የቪዲዮ ጨዋታዎች ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ

በመነጽር የሚጫወቱት የቪድዮጌም ዓይነት የሚጫወት ወጣት Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የቪድዮ ጌሞች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አድርገዋል

ወጣቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፒተር ሳምሶን እ.አ.አ በ1962 መጀመሪያ ላይ ወደ ቤቱ እየተጓዘ ነበር። ከባቡር ወርዶ ወደ ሰማይ ሲመለከት አንዲት ተወርዋሪ ኮከብ ያያል። በዚህ ጊዜ በድንገት እንደጨዋታ እጁን የመኪና መሪ እንደሚያሽከረክር ሰው እየዘወረ ኮከቧ ወዴት እነደተሰወረች ለማወቅ ሰማዩን ከወዲያ ወዲህ ይማትር ነበረ።

ይህ የሳምሶን ቅዠት መሳይ ድርጊት ቁጥር ስፍር ለሌላቸው የዘመናችን የቪዲዮ ጨዋታዎች መፈጠር መነሻ ለመሆን ቻለ።

ከዚያም ፒትር ሳምሶንና በአሜሪካ የሚገኘው የማሳቹሰትስ ቴክኖሎጂ ኢንስትትዩት ተማሪዎችም ስፔስዋር በተሰኘው የቪድዮ ጨዋታን አብዝተው ይጫዉቱ ነበር።

ሰፔስዋር የተሰኘው የቪድዮ ጨዋታም በዓለማችን የመጀመሪያውና ወሳኝ ፈር ቀደጅ ሆነ። ከዚያ ወዲህ ነበር የማህበረሰቡን አመለካከትና ኢኮኖሚውን የቪድዮ ጨዋታዎች እየቀየሩ የመጡት።

ሰፔስዋር ከመምጣቱ በፊት ኮምፕዩተሮች በጣም ትልቅ ከመሆናቸው በተጨማሪ ብዙ ሰው የሚደፍራቸውም አልነበሩም። ለኮምፕዩተሮቹ ተብሎ ለብቻ ሰፊ ክፍል የሚዘጋጅ ሲሆን ተጠቃሚዎቹም ከፍተኛ ሥልጠና የተሰጣቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ በዋነኝነት ኮምፕዩተሮችን ይጠቀሙ የነበሩት ባንኮችና ወታደራዊ ተቋማት ነበሩ።

ቀስ በቀስም ግዙፎቹ ኮምፕዩተሮች በመጠናቸው እያነሱና በትንሽ ቦታ ላይ በቀላሉ ሰዎች እንዲጠቀሙባቸው ቀለል ተደርገው መሰራት ጀመሩ። ተማሪዎችም ለምርምር ሥራዎቻቸው ይጠቀሙባቸውም ነበር።

ስቲቭ ስላግ ራስል በመባል የሚታወቀው የማሳቹሰትስ ቴክኖሎጂ ኢንስትትዩት ተማሪና ጓደኞቹ ነበሩ በትምህረት ቤታቸው ውስጥ በነበረው ፒዲፒ-ዋን በተባለው ኮምፕዩተር ላይ ስፔስዋር የተባለውን የቪዲዮ ጨዋታ የፈጠሩት። እነዚህ ተማሪዎች በርከት ያሉ ሳይንሳዊ መፅሃፍቶችን ያነቡ ስለነበር ስፔስዋርን ከጠፈር ጋር ለማመሳሰል በነበራቸው ምኞት፤ ከዋክብትን ተጠቅመው በሁለት የጠፈር መርከቦችን መካከል የሚደረግ ፍልሚያን የሚወክል የቪዲዮ ጨዋታን ፈጠሩ። ብዙም ሳይቆይ በርካታ ወጣቶች በዚህ ጨዋታ ተማረኩ።

ከጊዜ በኋላም የኮምፕዩተሮች ዋጋ እየቀነስ ሲመጣ የቪድዮ ጨዋታዎች በየቤቱና በማጫወቻ ቤቶች ውስጥ እየበዙና እየተዘወተሩ መጡ። ከገቢ አንፃርም የቪድዮ ጨዋታ ኢንዱስትሪው ከፊልሙ ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ቻለ። ይህ ክስተት ተጠቃሚዎች የቪዲዮ ጨዋታዎችን ለመግዛት ከሚያወጡት ገንዘብ በተጨማሪ በሃገራት ኢኮኖሚ ላይም በብዙ መንገዶች ተፅዕኖ አድጓል።

