ትራምፕ፤ ከዲሞክራቶች ጋር ስደተኞችን በተመለከተ አልተስማማሁም አሉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

ዶናልድ ትራምፕ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፈቃድ ያላገኙ ታዳጊ ስደተኞችን በተመለከተ ከዲሞክራቶች ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል የተባለውን ዜና አስተባበሉ።

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ''ስደተኞቹን በተመለከተ ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ በምላሹ መጠነ ሰፊ የድንበር ደህንነት ጥበቃ ላይ መስማማት ይኖርብናል።'' ብለዋል።

በአሜሪካ ለመኖር ፈቃድ ያላገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ስደተኞች እንዳይባረሩ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ላይ ከፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ ጋር መድረሳቸውን ሁለት ከፍተኛ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ባለሥልጣናት ተናገረው ነበረ።

ዲሞክራቶቹ ናንሲ ፔሎሲና ቸክ ሹመር እንዳሉት፤ የትራምፕ ዕቅድ የሆነውን የሜክሲኮ ድንበር ላይ አጥር እቅድን ሳይጨምር በድንበር ደህንነት ጉዳይ ላይም አብረው ለመሥራትም ተስማምተናል ብለው ነበረ።

የዋይት ሃውስ ባለሥልጣናት ግን የሜክሲኮ ድንበር አጥር ጉዳይ ከቀረበው ሃሳብ ውጪ መሆኑን አስተባብለዋል።

ከሳምንታት በፊት ፕሬዚዳነት ትራምፕ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ታዳጊዎች በተለየ ሁኔታ የሚስተናገዱበትን ፈቃድ ሰርዘውት ነበር።

ይህ በኦባማ ዘመን ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ ታዳጊዎችን ከመባረር ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ ሲሆን፤ በዚህም 800ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች አሜርካ ውስጥ እንዲቆዩ ከማስቻሉም በላይ እንዲማሩና እንዲሰሩ ጊዜያዊ ፈቃድ እንዲያገኙ አድርጓል።

በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳነት ትራምፕ ይህን አሰራር እንደሚያስቀሩ ይፋ ካደረጉ በኋላ፤ ኮንግረስ አዲስ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የስድስት ወራት ጊዜን ሰጥተው ነበረ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቸክ ሹመርና (የሚናገሩት) ናንሲ ፔሎሲ (በስተግራ) ስደተኞችን

ዋይት ሃውስ ውስጥ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ዴሞክራቶቹ ናንሲ ፔሎሲና ቸክ ሹመር ከፕሬዝዳነቱ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ እንደተናገሩት፤ ''የነበረውን አሰራር ወደ ህግ ለመቀየርና የሜክሲኮን ድንበር አጥር ሳይጨምር፤ የድንበር ደህንነት ጥበቃን በተመለከተ አብረን ለመሥራት የተስማማን ሲሆን፤ ይህም በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት አግንቷል'' ብለው ነበረ።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቁልፍ ጉዳይ የነበረው የድንበር አጥር ጉዳይን በተመለከተ የሚያስፈልግ ወጪን የያዘ የትኛውም ህግ ለምክር ቤት ከቀረበ ውድቅ እንደሚያደርጉት ዴሞክራቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ይህንን በተመለከተ ከዋይት ሃውስ የወጣ መግለጫ ግን ቀዝቀዝ ያለ ነበረ። መግለጫው የታክስ ማሻሻያ፣ የድንበር ደህንነትና የስደተኞች ጉዳይ ላይ ''ገንቢ ውይይት'' የተደረገበት ምሽት እንደነበረ ብቻ ጠቅሷል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ ግን ከዲሞክራቶች በኩል የተሰማውን አዲስ ሃሳብን የሚቃረን የትዊተር መልዕክት አስፍረው ነበረ። ''ስለስደተኞችና የድንበር ደህንነት ጉዳይ ላይ ውይይት ተደረገ ቢሆንም፤ የድንበር አጥሩን ላለማካተት ግን ስምምነት አልተደሰም'' ብለዋል።

የሹመር ረዳትም ለዚህ በሰጡት ምላሽ ''ፕሬዝዳንቱ የድንበር አጥሩን ጉዳይ እንደሚገፉበት ግልፅ ያደረጉ ቢንም፤ የስምምነቱ አካል ግን አይደለም'' ብለዋል።

ሪፐብሊካኖች በሁለቱም ምክርቤቶች የበላይነት ስላላቸው ማንኛውንም አይነት ስደተኞችን የተመለከተ ህግ ለማውጣት ድጋፋቸው የግድ አስፈላጊ ነው።