በሰዎች ይዞታ ሥር የቆዩ የዱር እንስሳት ታሪክ

በርካታ የዱር አራዊትና አዕዋፍ ከተፈጥሯዊው የመኖሪያ ሥፍራቸው ተለይተው እየተወሰዱ ለጉዳት በሚያጋልጣቸው ሁኔታ እንዲቀመጡ ማድረግ የወንጀል ድርጊት ነው።

ከዚህ ሲከፋ ደግሞ በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር እንዲወጡ ይደረጋል። በተለይ ደግሞ በድብቅ ከሃገር ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት እንስሳቱ ለሞት ይዳረጋሉ።

የሃገሪቱን ህግ በተጻረረ መልኩ ከአዕዋፍ እስከ አንበሳ ድረስ በግለሰቦች እጅ ተይዘው ለስቃይና ለጉዳት ይዳረጋሉ። አንበሳ ደግሞ ከፍተኛ ስቃይ ከሚደርስባቸው እንስሳት መካከል አንዱ ነው።

በረከት ግርማ ሆለታ ከተማ የሚገኘው፤ የቦርን ፍሪ በጎ አድራጎት ድርጅት የሚያስተዳድረው 'እንስሳ ኮቴ' ተብሎ የሚጠራው ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ነው።

ይህ ማዕከል በከፋ አያያዝ ለተጎሳቆሉና ለተጎዱ የዱር እንስሳት ክብካቤ ያደርጋል። በረከት ማዕከሉን ባስጎበኘን ወቅት ከግለሰቦች እጅና ከህገ-ወጥ የእንስሳት አዘዋዋሪዎች የታደጓቸውን በርካታ የዱር አራዊትና አዕዋፍ አሳይቶናል።

በጣቢያው ውስጥ የሚገኙት ሁሉም እንስሳት የራሳቸው የሆነ አስደናቂ ታሪክ አላቸው።

ዶሎ

ወደ ማዕከሉ ሲያመሩ በመጀመሪያ ሊመለከቷቸው ከሚችሏቸው እንስሳት መካከል አንበሳው ዶሎ አንዱ ነው።

ዶሎ በሱማሌ ክልል ዶሎ አዶ በሚባል ስፍራ በአንድ ሜትር ሰንሰለት ታስሮ በጨለማ ክፍል ውስጥ 4 ዓመታትን አሳልፏል። ለረጅም ዓመታት በጨለማ ክፍል ውስጥ ታስሮ መቀመጡ ዶሎን ለዓይነ ስውርነት ዳርጎታል።

በረከት እንደነገረን ግለሰቦቹ ዶሎን ያገኙት በደቦልነቱ ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በአንገቱ ዙሪያ የታሰረው ሰንሰለትም ዶሎ እያደገ ሲሄድ አንገቱን ከመከርከሩ በላይ ቆዳውን አልፎ ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበታል።

Image copyright BornFreeEthiopia
አጭር የምስል መግለጫ ዶሎ በግለሰብ እጅ እያለ

ከዚህም በተጨማሪ ይዘውት የነበሩት ሰዎች ተገቢውን የምግብ ዓይነትና መጠን ከመስጠት ይልቅ ይመግቡት የነበረው ከሆቴል የሚገኝን የምግብ ትርፈራፊ ነበር። ይህም የሰውነቱ መጠኑን በእጅግ እንዲቀንስና ጎፈሩ እንዲራገፍ አድርጎት ነበር።

ወደ ማዕከሉ ከተወሰደ በኋላ ግን በተደረገለት ክብካቤ ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል።

Image copyright Berelet Girma
አጭር የምስል መግለጫ ዶሎ አሁን በማዕከሉ ውስጥ ተፈጥሯዊና ሰላማዊ በሆነ በተከለለ ቦታ ላይ ይገኛል

