ካለሁበት 1፡ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት አስደናቂ የኤርትራው ወጣት የስደት ጉዞ!

የፎቶው ባለመብት, ሽሻይ
የሜዲትራንያን ባህርና የሳህራ በረሃን ኣቋርጦ ጀርመን የደረሰው ኤርትራዊ ስደተኛ፡ ሽሻይ ተስፋኣለም (ነሽነሽ)
ሽሻይ ተስፋዓለም እባላለሁ፤ በርካቶች ነሽነሽ እያሉ ነው የሚጠሩኝ። ተወልጄ ያደኩት ኤርትራ ውስጥ ኳዕቲት በምትባል አካባቢ ነው። ለሙዚቃና ለኮሜዲ ልዩ ፍቅር አለኝ። ይሁን እንጂ በሳዋ ወታደራዊ ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ነበር የሆንኩት።
በዚህ ሥራዬ ደስተኛ አልነበርኩም፤ የማገኘውም ገቢ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ወላጆቼን ገንዘብ ስጡኝ እያልኩ አስጨንቅ ነበር።
በጊዜ ሂደት የኤርትራን ኑሮ ጠላሁት። በሃገሪቷ ውስጥ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ለምፈልገው አይነት ኑሮ ምቹ ስላልነበረ ከሃገር ለመውጣት ወስንኩኝ። ከሁለት ዓመታት በፊት ከኤርትራ ለመሰደድ ስነሳ በቤተሰቦቼና በራሴ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አውቅ ነበር።
ለስደት ምን አይነት ዝግጅት ማድርግ እንዳለብኝ እርግጠኛ አልነበርኩም። ሆኖም ግን ለጉዞ የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ለማግኘት የነበረኝን ንብረት በሙሉ በመሸጥ፤ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የእግር ጉዞ ጀመርኩ። የኤርትራን ድንበር በእግር ለማቋረጥ መሞከር በራሱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባት ማለት ነው።
ፈጣሪ ረድቶኝ ከረጅምና እጅግ አድካሚ የእግር ጉዞ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ገባሁ። ከዚያም በኢትዮጵያ ዓዲሓርሽ በሚባል የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ለሰባት ውራት ያክል ቆይቻለሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ከኤርትራ የተሻለ ነጻነት ነበረኝ። ከሞላ ጎደል ካምፑ ለኔ ጥሩ ነበር። በሽረ እንዳስላሴ ከተማ ከሚገኝ የባህል ቡድን ጋር የሙዚቃ ሥራዎችን የመስራት እድልም አግኝቼ ነበር። በኢትዮጵያ ቆይታዬ የሰራኋቸው ሙዚቃዎችም አሉኝ።
ከዚህም በተጨማሪ በሙዚቃ ሥራችን ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች የሰላምና የአንድነት መልዕክቶችን እናስተላልፍ ነበር።
ሺሻይ ከኤርትራ ጀርመን ለመድረስ የተጓዘበት መንገድ
ጉዞ ወደ ሊቢያ
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ቆይታዬ መልካም የሚባል ቢሆንም አውሮፓ የመግባት ህልሜን ማሳካት እንዳለብኝ ሁሌም ይሰማኛል። ከዚያም ፍላጎቴን ለማሳካት ለሌላ የስደት ጉዞ እራሴን አዘጋጅ ጀመር። ኢትዮጵያ ውስጥ ከተዋወቅኳቸው ጓደኞቼ ጋር በመሆን ጉዞ ወደ ሱዳን ተጀመረ። ለቀናት በእግርና በመኪና ረጅም ጉዞ ካደረግን በኋላ ሱዳን ገባን። ሱዳን ከደረስን በኋላ አውሮፓ የመግባት ፈላጎቴ እጅጉን ጨመረ። በሱዳን በቂ እረፍት እንኳን ሳናደርግ እያንዳንዳችን ለደላሎች 1600 የአሜሪካን ዶላር በመክፈል ረጅሙን የሊቢያ ጉዞ ጀመርን።
የሊቢያው ጉዞ እጅግ ፈታኝና አደገኛ ነበር። የዓለማችንን ትልቁንና እጅግ ሞቃታማ የሆነውን የሰሃራ በረሃን ማለፍ ይጠይቃል። ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው የፈጣሪ እገዛ ተጨምሮበት እንጂ ሰሃራ በረሃን ማቋረጥ በእኔ አቅም የማይታሰብ ነበር። በበረሃው የአውሬ ሲሳይ ሳልሆን ከብዙ ድካምና ስቃይ በኋላ ሊቢያ እንደደረስን ተነገረን። ሊቢያ መድረሴን ስስማ አውሮፓ የደረስኩ ያህል ነበር የተሰማኝ። ካሳለፍኳቸው ስቃዮች መካከል ትልቁን የተጋፈጥኩት ሊቢያ ውስጥ ነበር። ከሊቢያ ወደ አውሮፓ መሄድ የሚፈልግ የሜዲትራንያን ባህርን በጀልባ ማቋርጥ አለበት። በሊቢያ ደግሞ ስደተኞችን የሚያዘዋውሩ በርካታ አደገኛ ደላሎች አሉ። እነዚህ ደላሎች ስደተኞችን የማሰር እና የማሰቃየት ልምድ አላቸው። እኔም በወቅቱ ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚያስፈልገው ገንዘብ ስላልነበርኝ ለሦስት ወራት በደላሎችና በህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በተደጋጋሚ ድብደባ ደርሶብኛል።
