በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ የሚገኙ ስደተኞች ሰቆቃ

ደቡብ ሱዳናዊ ስደተኛ
የምስሉ መግለጫ,

ሃኔሲ ለሶስት ዓመታት ወደኖረባት ለንደን መመለስ ያስባል

የ18 ዓመቱ ደቡብ ሱዳናዊ ሃኔሲ ማንጂንግ በባህር ላይ ጉዞው መጥፎ ነገር ሊገጥመው እንደሚችል ጠብቋል።

ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለማቋረጥ በሚያደርገው ጉዞ ክፉ ሊገጥመው ሕይወቱንም ሊያጣ እንደሚችል ያውቅ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2017 እስካሁን 2400 የሚሆኑ ስደተኞች የሜዲትራኒያን ባህር ሲሳይ ሆነው በወጡበት ቀርተዋል።

ሃኔሲ ግን ገና ከባህሩ ሳይደርስ የእገታና ድብደባ እጣ ገጠመው፤ ከተኩስም ተረፈ ።

ታዳጊው እንደሚለው በ2016 ስደትን የመረጠው በቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረው ችግር ወደ ግድያ ዛቻ ሲያድግ ነው።

አሁን ከሌሎች 1000 ወንዶች ጋር በትሪፖሊ በሚገኘው ትሪክ አል ሲካ በተሰኘው ማቆያ ውስጥ ይገኛል። ከእስረኞቹ ብዙዎቹ ሥራ ፍለጋ ተሰደው ከባሀር የተመለሱ ወይም ገና ከጅምሩ የተያዙ አፍሪካውያን ናቸው።

አሁን ብርሃንን በሚናፍቁበት አንድ መጋዘን ውስጥ ታጭቀው ለመተንፈስ እንኳን ይታገላሉ።

በመጨናነቅ በሚፈጠር ሙቀት ላይ በቆሻሻ ያደፈ ልብሳቸው ተጨምሮ ስቃያቸውን ያባብሰዋል።

አንዳንዶች ሙቀቱን መቋቋም ሲያቅታቸው የካርቶን ቁራጮችን በማራገብ ራሳቸውን ለማረጋጋት ይሞክራሉ።

በምሽት ደግሞ በሮች ሲለሚዘጉ ሽንታቸው ሲመጣ ጠርመሶችን መጠቀም ግድ ይላቸዋል።

"ከእስር ቤትም የባሰ ገሃነም ቢባል ይቀላል" ይላል ሄኔሲ

የምስሉ መግለጫ,

እስረኞችን ለመመገብ የሚያስችል በቂ ገንዘብ የለም

"በጥይት የተመታሁ መስሎኝ ነበር"

ሄኔሲ ወደብሪታኒያ ለመሄድ ባለው ጉጉት ነው፤ በመጀመሪያ የግብጽን ከዚያም የሊቢያ ድንበር ያቋረጠው።

በመንገድ ላይ ሳለ ግን የታጠቁ ቡድኖች እሱንና ሌሎች 40 ስደተኞችን ከአዘዋዋሪዎቻቸው ነጥቀው ወሰዷቸው።

"መሳሪያና ዱላ የያዙ ሰዎች መጡና ወደመኪናዎቻቸው እንድነገባ አስገደዱን፤ እኛም ከመኪናው መዝለል ጀመርን። ከቻድ የመጣ አንድ ሽማግሌ ላይ ተኮሱበትና ደሙ የለበስኩትን ከነቴራ አራሰው። እኔም የተመታሁ ነበር የመሰለኝ ቢሆንም መሮጤን አላቋረጥኩም ''

ሄኔሲ ከእንድ የአካባቢው ነዋሪ እርዳታ ቢጠይቅም ከማገዝ ይልቅ መልሶ ለአጋቾቹ አስረከበው።

"መጀመሪያ በጥፊ መታኝ ፤ ከዛ እየደበደደበኝ 'ለምን ሮጥክ?' አለኝ" ሄንሲ ሁኔታውን ያስታውሳል።

"በሶስተኛ ቀን ግን ፈጣሪ ይመስገን አዘዋዋሪው መጣና አስለቀቀን።''

ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ ትሪፖሊ ቢጓዝም የተሰጠው ቪዛ ሃሰተኛ በመሆኑ በአየረ ማረፊያው አካበቢ ወደሚገኝ እስር ቤት ተወሰደ።

"በየቀኑ ያሰቃዩን ነበር፤ ሰዎች ድምጽ ካሰሙም ሆነ ምግብ ለመብላት ከተጣደፉ ይደደበባሉ" ይላል።

ከእርሱ ጋር የታሰሩ ሰዎች ደግሞ ከዚህም የባሰ ነገር የገጠማቸው ናቸው፤ በታጣቂዎች እየተሸጡና እየተገዙ እንደባሪያ አገልግለዋል። ታዳጊ ሴቶች ደግሞ ማንም ሳይከላከልላቸው በታጣቂዎቹ ተደፍረዋል።

" ወደ ሀገሬ መሄድ ብቻ ነው የምፈለግው"

የምስሉ መግለጫ,

ኦስማን አብዱልሰላም

ሱዳናዊው ኦስማን አብዱልሰላም አንገቱ ላይ ያለውን ፎጣ ሲገልጥ ትልቅ ጠባሳ ይታይበታል።

በባኒ ዋሊድ እስር ቤት እያለ የደረሰበት እንግልት ማስታወሻ ነው። እስረኞቹ በስቃይ ውስጥም እያሉ ወደቤተሰቦቻቸው እየደወሉ ገንዘብ እንዲልኩላቸው የመጠየቅ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

"ሁልጊዜም እቤት ስንደውል እናለቅሳለን፤ እነሱ ደግሞ ጭንቅላታችን ይደበድቡናል። የማንታዘዝ ከሆነ ደግሞ ሰውነታቸውን ያቃጥሉታል። በአርሶ አደርነት የሚተዳደረው አባቴ ደግሞ ምንም ገንዘብ ስለሌለው ቤታችንን ሸጠ።"

ለኦስማን ነጻነት በሚል ቤተሰቦቹ 5000 ዶላር ከፍለዋል።

በቢቢሲ ሪፖርተር አሁንም ወደ አውሮፓ ለመሄድ ይፈልግ እንደሆነ ሲጠየቅ ግን እንባ ስለተናነቀው አይኖቹን በፎጣ ሸፈናቸው።

"ከዚህ ቦታ ወጥቼ ወደ ሀገሬ መመለስ ብቻ ነው የምፈልገው" የመጨረሻ ቃሉ ነው።

በግዳጅ የሚመለሱበት ቀን መናፈቅ

በትሪክ አል ሲካ የቁርስ ሰዓት ረጅም ሰልፍ ግን አነስተኛ ምግብ ማየት የተለመደ ነው።

ስደተኞቹ ትንንሽ ዳቦ፣ የገበታ ቅቤና ቀጭን ጭማቂ በትንሽ ኩባያ ይሰጣቸዋል።

ይህንን እውነት ደግሞ ስደተኞቹም ሆነ የማቆያው ኃላፊዎች እንዲታወቅላቸው ይፈልጋሉ፤ ምክኒያቱም ለአዘጋጆቹ የሚሰጡት ገንዘብ ስላጠራቸው ለጋሾችን ይፈልጋሉ።

በእርግጥም እነዚህ ሰዎች ነፃ የሚወጡበትን ጊዜ የማያውቁ እስረኞች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, BBC

የምስሉ መግለጫ,

የሶስት ወራቱ ጨቅላም የእስርቤት ህይወቱን ጀምሯል።

ሶላ ይህን አጭር እድሜውን በዚህ እስር ቤት ውስጥ ነው ያሳለፈው።

እናቱ ዋሲላ ገና በአራት ወሩ በባህር በኩል ወደ ጣሊያን ልታሻግረው ሞክራ ነበር።

"ጀልባችን ተሰበረችና እዛው ባህሩ ላይ ፖሊሶች ያዙን፤ ከዛ በኋላ በአምስት የተለያዩ እስር ቤቶች ቆይቻለሁ። በቂ ምግብ የለንም፤ ወላጆቻችን ጋር እንድንደውል አይፈቀድልንም፤ በሕይወት ልኑር ልሙት የሚያውቁት ነገር የለም፤ እኔ ና ልጄ እየተሰቃየን ነው" ትላለች።

ባለቤቷም በሌላኛው የስደተኞች ማቆያ ውስጥ ተመሳሳይ እጣፈንታ እየተጋፈጠ ነው።

መቼ እንደሚገናኙም ሆነ ነጻ እንደሚወጡ አታውቅም።

አሁን ግን ወደ አውሮፓ የመሔድ ህልሟን ትታ ወደ ሃገሯ ቶጎ የምትመለስበትን ቀን ትናፍቃለች።