"ሁሉም ሴቶች ከጥቃት ውጭ አይደሉም! "

የተደፈረች ህፃን የልጇን እጅ ይዛ
የምስሉ መግለጫ,

የተደፈረች ህፃን የልጇን እጅ ይዛ

"ምናለበት እንደ ህፃን ልጅ ቢያየኝ ኖሮ? የመማርና የማወቅ ህልሜን ባያጨልመዉ? መጪዉን ህይወቴን ነዉ የነጠቀኝ።" በማለት የምትናገረዉ ዘቢባ እንድሪስ* እድሜዋ 16 ሲሆን በእህቷ ባል ከአንድ ዓመት በፊት አሰቃቂ የሆነ የወሲብ ጥቃት ደርሶባታል።

በደረሰባት ጉዳት ፈገግታዋን፣ የልጅነት ነፃነቷን የተነጠቀችዉ ዘቢባ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በህፃንነቷ የልጅ እናት ሆናለች።

ይህንንም ሁኔታ መረር ባለ ቃል እንዲህ ትገልፀዋለች "ልጅ ፀጋ ነዉ ሲሉ እሰማለሁ፤ ልጅ በልጅነት ሸክም ነዉ እንጂ እንዴት ፀጋ ይሆናል? "

የተወለደችበትን መንደር ብትናገር በቤተሰቦቿ ላይ ሃፍረት አመጣለሁ ብላ የምታምነዉ ዘቢባ ከደቡብ አካባቢ እንደመጣች ትናገራለች።

አጥቂዉን ሳይሆን ተጠቂዎችን ማሳፈርና ማውገዝ በተለመደባት ቦታ፤ ዘቢባ ብቻ ሳትሆን ጥቃት የደረሰባቸዉ ህፃናትም ይሁኑ አዋቂ ሴቶች በሚደፈሩበት ወቅት ክብራቸዉን እንዳዋረዱ ይሰማቸዋል። የዘቢባም ስሜት ከዚህ የተለየ አይደለም።

ሀገሯ በነበረችበት ወቅት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የነበረችዉ ዘቢባ ድንገተኛ የሆነ የማያቋርጥ መንቀጥቀጥ እና የጀርባ ህመም ስለተሰማት ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች።

ለህክምናም እንዲሁም ትምህርቷን ለመቀጠል ትችል ዘንድ ታላቅ እህቷ ወደምትኖርበት አዲስአበባ መጣች።

እህቷ የተለያዩ ግለሰቦች ቤት እየተዘዋወረች ልብስ በማጠብ እና ድንች ጠብሳ በመሸጥ የምተዳደር ሲሆን ወደቤትም የምትመጣዉ መሸትሸት አድርጋ ነዉ።

ዘቢባ ቀኑን የእህቷን ልጅ በመጠበቅ እንዲሁም የቤት ሥራዎችን በመስራት ታሳልፋለች።

ሲያማት ተኝታ ብታሳልፍም መፅሀፎቿን ማየትና ማንበብ አላቋረጠችም። ዘቢባ ጀርባዋ እስኪጎብጥ ድረስ እበት እየዛቀች ያሳደጋቻትን የእናቷን ህይወት ለመቀየር ዋነኛ ህልሟ የህክምና ዶክተር መሆን ነበር።

ያንን ህልሟን የሚያጨልም ጉዳይ የተከሰተዉ አንድ ቀን ተኝታ በነበረችበት ወቅት ነዉ።

ከእህቷ ጋር በመጋረጃ በተከፈለ አንድ ጠባብ ቤት ዉስጥ በጋራ የሚኖሩ ሲሆን፤ ባልና ሚስቱ አልጋ ላይ ሲተኙ እሷ ደግሞ ፍራሿን አንጥፋ ትተኛለች።

የእህቷ ባል ቀድሞ ከሥራ የሚገባ ሲሆን ብዙ ጊዜ ከትንሽ ቃላት ውጭ ምንም ተባብለዉ እንደማያዉቁ ዘቢባ ታስታውሳለች።

በአንደኛዋ ቀን ግን አንድ ሰዓት አመሻሹ ላይ ጀርባዋን ከፍተኛ ህመም ተሰምቷት ጋደም ባለችበት ወቅት በቢላ አስፈራርቶ እንደደፈራት ትናገራለች። ለሌላ ሰው ትንፍሽ ብትል እንደሚገድላትም ጭምር ነበር የነገራት።