ከሦስት ወራት ስቃይ በኋላ ከቤተሰቦቼ የተላከልኝን 2000 ዶላር ከፈልኩኝ። ከዚያም የሜዲትራንያንን ባህር ለማቋረጥ እንድዘጋጅ ተነገረኝ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በግምት 1500 የምንሆን ስደተኞችን ደላሎቹ በሶስት ቡድን ከፍለው በአነስተኛ ጀልባዎች የሜድትራንያን ባህርን አቋርጠን ወደ ጣሊያን ለመግባት ጉዞ ጀመርን። ከነበረው ሰው ብዛት የተነሳ የጀልባዋን አካል ማየት ሁሉ ይከብድ ነበር። ጥቂት እንደተጓዝን ማለቂያ የሌለው ባህር እንጂ የመሬት አካል አይታይም ነበር። በዚህ እጅግ አስፈሪ በሆነው ባህር ላይ በሰላም የተጓዝነው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበረ። ከአንዷ ጀልባ በቀር እኔ የተሳፈርኩባት ጀልባን ጨምሮ ሁለቱ ጀልባዎች ችግር ገጠማቸው። እኔ ያለሁባት ጀልባ ተበላሸታ ስትቆም ሌላኛዋ ጀልባ ከአቅሟ በላይ ሰው ስለጫነች በዓይኔ እያያኋት ቢያንስ 500 ስደተኞችን እንደጫነች ሰመጠች። እጅግ በጣም አሰፈሪና አሰቃቂ ሁኔታ ነበረ።
የፎቶው ባለመብት, ANGELOS TZORTZINIS
ስደተኞች የሜዲትራንያንን ባህር በማቋረጥ ወደ ኣውሮፓ ይገባሉ።
ከሰዓታት በኋላ የሊቢያ የባህር ድንበር ጠባቂዎች ደርሰው እኛንና ከመስመጥ አደጋ የተረፉትን ወደ ሊቢያ በመመለስ እስር ቤት ወረወሩን። እስር ቤት እያለሁ ሦስተኛዋ ጀልባ ጣሊያን እንደደረሰች ሰምቻለሁ። ሊቢያ እስር ቤት ውስጥ እያለሁ እጀጉን ተስፋ ቆርጬ ነበር። በምንም አይነት ሁኔታ ግን ሊቢያ መቆየት እንደማልችል አውቅ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ገንዘብ እንድከፍል የፈለጉት ደላሎች ለሊቢያ ፖሊሶች ጉቦ በመስጥት ካስፈቱኝ በኋላ 800 የአሜሪካን ዶላር አስከፍለው ዳግመኛ የሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ተሰናዳሁ።
ሁለተኛው ጉዞ ግን እንደፈራሁት ሳይሆን ጣሊያን ደረስኩ። እዚያ ግን የተቀበለኝ ፖሊስ ነበር። ጣሊያን ሃገር በእስርና በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለ11 ወራት ቆይቻለሁ።
ጣሊያን ለወራት ከቆየሁ በኋላ በጀርመን መንግሥት ፈቃድ በህጋዊ መንገድ ወደ ጀርመን እንድገባ ተፈቀደልኝ። በመጨረሻ ያለምንም ስጋት ተመችቶኝ ከጣሊያን ወደ ጀርመን በአውሮፕላን ገባሁ። በሜዴትራንያን ባህር ላይ ከመስመጥ መትረፌ ግን ሁሌም ይደንቀኛል።
የፎቶው ባለመብት, ነሽነሽ
የጀርመን ኑሮ
ጀርመን ከገባሁ ሦስት ወራት ተቆጥረዋል። በምዕራባዊ ጀርመን ሙንስተር ከተማ ውስጥ ነው የምኖረው።
ህይወትን በጀርመንና በኤርትራ ከቶ ማወዳደር አይቻልም። ጀርመን እጅግ በጣም ጥሩ ሃገር ናት። ከደጃፌ ጀምሮ ዓይንን የሚማርኩ ነገሮችን አያለሁ። በጣም ንፁህና አረንጓዴ አካባቢ ነው።
በጣም ባማር ቤት ውስጥ ነው የምኖረው። አሁን ሥራ ከመጀመሬ በፊት የጀርመን ቋንቋ መማር ግዴታ ስለሆነ ለስድስት ወራት ጀርመንኛ ቋንቋን እየተማርኩኝ ነው።
የፎቶው ባለመብት, ነሽነሽ
ኣረንጓዴ አከባቢ፡ ማፐን ዲ፡ ጀርመን
ኤርትራ እያለሁ ሁል ጊዜ መብላት የምፈልገውን ዶሮ እዚህ እንደልቤ አገኛለሁ። እዚህ ሁኜ የሚናፍቀኝ ነገር ቢኖር ኤርትራ ውሰጥ ያሳለፍኩት ጥሩ ጊዜና የአብሮ አደግ ጓደኞቼ ፍቅር ነው።
የወደፊት ዕቅድ
በአጠቃላይ ለጥበብ ልዩ ፍቅርና ፈላጎት አለኝ። ወደፊት የሙዚቃ ሥራን መስራት እፍልጋለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በአማርኛና በትግረኛ የተፃፉ የፊልም ድርስቶች አሉኝ። እንዚህን ድርሰቶች ወደ ፊልም የመቀየር እቅድ አለኝ። ኤርትራ እያለሁ የአማርኛ ፊልሞችን በብዛት ከማየቴ የተነሳ ተዋናይት ሠላም ተፋዬን እጅግ አፈቅራታለሁ። ወደፊትም ድርሰቶቼን ከሠላም ጋር ወደ ፊልም ለመቀየር እመኛለሁ።
ለላይን ጽጋብ እንደነገራት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