ቢቢሲ አዲስ አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያና ኤርትራ ጀመረ

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ድረ-ገጻቸውን እየተመለከቱ
አጭር የምስል መግለጫ ድረ-ገጾቹ ካሁኑ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችለዋል

ቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ እ.አ.አ. ከ1940 በኋላ ባካሄድው ከፍተኛ ማስፋፊያ ለኢትዮጵያና ጎረቤት ሃገር ኤርትራ በሶስት አዳዲስ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ነፃና ገለልተኛ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን እጥረት ባለበት ቀጠና ውስጥ ድረ-ገጾቹ ''የእውነታ ምንጭ'' ይሆናሉ ይላል የቢቢሲው አርታኢ ዊል ሮስ።

የቢቢሲ የአማርኛ፣ የአፋን ኦሮሞና የትግርኛ ቋንቋ ድረ-ገጾች ሥራ በጀመሩ በጥቂት ወራት ውስጥ በሦስቱም ቋንቋዎች የሬዲዮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እ.አ.አ. በ2015 ለወርልድ ሰርቪስ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ይህም ድጋፍ በአፍሪካና እስያ አዳዲስ አገልግሎቶች አንዲጀመሩ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ አበርክቷል።

''በኢትዮጵያና በኤርትራ፤ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥራት ያለው መረጃ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ እንረዳለን'' ይላል የሦስቱ ቋንቋዎቸ አገልግሎት አርታኢ ዊል ሮስ።

ዊል ሮስ አክሎም "በሁለቱ ሃገራት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአድማጭ ተመልካች ቁጥር አለ- በትንሹ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሃገራቱ ውስጥ ይኖራል። ከዚህም በላይ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ወጣቱን ለመድረስ ይረዱናል" ብሏል።

የሦስቱ ቋንቋዎች የፌስቡክ ገጾች ካሁኑ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችሏል።

በሁለቱም ሃገራት ውስጥ የበይነመርብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት ተደራሽነት አነስተኛ በመሆኑ በጥቂት ወራት ውስጥ ''የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ለመዳሰስ'' የሬዲዮ አገልግሎት እንጀምራለን ሲል ያክላል ዊል ሮስ።

አዳዲስ የቢቢሲ አገልግሎቶች

በአፍሪካ

 • አማርኛ
 • አፋን ኦሮሞ
 • ትግርኛ
 • ኢግቦ፡ የናይጄሪያ የሥራ ቋንቋ ነው። በኢኳቶሪያል ጊኒም ይነገራል።
 • ዮሩባ፡ በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያና በምዕራብ አፍሪካ ቤኒንና ቶጎ ውስጥ ይነገራል።
 • ፒጅን፡ በደቡብ ናይጄሪያ፣ በጋና፣ በካሜሩንና በኢኳቶሪያል ጊኒ ይነገራል።

በእሲያ:

 • ጉጃራቲ፡ በህንድ ጉጃራት ግዛት ውስጥ በስፋትና በተለያዩ የህንድ ግዛቶች ውስጥ ይነገራል።
 • ማርቲ፡ ሙምባይን ጨምሮ በህንዱ ማሃራሽትራ ግዛት ውስጥ በስፋት ይነገራል።
 • ቴሌጉ፡ በአንድራና ቴላኛን የህንድ ግዛቶች ውስጥ ይነገራል።
 • ፑንጃቢ፡ በዓለማችን ላይ በብዙዎች ሰዎች ከሚናገሩት ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው። በፓኪስታንና በህንድ ይነገራል።
 • ኮሪያን፡ ዘዬው ይለያይ እንጂ በደቡብና በሰሜን ኮሪያ ውስጥ ይነገራል።

ተያያዥ ርዕሶች