ፈታኝ የሚባለውን የቱር ደ ፍራንስ ውድድርን መጨረስ የቻለው ፅጋቡ

ፅጋቡ በመለመማመጃው ቦታ ላይ
አጭር የምስል መግለጫ ፅጋቡ በመለመማመጃው ቦታ ላይ

በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ አትሌቲክስ በተለይም ረዥም ሩጫ እና ኢትዯጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ነው የሚታዩት። በባለፈው ወር ግን ኢትዮጵያን ወክሎ የተወዳደረው ፅጋቡ ገብረማርያም በብስክሌት ውድድር ስሟን ሊያስነሳ ችሏል።

ብዘዎቹ ፈታኝ በሚሉትም አለም አቀፉ ቱር ደ ፍራንስም ሲወዳደር የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው።

ትግራይ የተወለደው ፅጋቡ የብስክሌት ፍቅር ያደረበት በልጅነቱ ሲሆን አባቱም አቶ ገብረማርያም ከ 1962 እስከ 1972 በአዲስ አበባ እና በአስመራ ከተሞች የብስክሌት ተወዳዳሪ ነበሩ። ቤተሰቡም ከብስክሌት ጋር የተዋወቀው በአባትየው ምክንያት እንደሆነ ፅጋቡ ይናገራል። ለቤተሰቦቹ ሰባተኛ ልጅ የሆነው ፅጋቡ በእግሩ መሄድ ሲጀምር ቤተሰቦቹ ብስክሌት እንዳለማመዱት ይናገራል። ከዚያ በኋላማ ብስክሌትንና ፅጋቡን የሚለያያቸው ታጣ። "ወደ ትምህርት ቤትም ስሄድም ይሁን እናቴ ሱቅ ስትልከኝ የምሄደው በብስክሌት ነበር"በማለት ፅጋቡ ይናገራል።

እንዲወዳደር መነሻ የሆነውም ታላቅ ወንድሙ ሰለሞን ገብረማርያም በብስክሌት ተወዳድሮ ድል አድርጎ ሲገባ ማየቱ እንደሆነ የሚናገረው ፅጋቡ በ1997 ዓ.ም የብስክሌት ህይወቱን አሃዱ ብሎ ጀመረ።

ፅጋቡ ከብስክሌት በተጨማሪ ጎበዝ እግር ኳስ ተጫዋችም እንደነበረ ይናገራል። ከ15 አመት ዕድሜ ባላቸው በፕሮጀክት ስር ታቅፎ ትግራይን በመወከል በተለያዩ አካባቢዎች ተጫውቷል። "እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተሰቦቼ ስፖርተኞች ናቸው። ሁለቱ ወንድሞቼ እና እህቴ ሯጮች ናቸው። የቤተሳባችን የመጨረሻ ልጅ የሆነው ቅዱስም የኔን ዱካ በመከተል ላይ ነው" በማለት ፅጋቡ ይገልጻል።

ፅጋቡ ብስክሌት መወዳደር ሲጀምር የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዷል በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ ከዚያም ከስድስት አመታት በፊትም ስዊዘርላንድ ተልኮ ከፍተኛ ስልጠና የሚወስድበትን አጋጣሚ አግኝቷል። ይህ አጋጣሚ ስልጠናን ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ካሉ ብዙ ተወዳዳሪዎች የመገናኘትንም ዕድል ፈጥሮለታል።

አጭር የምስል መግለጫ ፅጋቡ ብስክሌት በመንዳት በመለማመድ ላይ

"የስዊዘርላንዱ ስልጠና በጣም እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ነበር" በማለት ዓለም አቀፍ ፈታኝ ውድድሮችን የተዋወቀበትንም ምዕራፍ ያወሳል። በወቅቱም የብዙ ብስክሌት ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ምዕራፍ የሚሉትን ቱርደ ፍራንስ ለመወዳደር ለራሱ ቃል የገባው።

ዓለም አቀፍ ውድድር ቀላል አልነበረም። በራሱ አንደበትም "በሀገሬ ስወዳደር ወንድሜ በዘርፉም ስላለ አይዞህ የሚለኝ ነበር። ከሀገር ውጭ ግን ጥርሴን ነክሼ መወዳደር እንዳለብኝ እንዲሁም ስደናቀፍ እንዳልወድቅ ለራሴ ራሴን አለሁ አልኩት።"

3, 540 ኪ.ሜ የሚሸፍነውን የቱር ደ ፍራንስ ፈታኝነት ብዙዎች ይናገሩታል። የፅጋቡም ምላሽም ከዚህ የተለየ አይደለም። "ቱር ደ ፍራንስ ላይ ስትወዳደር ሳር ተጎዝጉዞ አይጠብቅህም። ከፊትህ ተነጥፎ የሚጠብቅህን እንቅፋት ማለፍ ግድ ነው።" በማለት ፅጋቡ ለውድድሩ አፅንኦት ይሰጣል።

ምንም እንኳን መንፈሰ ጠንካራ ቢሆንም "ጨረቃ መግባት ይቀላል" ብለው ህልሙን ያጣጣሉበትም እንዳልታጡ ፅጋቡ ይናገራል። ይህንንም እውን ለማድረግ አምስት ዓመት ለፍቶበታል። በዚህ ውድድር መሳተፉ ለብዙዎች መነቃቃትን መፍጠር የቻለው ፅጋቡ ከሁለት አመት በፊት ውድድሩን ለመጨረስ ትንሽ ፈትኖት ነበር። በዚህ አመት ያደረገው ውድድር ግን ብዙ እንዳልከበደው ይናገራል። "በየጊዜው ራሴን የማይበትና የምፈትንበት ውድድር ነው። ለቀጣይ አመት መወዳደር ካለብኝ በአራት እጥፍ መለማመመድ እንደለብኝ አምናለሁ።" ይላል ፅጋቡ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በተለያዩ የብስክሌት ውድድሮች የሚወዳደረው ፅጋቡ ገብረማርያም ለብዙዎች መነቃቃትን እየፈጠረ ነው።

የቱር ደ ፍራንስ ውድድሩ ተወዳዳሪ ለመሆን እያንዳንዱ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ከያዟቸው 30 የተመረጡ ተወዳዳሪዎች ጥሩ ነጥብ ያስመዘገቡ 9 ተወዳዳሪዎች ብቻ ናቸው ዕድሉን የሚያገኙት።

ፅጋቡ ባህሬ መሪዳን በሚባል ቡድን የታቀፈ ሲሆን ከእርሱም ጋር አብረው 27 አለምአቀፍ ብስክሌተኞች ነበሩ። ከእነሱ ተመርጦ ነው ዘጠኙ ምርጥ ውስጥ የገባው። " ከዘጠኙ አንዱ ሆኖ መመረጥ ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል። ለስድስት ወራትም ያህል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ተለማምጃለሁ። " በማለት እልህ አስቆራጩን ስልጠና ይናገራል።

ድካሙም መና አልቀረም። ፅጋቡ ገብረማርያም የቱር ደ ፍራንስ ውድድር መጨረስ ከቻሉ ጥቂት ጥቁር አፍሪካውያን አንዱ ሆኗል።

ከዚህ ውድድር በተጨማሪም በአፍሪካ ሻምፒዮና፣ ቱር ደ ሩዋንዳ፣ ቱር ደ ታይዋን፣ ቱር ደ ጣልያን፣ ቱር ደ ስፓኛ፣ ቱር ደ ፍራንስ እና በኦሎምፒክ ላይ ተወዳድሯል።

ለመጀመርያ ጊዜ ካገር ውጭ በነበረው በሩዋንዳው ውድድር ሶስተኛ ደረጃ ሲይዝ፡ ከሶስት ቀን በኋላም በቱር ደ ሩዋንዳ በመሳተፍ አምስተኛ ወጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ ፅጋቡ በቡርኪናፋሶ በተካሄደ አፍሪካ ሻምፒዮናም ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ በማግኘት ድል አድርጓል።

በተለይም ከኦሎምፒክ ጋር ተያይዞ ፅጋቡ ከ 44 አመት በኋላ ኢትዮጵያን ወክሎ በብራዚሉ ኦሎምፒክ ተወዳድሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎች ሊያቁት የቻሉት ኤድ ሀሪ የተባለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ "ፅጋቡ በቱር ደ ፍራንስ ድል የሚያደርግ አፍሪካዊ መሆን ይችል ይሆን?" በማለት ከአምስት አመት በፊት ፅፏል" አሁን ያለኝን ዕድሜና ወኔ ነገ አላገኘውም፣ እሳት ሲቀጣጠል ካልተጠቀሙበት ወደ አመድነት ይቀየራል። ለውድድሩ መክፈል ያለብኝን መስዋእት እየከፈልኩኝ ነው።፡ ይህንን ከረሳሁ ደግሞ ድል ማድረግ አልችልም" ይላል።

አጭር የምስል መግለጫ ፅጋቡ ልጁን አቅፎ

ሰዎች በሚናገሩት ጉዳይ ብዙ የማይደናገረው ፅጋቡ የሚያልመውን ከግብ ለማድረስ የሰዎችን አሉታዊ አስተያየት እንደማይሰማ ይናገራል። "ራሴን በራሴ ካላደናቀፍኩት ታግሎ የሚጥለኝ ሃይል አይኖርም። ስቃይ እና መራራ ህይወትንም አውቀዋለሁ" ይላል በትምህርቱ ከስምንተኛ ክፍል እንዳቋረጠ የሚናገረው ፅጋቡ።

ከህይወት ብዙ የህይወት ተሞክሮዎችን ተምሯል። ለቡና ለየት ያለ ፍቅር ያለው ፅጋቡ ከልምምድ በፊት ቡና ሳይቀምስ ከቤት አይወጣም። ከልጅነት ጓደኞቹ ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት ያለው ፅጋቡ ለመቐለ አምባሴራ ኳስ ሜዳ ጓደኞቹ ለየት ያለ ፍቅር አለው። በብዙዎች ዘንድ ትሁት ነው የሚባልለት ፅጋቡ በ 2001 ዓ.ም ለአክሱም ከተማ ከምትወዳደረው ከሓድነት አስመላሽ ጋር ትዳር የመሠረቱ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ሴት ልጅ መውለዳቸው ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።