ሳንሱርን ተቋቁሞ ማለፍ የቻለ የሙዚቃ ጉዞ

አንዳንድ ዘፈኖች ቋንቋን ድንበርን አልፈው የመደመጥ ችሎታ አላቸው። ከነዚህ ዘፈኖች አንዱ የባህታ ገብረሕይወት የሆነው "ስቓይ ዝከኣል 'ዩ ኩልጊዜ፤ ናይ ፍቕሪ ስቓይ ግን ዘይከኣል እዩ" የሚለው ነው። መቼም ቢሆን ስቃይ ይቻላል፤ የፍቅር ስቃይ ግን የማይቻል ነው የሚል ትርጉም ያለው ይህ ሙዚቃ ትግርኛ ተናጋሪዎች ባልሆኑ ሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ተደማጭነትንና ተወዳጅነትን ለማትረፍ ችሏል። የሙዚቃ ሕይወታቸውን ለማውራት ከአምስት አስርት አመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የመድረክ ሥራቸውን 'ሀ' ብለው ወደ ጀመሩበት ራስ ሆቴል አመራን።

አጭር የምስል መግለጫ ባህታ ገብረህይወት የቀድሞ ፎቶዎችን በማገላበጥ

መዝፈን የጀመሩት በአማርኛ ቋንቋ ነበር "ለነገሩ በወቅቱ የአማርኛ ዘፋኝ ነበር የሚፈለገው" ይላሉ በዓዲ ግራት ከተማ ተወልደው ያደጉት ባህታ። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በጎንደር የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከገባደዱ በኋላ ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ አደረጉ። የተመረቁበትን የጤና ትምህርት ወደጎን በመተው ልባቸው ያዘነበለበትን የሙዚቃ ሕይወት መከተል ፈለጉ። በዚያን ጊዜ ለራስ ባንድ የዘፋኝ ቅጥር ማስታወቅያ መውጣቱ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ። በጊዜው በርካታ አመልካቾች ቢኖሩም ፈተናውን ግን እሳቸው አለፉ። ከእርሳቸውም ጋር በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ አሻራን መጣል ከቻሉ ሰዎች መካከል እንደነ ግርማ በየነ የመሳሰሉ ሙዚቀኞች ነበሩበት።

ሙዚቃ የጀመሩበትን ጊዜ ወደ ኋላ ሲያስታውሱ ለመጀመርያ ጊዜ መድረክ ላይ ያዜሟትን "የፍቅርን እንጎቻ ጣፍጦን ስንበላ… በቃኝ ትይ ይሆናል አንቺም እንደሌላ" የምትለውን ዘፈን አይረሷትም። ባህታ ከፍተኛ የሆነ የመዝፈን ፍላጎት ይኑራቸው እንጂ ሙዚቀኛ ሆኖ የመኖር ሃሳቡ ግን አልነበራቸዉም። ምንም እንኳን በሰለጠኑበት የህከምና ትምህርት ባይሰሩበትም የሂሳብ አያያዝ ትምህርትን በንግድ ሥራ ኮሌጅ ተከታትለዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ ቀደምት ዘፋኞች መካከል ከሆኑት አንዱ የሆኑት ባህታ ከድምፃዊነት በተጨማሪ ግጥምና ዜማም ራሳቸው እንደሚሰሩ ይናገራሉ።

