ሂዩስተን፡ በጎርፍ የተጎዳው የኬሚካል ማምረቻ ለኢትዮጵያዊያንም ሥጋት ሆኗል

Image copyright Getty Images

በከባድ ንፋስና ዝናብ በተመታችው ሂዩስተን ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ የኬሚካል ማምረቻ በቀጣይ ቀናት ሊፈነዳ ወይም በእሳት ሊያያዝ እንደሚችል ተሰግቷል።

ከባድ ዝናብ በጣለባቸው ቀናት አርኬማ የተሰኘው የኬሚካል ማምረቻ ምርቱን ማቀዝቀዝ ባለመቻሉ የእሳት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ፋብሪካው ገልጿል።

እስካሁን ባለው መረጃ ከባድ ንፋስና ዝናብ ካስከተለው "ሀሪኬይን ሃርቪ" በኋላ ቢያንስ 33 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ሂዩስተን ቴክሳስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውን ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስካሁን ባላቸው መረጃ ከመካከላቸው በአደጋው ህይወቱን ያጣ ሰው እንደሌለ ገልጸዋል። ነገር ግን ቤታቸው በጎርፍ ተጥለቅልቆ ወደ መጠለያዎች የገቡና በአቅራቢያ ወደሚገኙ ግዛቶች የሄዱ እንዳሉ ተናግረዋል።

የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወይኒ ሳሙኤል አደጋው ሲደርስ ቤቷ በጎርፉ በመጥለቅለቁ ምክንያት ልጆቿን ይዛ በመንግስት ወደተዘጋጀው መጠለያ ከገባች አምስት ቀናት ሆኗታል።

በአደጋው ወቅት እሷና ልጆቿ እጅጉን ተደናግጠው የነበረ ሲሆን፤ ልጇቿ እስካሆን ከድንጋጤው አላገገሙም።

እምብዛም በጎርፉ ጉዳት ባልደረሰበት የሂዩስተን ክፍል ነዋሪ የሆነው በፈቃዱ ሞረዳ ለተከታታይ አምስት ቀናት ከቤት መውጣት ካለመቻሉ ውጪ አስጊ ሁኔታ አልገጠመውም።

ትልቋ የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ማምረቻ ከተማ በሆነቸው ሂዩስተን ውስጥ ከ125 በላይ የነዳጅ ማጣሪያዎች እንዳሉ የተናገረው በፈቃዱ በጎርፉ ሳቢያ የነዳጅ እጥረት አጋጥሟል ይላል።

በአሁኑ ጊዜ ዝናቡ ጋብ ያለ ቢሆንም በከፍተኛ ደረጃ በውሃ ተሞልቶ ለአደጋ የተጋለጠውን የከተማዋን የውሃ ግድብ ለማስተንፈስ ሲባል የሚለቀቀው ውሃ የጎርፉ መጠን እንዳይቀንስ አድርጎታል ይላል በፈቃዱ።

Image copyright Haile Tefera

ሊፈነዳ ወይም በእሳት ሊያያዝ ይችላል የተባለው የኬሚካል ማምረቻም ነዋሪውን እንዳሳሰበ በፍቃዱ ጠቅሶ አሁንም ድረስ ማዕከላዊው የከተማዋ ክፍል በጎርፉ እንደተጥለቀለቀ ተናግሯል።

እስካሁን ድረስ 32000 የሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች በጊዜኣዊ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን 24000 የሰራዊት አባላት ችግሩን ለመቋቋም እየሰሩ ነው።