ሶስት ቃላትን ብቻ በመጠቀም አድራሻዎትን መግለጽ ይችላሉ?

ዋት3ዎርድስ Image copyright What3words

ቀደም ሲል ምንም አድራሻ የላቸውም ወደ ሚባ የዓለም አካባቢዎች ዕቃዎችን፣ ፖስታዎችን እንዲሁም ፒዛን ሳይቀር በቀላሉ ማቅረብ ተችሏል።

የሞንጎሊያ ነዋሪዎች የት እንደሚኖሩ የሚጠቁሙ ሶስት ቃላትን ብቻ በመጠቀም የባንክ ደብተር ማውጣትም ችለዋል።

አዲስ አበባ ውስጥም ያሉበትን ቦታ የሚያመለክቱ ሶስት ቃላትን ብቻ በመጠቀም ያዘዙት ምግብ ያሉበት ቦታ ድረስ እንዲቀርብ ማድረግ ይቻላል።

ይህ የተሳካው ዓለምን በሶስት ሜትር ስኩዌር 57 ትሪሊዮን ቦታ ከፋፍሎ ለእያንዳንዱ ክፍል ሶስት የተለዩ ቃላት ያላቸው መለያዎችን በሚሰጠው ዘዴ ነው።

ዋት3ዎርድስ የተሰኘው ዘዴ አሩሻ ታንዛንያ ውስጥ በተዘጋጀ ቴድግሎባል ኮንፈረንስ ላይ ለሁሉም አድራሻ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት አስታውቋል።

"አድራሻ ከሌለን መኖራችንም ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል" ሲል ከሃሳቡ አመንጪዎች መካከል አንዱ የሆነው ክሪስ ሼልድሪክ ይገልጻል።

"የባንክ ደብተር እንደማውጣት ያሉ ብዙ አገልግሎቶች አድራሻን ይፈልጋሉ። ይህንን ማግኘት ደግሞ ለአንዳንዶች ከባድ ሲሆን ለሌሎች ደግሞ የማይቻል ነው።"

በደቡብ አፍሪካ ደርባን የሚገኝ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ይህን ዘዴ ተጠቅሞ ለ11000 ነፍሰጡር እናቶች የሶስት ቃላት አድራሻ ይሰጣል።

"ቀደም ሲል አምቡላንስ ጠርተው እርዳታ እስኪያገኙ ድረስ ሰዓታትን ይፈጅ ነበር። አሁን ግን ደውለው የሶስት ቃላት አድራሻቸውን ብቻ በመስጠት በቀላሉ ያሉበትን ማሳወቅ ይችላሉ" ይላል ሼልድሪክ።

ዴሊቨር አዲስ ዘዴውን ተጠቅሞ አዲስ አበባ ከሚገኙ 25 ምግብ ቤቶች ደንበኞቹ ወዳሉበት ምግብ ያደርሳል።

ዋት3ዎርድስ ነዋሪዎች ባንክ ደብተር ሲያወጡ የሶስት ቃላት አድራሻቸውን የባንክ ፎርም ላይ እንዲሞሉ የሚያስችለውን ውል በቅርቡ ሞንጎሊያ ከሚገኘው ከሃን ባንክ ጋር ፈጽሟል።

"ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ በሆነ መንገድ የባንክ መረጃዎችን ለደንበኞች መስጠት ወሳኝ ነው" ሲል የከሃን ባንክ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ጃቭክላን ቱርሙንክህ ይገልጻል።

"ብዙ ጊዜ በደንበኞች የሚሞላው አድራሻ የሚታወቅ ባለመሆኑ መረጃዎችን በምንልክበት ወቅት ከመደበኛው የፖስታ አድራሻ በተጨማሪ የደንበኞችን የሶስት ቃላት አድራሻ እንጠቀማለን። ይህ ደግሞ ደንበኞች የትም ቢሆኑ የመረጃዎችን ደህንነት ጠብቀን እንድናደርስ ረድቶናል።"

ዋት3ዎርድስ በቅርቡም ከናይጄሪያ የፖስታ አገልግሎት ጋር ውል ተፈራርሟል።

ናይጄሪያ በምጣኔ ሃብት ረገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ካላት 180 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 20 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው የሚላክላቸው ፖስታ ቤታቸው ድረስ የሚመጣላቸው። የናይጄሪያ ፖስታ እና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይህንን ቁጥር በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ወደ 70 በመቶ ለማድረስ አቅዷል።

ዘዴው እስካሁን በሞንጎሊያ፣ በአይቮሪኮስት፣ በቶንጋ እና በሰለሞን ደሴቶች የፖስታ አገልግሎቶች ላይ ተግባራዊ ሆኗል።

ቀላል መፍትሔ

ክሪስ ሼልድሪክ ለአስር ዓመታት ሙዚቀኛ ሆኖ ከሰራ በኋላ ነው ድርጅቱን በ2013 (እአአ) ያቋቋመው።

"አዲስ ቦታ ስንሄድ ሁሌም ሰዎች ይጠፋሉ። የባንዱ አባላት ጂ ፒ ኤስ (አቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ) እንዲጠቀሙ ብመክርም ፍላጎት የላቸውም ወይም አጠቃቀሙ ላይ ስህተት ይፈጥራሉ።" የሚለው ሼልድሪክ፤

"በዚህ ወቅት የሂሳብ ባለሙያ ከሆነ ጓደኛዬ ጋር ቀላል መፍትሄ እንዴት መፍጠር እንደምንችል መነጋገር ጀመርኩ።"

በዚህም የሂሳብ ቀመርና 40 ሺህ ቃላትን አገኙ። ቀደም ሲል በእንግሊዝኛ ብቻ የነበሩት ቃላት አሁን በ14 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል።

ዋት3ዎርድስ ዳታ አጠቃቀም ላይ ገደብ በመጣሉና ኩባንያዎች አገልግሎቱን በሌላ ምርት ሲጠቀሙ እንዲከፍሉ ማድረጉ ትችት አስከትሎበታል።

Image copyright What3words

ይህ ዘዴ የደረሰበት ደረጃ በቴድግሎባል ኮንፈረንስ ላይ ቢቀርብም ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ውሏል ለማለት ገና ረዥም መንገድ ይቀረዋል።

በታንዛንያ የዓለም ባንክ ባልደረባ የሆነው ኤድዋርድ አንደርሰን ዘዴውን በማሻሻል ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መፃህፍት ለማዳረስና የተበላሹ የውሃ ቧንቧዎችን በቀላሉ ለመጠቆም እንዲያስችል ለማድረግ አስቧል።

"ሃሳቡ ጥሩ ቢሆንም ችግር ይኑረው አይኑረው ከወዲሁ አልታወቀም። ሶስቱን ቃላት ለማወቅ ጂ ፒ ኤስ የሚያስፈልግ ሲሆን ዘዴው ሰዎች ያሉበትን ቦታ እንዲያውቁ ሳይሆን ሌሎች እነሱ የት እንዳሉ እንዲያውቁላቸው ለማድረግ ተዘጋጀ ነው" ይላል።

ዘዴው በድምጽ አገልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች ዘንድ ተፈላጊነት ሊኖረው ይችላል ይላል ኤድዋርድ።

"አድራሻዎትን ያለአሽከርካሪ ለሚነዳ መኪና ወይም ዕቃ ለሚያቀርብ ድሮን (አነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላን) በድምጽ ብቻ ሊነግሩ ይችላሉ" ሲል ሃሳቡን ያጠናቅቃል።

ተያያዥ ርዕሶች