በተለይም በኢትዮጵያ ታሪክ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ለተጫወተው የሮሃ ባንድም ባህታ አንደኛው ሙዚቀኛ ነበሩ። ምንም እንኳን ከሮሃ ባንድ በፊት ራስ፣ ዋልያስ፣ ሶል ኤክስ የሚባሉ ባንዶች ቢኖሩም ሮሃ ግን የደርግ ጊዜን ቅድመ ምርመራን (ሳንሱር) ተቋቁሞ ለብዙ ዓመታት መዝለቅ የቻለ ባንድ እንደሆነ ባህታ ይናገራሉ። በቅድመ ምርመራ ወቅት ሙዚቃ መስራት በጣም አስቸጋሪ እንደነበር የሚናገሩት ባህታ "በማስታወቂያ ሚኒስቴር የቅድመ ምርመራ ክፍል የአንድ ዘፈን ከላይ የሚነበበው ግጥም ብቻ ሳይሆን ምን አይነት ድብቅ ትርጉም አለው በሚል ሳይቀር ይፈተሻል፤ ይጣራል።" በማለት ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት፤ በርካታ ዘፈኖች ፖለቲካዊ ትርጉም እየተሰጣቸው ሳይወጡ መቅረታቸውንም በቁጭት ይናገራሉ። በተለይ ከቀደምት ሥራዎቻቸው መካከል "ፅመድ ብዕራይ" (ጥመድ በሬ) የሚለውን "ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?" በሚል ከፍተኛ ጥያቄ ተነስቶባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ጥመድ በሬ የሚል የአማርኛ ትርጉም ቢኖረውም ለሳንሱር ሲቀርብ እረስ በሬ በሚል ትርጉም ነው የቀረበላቸው። " እያንዳንዱ ግጥም ሰምና ወርቅ ነበረው። ሰሙ በአማርኛ ተተርጉሞ ለሳንሱር ይቀርባል፤ ያልፋልም። ወርቁ ወይም ድብቅ ትርጉም ያለው ግጥምም በዚህ መልኩ ያልፋል።" በማለት ይናገራሉ።

በተለይም ትግርኛ መዝፈን በጀመሩበት ወቅት ነገሮች ቀላል እንዳልሆኑ ከመረዳታቸውም በላይ የተለያዩ ተንኮሎች የእንደሚፈፀሙ ተገነዘቡ። ይህንንም ሁኔታ እንዲህ በማለት ያስረዳሉ "በዚያን ጊዜ ውስጥ ነው አይን ውስጥ መግባት የጀመርኩት። እያንዳንዷን ነገር እንዴት መወጣት እንዳለብኝ ብልሃት ነበረኝ" ይላሉ።

ብዘዎች ግጥሞቻቸው የፖለቲካዊ ትርጉም እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ባህታ፤ በዚህም ምክንያት ለእስርና ለስቃይ ተዳርገዋል። በተጨማሪም ፍርሃቱና መብሰክሰኩ የብዙዎችን ሙያ ያቀጨጨ ጉዳይ ነው በማለት የሚናገሩት ባህታ "የበርካቶችን ፈጠራና ብቃትም ገድሏል" ይላሉ። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድም ሆኖ በወቅቱ ለህዝብ ሲቀርቡ የነበሩት የሙዚቃ ሥራዎች ብስለትና ጥራት ያላቸው እንደነበሩ በአፅንኦት ይናገራሉ።

የግጥሞቹ መነሻቸው በየእለቱ ከሚያጋጥማቸው ጉዳዮችንም ይዳስሳል። ከዚሀም ውስጥ አነዱ "በተለየ ፍቅር ልቤ ተመርዞ፤ እጅግ ደስ ይለኛል ወደ ሐረር ጉዞ" ብለው የዘፈኑት ዘፈን መነሻው ሐረር ሄደው በፍቅር መጠመዳቸው እንደነበርም አልሸሸጉም። ባህታ ከሙዚቀኝነታተቸው በተጨማሪ ታጋይም ነበሩ። የዚህም መነሻ የሆነው አንድ ቀን ከአዲስ ኣባባ ወደ ዓዲግራት በመጓዝ ላይ እያሉ መቐለ ላይ ሸጉጥ ይዘው በመገኘታቸው ይታሰራሉ። በዋስ ከእስር ቢለቀቁም በቀጥታ ወደ በርሀ ለመውጣት እንደወሰኑ ይናገራሉ። ይሄንንም ተከትሎ 1968 ዓ/ም በወቅቱ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ከነበረው ህወሓት ጋር ተቀላቀሉ። በትግል ቆይታቸውም የድርጅቱ የባህል ቡድን ኣባል ሆነውም ነበሩ። በትግል ዘፈኑም እንደነ ንግሰት ሓየሎም ከመሳሰሉ ሙዚቀኞች ጋር በጋራ ሰርተዋል። እሳቸው ሲሰሩበት የነበረ የባህል ቡድን ግልፅ ባልሆነ ምክንያት መፍረሱን ተከትሎ ወደ መደበኛ የትጥቅ ትግል ተመልሰው ገብተዋል።

"ኢድዩ ጋር በተደረገ ውጊያ ተሳትፌያለሁ።" ይላሉ ባህታ ነገር ግን በትግል ውስጥ ብዙም አልቆዩም "አንዳንድ ችግሮች ስለነበሩብኝ ትግሉን ተሰናብቼ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ።'' ቢሆንም ግን የሙዚቃ ሙያቸውን ተመልሰው አልቀጠሉበትም። በአገር ፍቅር ቲያትር በሂሳብ አያያዝ ሙያ ተቀጥረው መስራትም ጀመሩ።

ሙዚቃ ውስጥ የነበሩበት ጊዜ ወርቃማ እንደነበር የሚያምኑት ባህታ የድሮ ዘፋኞች ሆነ ሥራቸው በሳልና አርቆ ኣሳቢ አንደነበሩ ያምናሉ። "በወቅቱ የነበረውን አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ተቋቁመው፤ በፍቅር አስመስለው ብዙ መልዕክት ያለው ሥራን መስራታም ችለዋል። " ይላሉ።

ይሄም ቢሆን ይላሉ "በእርግጥ ዛሬም አንዳንድ ጎበዝ ሙዚቀኞች አሉ" በማለት ጥረታቸውን ያደንቃሉ። በተለይም የትግርኛ ዘፋኞችን በተመለከተ "ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት አርቲስቶች የመኖራቸውን ያህል፤ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሥራ ላይ የተጠመዱ ብዙ አርቲስቶች ደግሞ አሉ። " በማለት መረር ያለ ነቀፌታም ያሰማሉ። በተለይም ብዙ የተለፋበትን የቀደምት አርቲስቶችን ሥራ እንደገና የሚሰሩትን አጥብቀው ይቃወማሉ። "ድሪቶ ሙዚቃ በመስራት ላይ ናቸው። ይህ አስነዋሪ ነገር ነው።" በማለት በዚህ ላይ የተሰማሩ ዘፋኞች በተግባራቸው ሊያፍሩ እንደሚገባ ጨምረው ያስረዳሉ። ይህንንም ቅሬታችውን ለአንዳንድ ዘፋኞች ገልፀውላቸዋል። ባህታ "መዋስ ነውር ባይሆንም፤ ሌብነትን ግን መታገስ የለብንም" ይላሉ።

የዱሮ ሙዚቃዎችን እንዲህ ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ መሰራቱ የሳንሱርን ያህል ፈጠራንና ችሎታን የሚገድል አዝማምያ አለው ብለውም ያምናሉ። ሙዚቃ ሰሪዎችም ብቻ ሳይሆን አድማጮችም ይህንን ድርጊት ማበረታት እንደሌለባቸው ይናገራሉ። ቅድመ ምርመራን በተመለከተ ከበፊቱ ጋር ሲያነፃፅሩት በአሁኑ ወቅት የተሻለ መሆኑን እንዲሁም ደግሞ የተሟላ የሙዚቃ መሳርያ ያለበት ዘመን በመሆኑ እንደመልካም አጋጣሚ ይመለከቱታል።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩት ባህታ በ74 አመታቸውም አሁንም ጠንካራ ናቸው። የአምስት ልጆች አባትና የልጅ ልጆች ያሉዋቸው ባህታ እንደ ድሮው ባይሆን ዛሬም በአንዳንድ ትላልቅ መድረኮች ሙዚቃ ይጫወታሉ። " የሙዚቃ ፍቅር አይለቅም" በማለትም ይናገራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች