ማሪያ የተባለው ከባድ አውሎ-ነፋስ ወደ ካረቢያን ደሴቶች እየተቃረበ ነው

ማሪያ ተብሎ የተሰየመው እጅግ አደገኛ አውሎ-ነፋስ

የፎቶው ባለመብት, EPA/NASA

ማሪያ ተብሎ የተሰየመው እጅግ አደገኛ አውሎ-ነፋስ ወደካረቢያን የሊዋርድ ደሴቶች እየተቃረበ ነው።

የአሜሪካው ብሔራዊ የአውሎ-ነፋስ ጣቢያ እንዳለው ይህ ምድብ አንድ ተብሎ የተመደበው አውሎ-ነፋስ በሚቀጥሉት 48 ስዓት ውስጥ ኃይሉን በማጠናከር ሰኞ አመሻሽ ላይ የሊዋርድ ደሴቶችን ይመታል ።

ባሳለፍነው ወር ኢርማ ከባድ አውሎ-ነፋስ ይህን አካባቢ እንዳልነበር አድርጎት ነበር፣ አሁንም በተመሳሳይ አቅጣጫ ማሪያ እየመጣ ይገኛል።

ጓዲሎፔ፣ ዶሚኒካ፣ ቅዱስ ኪትስና ኔቪስ፣ ሞናትሴራት እና ማርቲኒክ በተባሉ ደሴቶች የከባድ አውሎ-ነፋስ ማስጠንቀቂያ ተላልፎላቸዋል።

ከነዚህ ደሴቶች መካከል አንዳንዶቹ በኢርማ ከደረሰባቸው ጉዳት ገና አላገገሙም።

ይህ ምድብ 5 ተብሎ የነበረው አውሎ-ነፋስ የ37 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አውድሟል።

የአሜሪካው ብሔራዊ የአውሎ-ነፋስ ጣቢያ እንዳለው አሁን ደግሞ ማሪያ በስዓት 137 ኪ.ሜ እየተጓዘ ይገኛል።

ጣቢያው እንዳስጠነቀቀው ይህ አውሎ-ነፋስ አደገኛና ጠንካራ በሆነ ማዕበል የተጀበ ሲሆን የውሃን አካል ከ1.5-2.1 ሜትር ድርስ ከፍ ያደርጋል።

በተለይም በማዕከላዊና በደቡባዊ ሊዋርድ እሰከ 20 ኢንች ሊደርስ የሚችል ዝናብ ሊኖር ይችላል።

ይህም በደሴቶቹ ላይ አደገኛ ጎርፍና የመሬት መሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል ትንበያ አስቀምጧል።

ባለፈው ወር በተከሰተው በኢርማ አውሎ ነፋስ በብሪታንያዋ ቨርጅን ደሴቶች የነበሩ ቤቶች ሁሉ ወድመዋል።

አካባቢውን የጎበኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን ጉዳቱን ከአንደኛው የአለም ጦርነት በኋላ ከተመለከቷቸው ምስሎች ጋር አመሳስለዋቸዋል።

በአሜሪካም 11 ሰዎች ሲሞቱ ወደ 6.9 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶችም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል።