የከተሜን ህይወት ቀላል ለማድረግ ጤፍን ፈጭቶ መሸጥ!

ቃልኪዳን በለጠ

ቃልኪዳን በለጠ ከጥቂት ወራት በፊት ሥራ የጀመረው አነስተኛ የንግድ ድርጅቷ ጤፍን እየፈጨ በ5፣ በ10 እና በ25 ኪሎዎች ለተጠቃሚዎች እያደርሰ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት ከከተማ የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ጋር በተያያዘ ልዩ ልዩ የባልትና ውጤቶችን በተለያዩ መጠኖች አዘጋጅቶና አሽጎ መሸጥ እየተለመደ መጥቷል። ይሁንና ይህ ልማድ ለአያሌ ዘመናት ዐብይ ዕለታዊ ምግብ ሆኖ እስከዛሬ በዘለቀው ጤፍ ላይ እምብዛም ሲተገበር አይታይም ነበር።

በተለምዶ ጤፍ በጥሬውና በብዛት የሚሸመት በመሆኑ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ሰዎች አስቸጋሪ ነው የምትለው ቃልኪዳን፤ ይዛ የቀረበችው ምርት በገንዘብ እንዲሁም በጊዜ ላይ የሚፈጠርን ጫና የሚቀርፍ አማራጭ እንደሆነ ታምናለች።

ከሁለት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተመረቀችበት የሙያ ዘርፍ ጋዜጠኛነት ቢሆንም አሁን ስምንት ሰራተኞች ያሉትን ሮያል ባልትና ብላ የሰየመችውን አነስተኛ የንግድ ድርጅት ትመራለች።

በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተፈላጊ የሆነውን ጤፍ አዘጋጅቶና መጥኖ ማቅረብ ዘመናዊ ሕይወትን የማቀላጠፍ ሚና ይኖረዋል ትላለች ቃልኪዳን። ''ገብያ ድረስ ሄጄ ጤፍ መግዛት ወይም ወፍጮ ቤት በመሄድ ጊዜዬን ማባከን አልፈልግም፤ ለዛም ነው የከተማው ሰው ከመደብሮች ውስጥ ሳሙና ወይም ዘይት ገዝተው እንደሚሄዱት ሁሉ ጤፍንም በሚፈልጉት መጠን እንዲያገኙ እድሉን የፈጠርኩት'' ብላለች።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የከተሜን ህይወት ቀላል ለማድረግ ጤፍን ፈጭቶ መሸጥ!

ቃልኪዳን የመሰረተችው ዓይነት ምርትን የሚያቀርቡ ድርጅቶች መስፋፋት ዋነኛው ትሩፋት ተጠያቂነት ነው ትላለች። ''ይህም ተጠቃሚዎች በሚገዟቸው የምግብ ምርቶች ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ያደርጋል። እኔም ለማቀርበው ምርት ጥራት ሃላፊነቱን እወስዳለሁ'' ስትል ጨምራ ተናግራለች። ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ጤፍን በሚፈጩበት ወቅት ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለዋል የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ያጋጥሟት ችግሮች

''ሥራውን በጀመርኩበት ጊዜ የጤፍን አይነቶችን ለይቼ ለማወቅ እቸገር ነበር። ከዚህ በላይ ግን ከብዶኝ የነበርው ከጤፍ ደላሎች ጋር አብሮ መስራት ነበር። ለዚህ ችግር መፍትሄ ያደረኩት ደግሞ ጥሩ የጤፍ አቅርቦት በሚገኝባቸውን ቦታዎች፤ አነስተኛ መጋዘኖችን ተከራይቼ በቀጥታ ከገበሬዎች ጤፉን በመግዛት አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ ወደ አዲስ አበባ አጓጉዛለሁ'' ትላለች።

ቃልኪዳን ለጀማሪ ድርጅቷ ትልቅ እቅድ አላት፤ ''ጤፍ ከኢትዮጵያ ውጪም ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ፤ ይህ ለእኔ የንግድ ሥራ መልካም አጋጣሚ ነው። እድሉ ከተመቻቸም በአጭር ጊዜ ውስጥ የጤፍ ዱቄትን ወደ ውጪ የመላክ እቅድ አለኝ'' ስትል ትናገራለች።

ልዕለ-፥ምግብ

ጤፍ በውስጡ በያዛቸው ጤናማ ንጥረ ነገሮች ምክንያት በብዙ ቦታዎች ተመራጭ እየሆነ ነው። ተወዳጅነቱ በአንድ በኩል ግሉተን ከሚባለው ንጥረ ነገር ነፃ በመሆኑ እንዲሁም በፕሮቲን እና በካልሲዬም ከመበልጸጉ የሚመነጭ ነው። አንዳንዶች እንዲያውም "አዲሱ ልዕል-ምግብ" እያሉ ያወድሱት ይዘዋል። በዚህም ምክንያት እንጀራ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች እየታወቀ ነው።

ይሁንና ከባህልና በዘመናት ከዳበረ ልምድ በመነሳት በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንጀራን ከመግዛት ይልቅ በቤት ውስጥ ጋግሮ መጠቀምን ይመርጣሉ። ስለዚህ ጤፍን ገዝቶ፣ አዘጋጅቶ፣ አስስፈጭቶና ጋግሮ አስከ ማቅረቡ ድረስ ያለው ከባድ ሃላፊነት በሴቶች ትከሻ ላይ ይወድቃል። ቃልኪዳን በጀመረችው ሥራ በርካታ ሴቶች ጤፍን ለምግብ በማዘጋጀት በኩል ያለባቸውን የሥራ ጫና በግማሽ ሊቀንስ ይችላል ብላ ታምናለች።