የሳምንቱ ቡድን ውስጥ አጉዌሮ፣ የሱስ፣ ደብሩይን፣ ቫሌንሽያና ኮላስናች ተካተዋል

የቀድሞ ማንችስተር ዩናይትድና የቶተንሃም ተጫዋች የነበረው የጋርስ ክሩክስ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን!

የሳምንቱ ምርጥ ቡድን

ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች በዚህ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ተቀናቃኞቻቸው ላይ 10 ጎሎችን ማሳረፍ ችለዋል። ማንቸስተር ሲቲ ዋትፎርድን 6 ለ 0 እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን 4 ለ 0 በማሸነፍ ጠንካራ ግስጋሴያቸውን ቀጥለውበታል።

የክሪስታል ፓላስ አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት ሮይ ሆጅሰን በሳውዝሃምፕተን 1 ለ 0 ተሸንፈው ሥራቸውን ሲጀምሩ፣ አርሴናል ከቼልሲ ጋር ባደረገው ፍልሚያ ከስድስት ዓመታት በኋላ በሊጉ በስታንፎርድ ብሪጅ የመጀመሪያ ነጥቡን አግኝቷል።

ሊቨርፑል ከበርንሌይ አቻ ሲለያይ፤ ኒውካስልና ቦርንወማውዝ አሸንፈዋል።

ቶተንሃም ከስዋንሲ፤ ዌስት ሃም ከዌስት ብሮም እና ሃደርስፊልድ ከሌስተር በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሌሎች ጨዋታዎች ናቸው።

  • የሳምንቱ ምርጥ ቡድን

ግብ ጠባቂ - ኒክ ፖፕ (በርንሌይ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርንሌይ ከሊቨርፑል ጋር አንድ እኩል ባጠናቀቀበት ጨዋታ ግብ ጠባቂው ኒክ ፖል ስምንት ኳሶችን አድኗል። በዚህም ከሉካስ ፋብያንስኪ እኩል በሳምንቱ ብዙ ኳሶችን ያዳነ ግብ ጠባቂ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት በጉዳት የወጣውን ቶም ሂተንን በመተካት ምርጥ ብቃቱን ማሳየቱ ይታወሳል።

እንደጋሬት ኩክ ገለጻ ግብ ጠባቂው በሻምፒዮንስ ሊግ መጫወት የሚያስችለውን አቋም በጨዋታው ላይ አሳይቷል።

ተከላካይ - ጀማል ላሴልስ (ኒውካስል )

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጃማል ላሴልስ በፕሪሚየር ሊጉ ያስቆጠራቸው አራቱ ጎሎች ከማዕዘን ምት የተገኙ ናቸው።

ኒውካስትል ዩናይትድ ከሰሞኑ እያሳየ በሚገኘው ጠንካራ እንቅስቃሴ ውስጥ ላሴልስ ቀዳሚውን ድርሻ ይዟል።

የኒውካስል አምበል የሆነው ላሴልስ ባለፈው ሳምንት ስዋንሲ ላይ ካስቆጠረው የጭንቅላት ኳስ በተጨማሪ ስቶክ ላይ ያስቆጠራት ጎል ክለቡን አሸናፊ አድርጋለች።

ተከላካይ - ጆኤል ማቲፕ (ሊቨርፑል)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጆኤል ማቲፕ ከነሐሴ 2016 ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ከተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሊቨርፑል 59 በመቶውን ሲያሸንፍ እሱ በሌለበት 44 በመቶ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው።

ጠንካራ የመከላከል ፍላጎት ያለው ካሜሮናዊው ማቲፕ እንዳሳየው ብቃት ባይሆን ኖሮ ሊቨርፑል በበርንሌይ የመሸነፍ ዕድል ነበረው።

ቤን ሚ የሞከራትን ኳስ ማቲፕ ከግብ መስመር ላይ ማዳኑ ለቀያዮቹ ውጤት ትልቅ ሚና ነበረው።

ተከላካይ - ሽኮርዳን ሙስጣፊ (አርሴናል)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዘንድሮው ፕሪሚር ሊግ 16 ኳሶችን ከመከላከል ቀጠና ያወጣው ሽኮርዳን ሙስጣፊ ከናቾ ሞንሪያል ቀጥሎ ለአርሴናል ሁለተኛው ጠንካራ ተከላካይ ያደርገዋል። ሞንሪያል 21 ኳሶችን ከመከላከል ቀጠና በማውጣት የክለቡ ቀዳሚ ተጫዋች ነው።