ሳፊያ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁደታ በተባለ በደቡብ ኢትዮጵያ ባለ ቦታ የአንበሳ ደቦል በሰንሰለት ታስራ በግለሰቦች እጅ ትገኛለች የሚል መረጃ ለቦርን ፍሪ ማዕከል ይደርሳል።

የማዕከሉ ሰራተኞች ወደ ተባለው አካባቢ ሲደርሱም ሳፊያ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ በስንሰለት ታስራ በልጆች በተወረወረ ድንጋይ የፊት እግሯ ተሰብሮ አገኟት።

ሳፊያ በወቅቱ 27 ኪ.ግ ብቻ ነበር የምትመዝነው። በቦርን ፍሪ አማካኘነት በተደረገላት ክብካቤ ዛሬ ላይ ከዶሎ ጋር በእንስሳ ኮቴ ማዕከል ውስጥ በተከለለላቸው ተፍጥሯዊ ቦታ እየኖሩ ይገኛሉ።

Image copyright BornFreeEthiopia

አንድሪያና ጃኖ

አንድሪያ እና ጃኖ የተባሉት ወንድማማች አንበሶች ከብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መልካም ፍቃድ ወደ ጣቢያው የመጡ ናቸው።

በረከት እንደነገረን አንዲሪያ እና ጃኖን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በእንስሳ ኮቴ የሚገኙት አንበሶች በሰዎች ቁጥጥር ሥር ለበርካታ ዓመታት ስለቆዩ ወደ ዱር ተመልስው ለመኖር ይከብዳቸዋል።

ስለዚህ በተቻለ መጠን ከስው ጋር ቀጥተኛ ግንኘነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ተፈጥሯዊ በሚመስል የተከለለ የመኖሪያ አካባቢ ላይ እንዲኖሩ ይደረጋል ብሏል።

አቦ ሸማኔዎች

አዕዋፍና የዱር አራዊት ተፈጥሮ በሰጠቻቸው የመኖሪያ ቦታቸው ላይ ሳይረበሹ የመኖር መብታቸውን ማንም ሊጋፋቸው አይገባም! የሚለው በረከት በእንስሳኮቴ ማዕከል ውስት የሚገኙትንም አቦ ሸማኔዎች አስጎብኘቶናል።

ከበረከት እንደሰማነው አቦ ሸማኔዎች ከሌሎች የዱር እንስሳት በተለየ መልኩ እንደ የቤት እንስሳት ሊላመዱ ይችላሉ። ይህ ተፍጥሯዊ ባህሪያቸው በአረብ ሃገራት በሚገኙ ከበርቴዎች ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዲኖራቸው አድርጓል።

ስለዚህም እንስሳቱ የህገ-ወጥ የእንስሳት አዘዋዋሪዎች ኢላማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በእንስሳ ኮቴ ማዕከል ውስጥ 11 አቦሸማኔዎች ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል ህገ-ወጥ የእንስሳት አዘዋዋሪዎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲያጓጉዟቸው ድንበር ላይ የተያዙ ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ወደ ሶማሌላንድ በሚጓዙ ተሸከርካሪዎች ላይ በሚደረጉ ፍተሻዎች የተገኙ አቦሸማኔዎችም አሉ።

አጭር የምስል መግለጫ በረከት ግርማ

በየጊዜው በህጋዊና ህገወጥ በሆነ አደን ምክንያት በሰዎች የሚገደሉት የዱር አራዊትና አዕዋፍ ስፍር ቁጥር የላቸውም፤ የሚለው በረከት እንስሳትን የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነት የሁሉም መሆን አለበት ይላል።

የቦርን ፍሪ የእንስሳት መንከባከቢያ ማዕከል የሆነው እንስሳ ኮቴ ለጉዳት ለተጋለጡ የዱር አራዊትና አዕዋፍ መጠለያና ማገገሚያ በመሆን እጁ የገቡትን እንስሳት እየታደገ ይገኛል።

ተያያዥ ርዕሶች