"እሱ ስላስፈራራኝ ብቻ ሳይሆን የእህቴን ህይወትም መበጥበጥም ስለማልፈልግ ለማንም መንገር አልፈለኩም" ትላለች።

ከዚያ ትንንሽ እጆቿን እያፋተገችና እንባዋ በጉንጮቿ ላይ እየወረደና ሳግ እየተናነቃት "ብዙ ደም እየፈሰሰኝ ነበር። ደሜን ጠራርጌ ወደየት እንደምሄድ ሳላዉቅ ወደ መንገድ እያለቀስኩ ወጣሁ" መንገድ ላይ አይዞሽ ያላትም ሰው አልነበረም።

ለምን ያህል ሰዓት መንገድ ላይ እንደቆየችም አላወቀችም ደንዝዛ ቆማ ባለችበት ጊዜ እህቷ ከሥራ ስትመለስ ተገናኙ።

የምስሉ መግለጫ,

ብዙ የተደፈሩ ህፃናት ለእርግዝና ይዳረጋሉ

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ

መንገድ ላይ ምን እየሰራች እንደሆነ ስትጠይቃት "አይ ትንሽ አሞኝ ነዉ" በማለት መለሰችላት እህቷም ምንም አልጠረጠረችም፤ ህይወትም በዛው ቀጠለ። አንድ ቀን ውሀ በቤት ውስጥ ስላልነበር ቀድታ ስትመለስ ወድቃ የጎን አጥንቷ ስለተጎዳ እህቷ ወደ ሆስፒታል ወሰደቻት።

ከዚህ ጉዳቷ በተጨማሪ የሰባት ወር እርጉዝ መሆኗን በምርመራ ወቅት በመታወቁ የዶክተሩ የመጀመሪያ ጥርጣሬ የቤት ዉስጥ ሰራተኛ መስላዉ ነበር። ዶክተሩም እህቷን አስጠርቶ እርጉዝ መሆኗን በተናገረበት ጊዜ ነበር ምን እንደደረሰባት ለመንገር የተገደደችዉ።

ጉዳዩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተመራ፤ ህይወት ሙሉ በሙሉ የጨለመባት በመሰላት ወቅት ለተደፈሩ ሴቶች መጠለያ ወደሆነዉ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር በሰዎች ትብብር የመጣችዉ።

የደፈራት ግለሰብ ምን ያህል ዓመት እንደተፈረደበት ባትሰማም እንደታሰረ አውቃለች።ከእስሩ በላይ ያስደሰታት ነገር ቢኖር እህቷ ለእሷ የሰጠቻት ድጋፍ ነወ።

"ከጎኔ መሆን ብቻ ሳይሆን የእኔ ደፋሪ ከሆነ ሰዉ ጋር፤ ልጅነቴን ከቀማኝ ሰዉ ጋር ትዳር ብላ አለመቀጠሏ ሁሉ ነገር ጨለማ አለመሆኑን ያሳየኝ ጉዳይ ነው" ትላለች ዘቢባ።

ሰዎችን ቀና ብላ ለማየት ብዙም የማትደፍረው ዘቢባ መጠለያው ዉስጥ ከመጣችበት ጊዜ ጀምሮ ህይወቷ እንደተቀየረ ትናገራለች። "እርጉዝ በነበርኩበት ወቅት ራሴን ከሰዎች በታች ነበር የማየዉ ማድረግ የምችለው ማልቀስ ብቻ ነበር" በማለት ዘቢባ እያለቀሰች ትናገራለች።

የምስሉ መግለጫ,

የተደፈረች ህፃን ልጅ በፖሊስ እርዳታ ወደ መጠለያው ስትወሰድ

ያንሰራራ ተስፋ

በመጠለያው ቆይታቸው በምግብ ሥራ፣ በልብስ ስፌት፣ በፀጉር ሥራ፣ በቀርከሃና በጣዉላ ሥራዎች የተለያዩ ስልጠናዎች መዉሰድ የሚችሉ ሲሆን ዘቢባም የፀጉር ሥራ ስልጠናን እየወሰደች ነው። "ይሄንን ቤት ፈጣሪ እንዳዘጋጀልኝ ነው የምቆጥረው" ትላለች ዘቢባ።

አሁን ያለችበት ቦታ ለመድረስ ግን በማዕከሉ ውስጥ በተለያዩ የምክር አገልግሎት ማለፍ ነበረባት።

የማዕከሉ የስነልቦና አማካሪዎች በደረሰባት ጥቃት ደፋሪዋ የእሷን ክብር ሳይሆን ራሱ እንደተዋረደ፤ ከልጇም ጋር ባላት ግንኙነት ዙሪያና የወደፊት ህይወቷንም በተስፋ እንድታየው አግዘዋታል።

"ምንም እንኳን በወራት ውስጥ ማልቀሴ እየቀነሰና ጓዋደኞችም ስላፈራሁ መሻሻል ባሳይም አሁንም ብቸኝነቱና ተስፋ መቁረጡ አለ" ትላለች።

በዚህ መጠለያ ከሚገኙት ውስጥ ዘቢባ ብቸኛዋ አይደለችም።

የጭካኔ በትር

የ13 ዓመት እድሜ ያላት ማስተዋልም ከመጣች ስምንት ወሯ ሲሆን፤ የተደፈረችዉ ጎረቤት ከብት ለማገድና ለአንዳንድ ሥራዎች በተቀጠረ ግለሰብ ነው።

እንጨት ለመልቀም በምትሄድበት ወቅት በለበሰችው የአንገት ልብስ አፍኖ እንደደፈራት ፈራ ተባ በማለት ትናገራለች።

ይሄንን የሚሰቀጥጥ ሁኔታ የዘጠኝ ዓመት እህቷ ተመልክታለች። "ለሰዓታት ራሴን ስቼ ነበር። በኋላ እህቴ ነች ያነቃችኝ" ትላለች ማስተዋል።

ማስተዋልም ለአሳዳጊ አያቶቿ የገጠማትን ትንፍሽ ማለት አልፈለገችም። "በደም የተበላሸውን ልብስ እንዳያዩት ደበቅኩት፤ ምክንያቱም የኔ ጥፋትና አውቄ እንዳደረኩት ነው የሚያስቡት። እናም በህይወት መኖር አልፈለኩም። ለታናሽ እህቴ ስል ነው በህይወት የቆየሁት" በማለት ፊቷን በእጇ ሸፍና በማልቀስ ትናገራለች።

ነገሩ የታወቀው የማያስቆም የማያስቀምጥ ህመም ማህፀኗ አካባቢ ሲሰማት ታናሽ እህቷ ለአያቷ ተናግራ ጉዳዩንም ህግ እንዲይዘው ተደረገ።

የማስተዋል የአካል ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም ጥቃት አድራሹ ከትንሽ ጊዜ እስር በኋላ ተለቀቀ። ይሄ ጉዳይ ለማስተዋል ግልፅ አልሆነላትም። "ፍርድ ቤት የሚረዱ መስሎኝ ነበር እነሱ ግን ምንም አልመሰላቸውም" በማለት ተስፋ የቀረጠችበትን ሁኔታ ትገልጻለች።

ጉዳዩ በሰፈሯ ከተሰማም በኋላ የሰፈሩ ህፃናት መሳቂያ መሳለቂያ አደረጉዋት።

የደፈራትም ሰው መተናኮሉን ቀጥሎ አያቶቿንም መሳደብ እንዲሁም እንደመታት ትናገራለች።

ትምህርቷን ለመቀጠል ከብዷት በነበረበት ጊዜ ነበር አክስቷ ወደዚህ መጠለያ ያመጣቻት።

እዚህ ከመጣች በኋላ ለወደፊቱ የምታልመው ፖሊስ የመሆን ተስፋዋ ቢያንሰራራም አሁንም የታናሽ እህቷን ጉዳይ ስታስብ ጭንቅ ይላታል። "እስከዛሬ የሚያስቀምጧትም አይመስለኝም" ትላለች እንባ እየተናነቃት።

ለማመን በሚከብድ ሁኔታ በጭካኔ ቆሳስለው፤ አንዳንዶቹም ፊታቸው በእሳት ተጠብሶ ነው ወደዚህ መጠለያ የሚመጡት።

የምስሉ መግለጫ,

የተደፈሩ ሴቶች ስልጠና ሲወስዱ

ብሩህ ተስፋ

በዚህ መጠለያ ውስጥ መስማት የሚከብዱና ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ታሪኮች ቢኖሩም በስቃይ ውስጥ አልፈው ነገን ለመኖር በተስፋ ሲያልሙ ማየት የሚገርም ነው።

ቤተሰቦቿ ገና በስድስት ዓመቷ ሞተውባት በሰው ቤት ስትንከራተት የአሰሪዋ ልጅ በጩቤ አስፈራርቶ የደፈራት የ14 ዓመት እድሜ ያላት መሰረት፤ የምታስበው ህፃናት እንዴት እንዳይደፈሩ ማድረግ ይቻላል የሚለው መፍትሄ ላይ ነው።

"ሁሉም ሴቶች ከጥቃት ውጭ አይደሉም" የሚል እምነት ያላት መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን የሚያረጋግጥ ነገር አይታለች።

ይህ መጠለያ ከ14 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በተወጣጡ አምስት ሴቶች እንደተጀመረ የሚናገረው የድርጅቱ የፕሮግራም አስተባባሪ ግሩም አለማየሁ፤ ፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ማህበር ተብሎ እንደተመሰረተ ይናገራል።

የዚህ ሀሳብ መነሻ የሆነው የተደፈሩ ህፃናትና ሴቶች ወደ ክስ ካመሩ በኋላ በተደጋጋሚ ጥቃት በመድረሱ፤ እንዲሁም በቤተሰብ የሚደፈሩ ህፃናት ጉዳዩ ወደ ክስ ከሄደ በኋላ ቤታቸው ተመልሰው መሄድ ስለማይችሉ ይሄ መጠለያ ማረፍያ እንዲሆን ታስቦ ተሰራ።

መጠለያው ምግብ ማደሪያ የምክር አገልግሎት የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣል።

ከዚህም በተጨማሪ በሁለት የተከፈለ የትምህርት ፕሮግራምም አለ። የመጀመሪያው አጠቃላይ ትምህርት የሚሰጥበት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በቤተሰብ የተደፈሩና ትምህርታቸውን ቤታቸው ሆነው መከታተል ለማይችሉ ሴቶች ዩኒቨርስቲ እስኪጨርሱ ድረስ ድጋፍ የሚሰጥበት ነው።

ከአዲስ አበባው መጠለያ በተጨማሪ በአዳማ ከተማ እንዲሁም በሃዋሳ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ የማረፍያ አገልግሎት ይሰጣቸዋል። በአጠቃላይም ከ1500 በላይ ለሆኑ ሴቶችም መጠለያ ነው።

አቶ ግሩም እንደሚገልፁት መቀበል ከሚችሉት በላይ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ስለሚመጡ ከአልጋ በተጨማሪ ፍራሽ በማንጠፍ ይቀበሏቸዋል።

ምንም እንኳን አንዲት ሴት በአማካኝ ለሶስት ወራት ትቆያለች ብለው ቢያስቡም፤ አቶ ግሩም እንደሚሉት ብዙዎቹ ወልደው ስለሚመጡ ታርሰው እንዲሁም ልጆቻቸውን እስኪጠነክሩ ድረስ እስከ ሁለት ዓመት የሚቆዩበት ጊዜ አለ።

ቆይታቸውን ከጨረሱ በኋላ የሶስት ወር የቤት ኪራይና በቀጣዩ ለሚሰሩት ሥራ መነሻ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።

በዓመታትም ውስጥ ብዙ ሴቶች ተስፋቸው አንሰራርቶ ከወጡ በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ያለው ውጣ ውረድ ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ የሚናገረው አቶ ግሩም ይህ መጠለያ አዲስ ህይወት እንደሚሰጣቸው ግን አይጠራጠርም።

*የጥቃት ሰለባዎቹ ስም ለደህንነታቸው ሲባል ተቀይሯል።