እሁድ በተካሄደው የለንደን ደርቢ ሙስጣፊ የቼልሲውን አጥቂ ሞራታ ጥሩ እንቅስቃሴ ሳያደርግ እንዲያመሽ አግዶታል።

መድፈኞቹ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአንፊልድ ከደረሰባቸው የሽንፈት ጫና የተላቀቁ ይመስላሉ። ሙስጣፊ፣ ላውረን ኮሽሊኒ እና ሰኢድ ኮላስኒች ጤናማ ከሆኑ አርሴናል ከአንድ እስከ አራት ያሉትን ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ ዕድሉ ከፍ እንደሚል ተንታኙ ይናገራል።

ቀኝ መስመር ተከላካይ - አንቶንዮ ቫሌንሽያ (ማንቸስተር ዩናይትድ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንቸስተር ዩናይትድ አንቶንዮ ቫሌንሽያ ኦልድትራፎርድ ላይ ጎል ያስቆጠረባቸውን 12 ጨዋታዎች በሙሉ ማሸነፍ ችሏል።

ቫሌንሽያ እንደቀድሞው ጎል እያስቆጠረ ባይሆንም ኤቨርተን ላይ ያስቆጠራት ጎል ግን እጅግ ማራኪ ነበረች። ተከላካዩ አክርሮ የመታት ኳስ መረብ ላይ አርፋ እንኳን የኤቨርተኑ ግብ ጠባቂ አየር ላይ ነበር። አስደናቂ ጎል ነው ያስቆጠረው።

አማካይ- ኬቪን ዲ ብሩይን (ማንችስተር ሲቲ)

የፎቶው ባለመብት, Rex Features

አጉዌሮን የሚያህል ቁመት ያለው ሰው እንዴት በጭንቅላት ሊያስቆጥር ይችላል? ሚስጥሩ የኳስ አቀባዩ ነው።

ኬቪን ዲ ብሩይን ለሰርጂዎ አጉዌሮ እጅግ ውጤታማ የሆኑ ኳሶችን ያሳልፋል። ከዋትፎርድ ጋር በነበረው ጨዋታ ለጎል የሚሆን ኳስ በማቀበል ማንችስተር ሲቲ በርካታ ጎሎቹን እንዲያስቆጥር ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ችሏል።

ማንችስተር ሲቲ በቻምፒዮንስ ሊግ ፌይርኖርድን ያሸነፈበትን መንገድ ብንመለከት እንዲሁም ከሶስት ቀናት በኋላ ዋትፎርድን በቀላሉ በብዙ ጎል ልዩነት ማሸነፉን ብናጤን ብዙ ነገር ይነግረናል።

የመጀመሪያው ሲቲ እንደ ቡድን እየተጠናከረ መምጣቱን፤ ሁለተኛ በተመሳሳይ ወቅት በቻምፒዮንስ ሊግና በፕሪሚያር ሊጉ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚችሉ እንዲሁም ሁሉም የሲቲ ተጨዋቾች ጎል የማስቆጠር ፍላጎት እንዳለቸው መረዳት እንችላለን።

የሰሞኑ የሲቲ ብቃት በፕሪሚየር ሊጉ ሰንጠረዥ ላይ በእኩል ነጥብ የሚገኙት ማንችስተር ዩንይትዶችን ማስጨነቁ አይቀርም።

አማካይ- ማሪዮ ሌሚና (ሳውዝሃምፕተን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዘንድሮው የውድድር ዓመት 90 በመቶ የሚሆኑ የተሳኩ ኳሶችን በማቀበል ማሪዮ ሌሚና የሳውዝሃምፕተን ቀዳሚ ተጫዋች ነው። ከዚህ በተጨማሪ እጅግ ጠንካራ ነው።

በትልልቅ ክለቦች ውስጥ ለመጫወት ሁሉንም ነገር ማሟላት አስፈላጊ ነው። ሌሚና እያንዳንዱን የክሪስታል ፓላስን እንቅስቃሴ ሲያጨናግፍ አምሽቷል።

የቀድሞው የጁቬንቱስ ተጫዋች ከኳስ ጋር ካለው ስኬታማ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ኳስ በማስጣል በኩል የነበረው ሚና የተቃራኒ ቡድንን የጨዋታ ፍሰት ያስተጓጎለ ሆኗል።

ሌሚና እንደአርሴናልና ሊቨርፑል ባሉ ክለቦች መጫወት የሚችል ሆኖ ይሰማኛል ሲል ክሮክስ ይገልጻል።

ግራ መስመር ተከላካይ - ሰኢድ ኮላሲናች (አርሴናል)

የፎቶው ባለመብት, Rex Features

በዘንድሮው ዓመት ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ከሰኢድ ኮላስኒች የሚቀድም የአርሴናል ተጫዋች የለም።

ኮላስኒች ጠንካራ ተክለ ሰውነት ያለው ተጫዋች መሆኑን ክሩክስ ይገልጻል። ያለፈው ዓመት ምርጥ ተከላካይ በነበረው ዴቪድ ሉዊዝ ከተፈጸመበት ከባድ ሸርተቴ በኋላም ቢሆን ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ችሏል።

አጥቂ - ሞሃመድ ሳላህ (ሊቨርፑል )

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ አራት ግብ በሆኑ ኳሶች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ሞሃመድ ሳላህ በክለቡ ቀዳሚ ለመሆን ችሏል።

ሳላህ በሊቨርፑል ውጤታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ግብጻዊው ለመርሲሳይዱ ክለብ በሰባት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂ -ሰርጂዮ አጉዌሮ (ማንቸስተር ሲቲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንቸስተር ሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ ከሜዳው ውጭ በተጫወተባቸው እና አጉዌሮ ቋሚ ተሰላፊ በነበረባቸው ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ማኑዌል ፔሌግሪኒ የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት የነበረውን ጠንካራ አቋሙንም መድገምም ችሏል።

ዋትፎርድ ላይ ያስቆጠራት ሶስተኛ ጎል እ.አ.አ በ1986 ዲያጎ ማራዶና እንግሊዝ ላይ ካስቆጠራት ጎል ጋር ተመሳሳይነት አላት።

አጉዌሮ የዋትፎርድ ተከላካዮችን በአስገራሚ ሁኔታ አልፎ ወደ ግብ የመታትን ኳስም ግብ ጠባቂው አድሪያን ማሪያፓ ከማየት ውጭ ምንም ሊያደርጋት አልቻለም። ይህ ድንቅ ስራ ነው።

ጨዋታው አጉዌሮ በፕሪሚርሊጉ ስድስተኛ እንዲሁም ለክለቡ አስረኛ ሃትሪኩን ያስመዘገበበት ሆኗል።

አጥቂ - ጋብሪኤል የሱስ (ማንቸስተር ሲቲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋብሪኤል የሱስ ለማንቸስተር ሲቲ በፕሪሚር ሊጉ በተሰለፈባቸው 15 ጨዋታዎች በአስራ አምስት ግቦች ላይ ተሳትፎ ነበረው።

ተጋጣሚ ቡድን ጥቃትን በመለየት ሲከላከል እጅ አለመስጠት የጠንካራ ተጫዋች ምልክት ነው።

የዋትፎርዶቹ ጆሴ ሆሌባስና ዳርይል ያንማት ተክለሰውነታቸውን ተጠቅመው ኬቪን ዲ ብሩይንን እና ጋብርኤል የሱስን ለማቆም ጥረዋል። የሱስ በዚህ ሳይበገር ግብ ለማስቆጠር ችሏል።