Image copyright Everquest
አጭር የምስል መግለጫ ኢኮኖሚስቶች ከጊዜ በኋላ የቪድዮ ጨዋታዎች የእውነት ገንዘብ እንደሚገኝበት ተገነዘቡ

ይህንን የቪዲዮ ጨዋታዎች ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ውጤት በደንብ የተነተነው ኤድዋርድ ካስትራኖቫ የተሰኘው ኢኮኖሚስት ነበር። የጥናቱ መነሻም ምናባዊ ከተማን የመሰለው ኖራት የተሰኘውና በአንድ ጊዜ ከዓለም ዙሪያ 60 ሺህ ሰዎችን የሚያጫውተው የቪዲዮ ጨዋታ ነበር። በኖራት ምናባዊ ከተማ ውስጥ ተጫዋቾች በሙሉ አንድ ገፀ-ባህሪን በማጫወት የቻሉትን ያህል ሀብት ማካበት ነበር ዓላማቸው። ከጊዜ በኋላ ግን የጨዋታው ተሳታፊዎች ትዕግስት እያጡ በመምጣታቸው ከሌሎች ተጫዋቾች ላይ በጥሬ ገንዘብ የገፀ-ባህሪያቱን ሀብት ይገዙ ጀመር።

በዚህም የተነሳ በቻይናና በሕንድ ሃገር የሚገኙ ሰዎች የዚህን የቪዲዮ ጨዋታ የሃብት ሽያጭን እንደ መደበኛ ሥራና የገንዘብ ምንጭ አደረጉት። በዚህም ምክነያት ለተለያዩ ጨዋታዎች ጨረታ በጃፓን ሃገር በሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር በወር ለግብይት የሚውልበት ጊዜ አለ። በቅርቡ የብዙ ሰዎችን አድናቆት ካተረፉት ጨዋታዎችም መካከል ካንዲ ክራሽ ሳጋና ፖኬሞን ጎ የሚጠቀሱ ናቸው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የፖኬሞን አዲሱ ፖኬሞን ጎ የተሰኘው ጨዋታ በእውነታ ላይ መመሥረቱ በከፊል ባለቤት ለሆነው ብዙ ገንዘብ አስገኝቷል

እነዚህ የቪድዮ ጨዋታዎች ብዙዎችን ያዝናኑ ይሁኑ እንጂ፤ አጠያያቂ እየሆነ ያለው ስንቱ ሥራ ትቶ ለመጫወት እንደሚመርጥ ነው።

እንደ ኤድዋርድ አባባል አንድ ሰው የምግብ ቤት አስተናጋጅ ሆኖ እየሠራ የጠፈር መርከብ ካፒቴን መሆን ከቻለ የቪዲዮ ጨዋታን ዓለም መምረጡ የሚያስገርም ሊሆን አይችልም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ በ2016 አራት የምጣኔ ሃብት አጥኚዎች አሜሪካ ውስጥ ባደረጉት ጥናት አስገራሚ ውጤት ላይ ደርሰው ነበር። በወቅቱ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገና የሥራ አጥነት መጠን በቀነሰበት ጊዜ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ወጣት ወንዶች ከመደበኛ ሥራ ይልቅ የትርፍ ጊዜ ሥራን አሊያ ደግሞ ያለ ሥራ መቀመጥን ይመርጡ ነበሩ።

ኢኮኖሚስቶቹን ይበልጥ ያሰደመመው ደግሞ በበርካታ ሥራ አጥ ሰዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደስታ የራቃቸው መሆናቸውን ቢሆንም፤ በተቃራኒው እነዚህ ወጣቶች ግን እጅግ ደስተኛ መሆናቸው ነበር።

አጥኚዎቹ በመደምደሚያቸው፤ እነዚህ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ ገቢያቸውንም እየተጋሩ በቪዲዮ ጨዋታዎች ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ወጣቶቹ አስተናጋጅ ሆኖ ከመሥራት ይልቅ፤ በቪዲዮ ጨዋታ ላይ ያለውን የምናብ ዓለም የጠፈር መርከብ ካፒቴን መሆንን መምረጣቸው ነው።