው ባዶ ሆኖ በክብ ቅርጽ የተሰሩ መቅረጫዎችን እየተሽከረከሩ ድምጹን የሚያስቀሩበት ከዚያም መልሰው የሚያጫውቱበት ፈጠራ ነበር።

መጀመሪያ መቅረጽ ማለት በመተየቢያ መሳሪያ ላይ የካርቦን ቅጂ እንደመፍጠር ነበር፤ አንድ ጊዜ ሲያቀነቅኑ መቅረጽ የሚቻለው በሦስት ወይም በአራት ማጫወቻዎች ብቻ ነበር።

በዚሁ ምክንያት በ1890ዎቹ የአሜሪካዊውን ጆርጅ ጆንሰንን ሙዚቃዎች የመስማት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ቀን በቀን ያለመታከት አንዱን ሙዚቃ በተደጋጋሚ የማስቅረጽ ግዴታ ነበረበት።

በቀን ሃመሳ ጊዜ እንኳን ቢቀረጽ የሚኖረው ከፈተኛ የቅጂ 200 ብቻ ነው፤ እናም ድምጹ እስኪዘጋ እሱም በቃኝ እስኪል ድረስ አንዱን ሙዚቃ መልሶ መላልሶ ይጫወት ነበር።

የኮከብ አቀንቃኞች ምጣኔ ብት

ኤምል በረሊንር በሸክላ ዲስክ የመቅረጽ ቴክኖሎጂን ሲያስተዋውቅ ለብዙ ቅጂዎች መፈጠር መንገድ ተከፈተ። ሬዲዮና ፊልምም ተከተሉ።

እንደቻርሊ ቻፕሊን ያሉ ሥራዎችም በቀላል ዓለማቀፍ ገበያን መቀላቀል ጀመሩ። ለቻርሊ ቻፕሊን እና ለኤልተን ጆን ቴክኖሎጂ የከፍተኛ ዝናና የተጫማሪ ገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል፤ ለሌሎች ግን ትልቅ አደጋ ነበር።

ያኔ በኤልዛቤት ቢሊንገተን ጊዜ በርካታ ልምድ ያላቸው አቀንቃኞች በሙዚቃ አዳራሾች በቀጥታ ይጫወቱ ነበር። እሷም ብትሆን በአንድ ጊዜ ልትጫወት የምትችለው በአንድ መድረክ ላይ ብቻ ነበር።

ሆኖም የዓለም ታላላቅ ሙዚቀኞችን ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ማድመጥ እየተቻለ ገና በውድድር ላይ ያሉትን ፊት ለፊት ማየቱ ምን ይፈይዳል?

የመቅረጫ መሳሪያዎቹ ሙዚቃቸውን ወደሚያሰቀርጹ አርቲስቶች ኪስ ዳጎስ ያለ ገንዘብን ሲስገቡ፤ በመድረክ ላይ ብቻ የሚጫወቱት ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው እንዲዳከም አድርገዋል።

የቴክኖሎጂ ግኝቶች በሌሎች ዘርፎች ላሉ ታዋቂ ሰዎችም ቢሆን የከፍተኛ የሃብት ምንጭ ሆነውላቸዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች የሳተላይት ቴሌቪዥን መፈጠር ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል

ከጥቂት አስር ዓመታት በፊት በየሳምንቱ የሚደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ሊያይ የሚችለው በስታዲየም የተገኘው ሰው ብቻ ነበር።

አሁን ግን እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሳተላይት ቴሌቪዥን በአንድ ጊዜ ይታደሙታል።

በ1980ዎቹ እንኳን የእንግሊዝ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ተጫዋቾች በሦስተኛው ዲቪዚዮን ካሉት ሁለት እጥፍ የሚደርስ ገንዘብ ያገኙ ነበር ፤ አሁን ግን ገቢያቸው በ25 እጥፍ ይበልጣል።

ያለእኩልነት የመዝለቁ ጉዳይ

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የካሴት፣ ሲዲና የዲቪዲ ፈጠራዎች የአርቲስቶችን ምጣኔ ሃብት ይበልጥ እያሳደጉት መጡ።

በጊዜ ሂደት ደግሞ ሰዎች የሚፈልጉትን ሙዚቃ ለማድመጥ ማንኛውንም አይነት ዲስክ መግዛት ሳይኖርባቸው፤ ያለምንም ወጪ በቀላሉ በበይነ መረብ ማግኘት ቻሉ።

አርቲስቶቹም አልበሞቻቸውን ለመሸጥ የሙዚቃ ዝግጅታቸውን የመግቢያ ቲኬቶች ከመጠቀም ይልቅ በተገላቢጦሽ አልበሞች የመድረከ ትኬቶች ማሻሻጫዎች ሆኑ።

ኢንደስትሪው እስካሁኑ ዘመን ያለእኩልነት መዝለቁ ግን አሁንም በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው።

አንድ በመቶ የሚሆኑት ታዋቂ አርቲስቶች ከሙዚቃ ዝግጅቶች የሚያገኙት ትርፍ ሌሎቹ 95 በመቶ የሚሆኑት ሙዚቀኞች ከሚያገኙት ገቢ ድምር ቢያንስ በአምስት እጥፍ ይበልጣል።

ተያያዥ ርዕሶች