ሕንድ ውስጥ ህንፃ ተደርምሶ ሰባት ሰዎች ሞቱ

ነሐሴ 25 ሙምባይ ውስጥ የተደረመሰው ህንፃ
አጭር የምስል መግለጫ አምቡላንሶች፣ የእሳት አደጋ መኪኖችና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአደጋው ሥፍራ ነፍስ ለማዳን ጥረት ሲያደርጉ።

ሙንምይ ውስጥ በደረሰ የህንፃ መደርመስ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ በፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ በርካታ ሰዎችን ለማዳን የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍለጋ ላይ መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የሕንድ የንግድ ከተማ በሆነችው ሙምባይ ባለስድስት ፎቅ ህንፃ የተደረመሰው ሃሙስ ዕለት ነው።

ብዙ ህዝብ በሚኖርበት ብሄንዲ በተባለው አካባቢ ይገኝ ነበረው ይህ ህንፃ መቶ ዓመታት የሚደርስ እድሜ ነበረው ተብሎ ይታመናል።

አምቡላንሶች፣ የእሳት አደጋ መኪኖችና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአደጋው ሥፍራ ነፍስ ለማዳን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ሙምባይ ካጋጠማት ከባድ ዝናብና ጎርፍ ገና በማገገም ላይ ትገኛለች።

የመኖሪያ ህንፃው የመፍረስ አደጋ የደረሰበት በህንድ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት ሁለት ሰዓት ከአርባ ገደማ እንደሆነ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

''አርባ የሚደርሱ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ አሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን፤ አርባ ሶስት አባላት ያሉት የነፍስ አድን ቡድን በፍለጋ ላይ ተሰማርቷል'' ሲሉ አንድ የህንድ ብሄራዊ የአደጋ መከላከል ኃይል ባለሥልጣን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ሙምባይ ውስጥ ከተደረመሱ ህንፃዎች መካከል ይህ ሦስተኛው ነው። ፖሊስ እንደሚጠረጥረው ማክሰኞ ዕለት የጣለው ከባድ ዝናብ የህንፃውን መዋቅር በማዳከም እንዲፈርስ አድርጎት ሊሆን ይችላል።

ምክንያቱ ትክክል ይሁንም አይሁን፤ ዋናው ጥያቄ በዚህች እያደገች ባለች ከተማ ስለምን በርካታ ሰዎች ባረጁና ለአደጋ በተጋለጡ ህንፃዎች ውስጥ እንዲኖሩ እንደሚፈቀድ ነው።

ሙምባይ ውስጥ ቤቶችን የመግዣም ሆነ የመከራያ ዋጋ እስያ ውስጥ ካሉት ውድ ከተሞች መካከል የሚመደብ ነው።

ጥራታቸው በተጠበቀ ሁኔታ የተገነቡ ህንፃዎች አቅርቦት ውስን ነው፤ በመሆኑ በርካታ ሰዎች አማራጭ በማጣት ደረጃቸውን ባልተበቁና በተጨናነቁ ህንፃዎች ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ።

የተደረመሰው ህንፃ ምንም እንኳን 100 ዓመታትን በማስቆጠሩ ፈርሶ ስፍራው ለመልሶ ግንባታ እንዲዘጋጅ የተለየ ቢሆንም ሰዎች እየኖሩበት ነበረ።

ነዋሪዎችን ለአደጋ ከተጋለጡ ህንፃዎች ለማስወጣት የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ባለሥልጣናት ጥረታቸውን ቢያጠናክሩም በሚፈለገው ፍጥነት ግን እየተከናወነ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ሕንድ ውስጥ በህንፃዎች ላይ የመደርመስ አደጋ የሚደጋገም ሲሆን፤ በተለይ በዝናባማ ወቅቶች ይከሰታል። ደካማ የግንባታ ጥራት ደረጃና የህንፃዎች ማርጀት የዘወትር ምክንያቶች ናቸው።

ሕንድ ውሰጥ በየዓመቱ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በህንፃዎች መደርመስ ሳቢያ ለሞት ይዳረጋሉ።

ባለፈው አንድ ወር ብቻ ሙምባይ ውስጥ ሦስት የህንፃዎች መፍረስ አደጋ አጋጥሟል። ባለፈው ሃምሌ ወር ጋትኮፓር በተባለ ሥፍራ ባለአራት ፎቅ ህንፃ ተደርምሶ 17 ሰዎች ሞተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