ከድንበር ውዝግብ በኋላ ቻይናና ህንድ በውሃ ምክንያት ተፋጠዋል።

በጣም የሞላ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በየዓመቱ በዝናብ ወቅት ወንዙ በጣም ይሞላና በሰሜን ምስራቅ ሕንድ እና በባንግላዴሽ ትልቅ ኪሳራ ያስከትላል።

ቻይናና ሕንድ አሁንም ሊከሰት የሚችል የድንበር ጦርነትን ቢያረግቡም ፍጥጫው ግን ወደ ሌላ አከራካሪ አለመግባባት አምርቷል፤ ውሃ።

በዚህ የዝናብ ወቅት በስምምነታቸው መሠረት ዴልሂ ከቻይና ስለ ብራሕማፑትራ ወንዝ ማግኘት የነበረባትን የሃይድሮሎጂ ማለትም የውሃ ደረጃ እንቅስቃሴና ስርጭትን የተመለከተ የሳይንሳዊ ጥናት መረጃ እንዳልተረከበች ተናግራለች።

የእስያ ትልቁ ወንዝ የሆነው ብራሕማፑትራ ከቲቤት ተነስቶ ወደ ሕንድ ፈሶ ከዚያም ወደ ባንግላዴሽ በማምራት ከጋንጂዝ ጋር ተቀላቅሎ በቤንጋል ሠርጥ ያበቃል።

ቤይጂንግ የሃይድሮሎጂ ጣቢያዎቹ ማሻሻያ እየተደረገላቸው በመሆኑ ምንም አይነት መረጃ ማቅረብ እንደማይቻል ኣሳውቃለች።

ቢቢሲ እንደሚለው ግን ባንግላዴሽ ከብራሕማፑትራ ተፋሰስ የታችኛው ክፍል ላይ ያለች አገር ብትሆንም ከቻይና እስካሁን ድረስ መረጃ እየተቀበለች እንደሆነ ነው።

ይህ የወንዝ መረጃ ጠብ በቻይናና በሕንድ መካከል በሂማላያ ድንበር ተነስቶ ለሁለት ወራት የቆየውን ፍጥጫ ተከትሎ የተከሰተ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

በቻይናና በሕንድ መካከል የነበረው ግጭት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

አለመተማምን

የባንግላዴሽ የዉሃ ሀብቶች ሚኒስቴር አኒሱል ኢስላም ሞሃማድ አገራቸው ውሃን የተመለከተ መረጃዎችን ከቻይና እየተቀበለች እንደሆነ ለቢቢሲ ኣሳውቀዋል።

ለሕንድ ግን ቻይና መረጃ የማካፈሉን ተግባር ድጋሚ ትቀጥላለች የሚለው ሃሳብ አጠራጣሪ ሆኖባታል።

የቻይና ቃልአቀባይ የሆኑት ጌንግ ሽዋንግ "ይህን በተመለከተ ተገቢውን የሃይድሮሎጂ መረጃ መስጠት መቀጠል መቻል ወይም አለመቻላቸው ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የማሻሻያ ሥራ ሂደት ላይ ተወሰነ ነው።"

ሕንድና ከቻይና ጋር ስለ ብራሕማፑትራ ወንዝ የፍሰት መረጃዎችን ለመቀበል ስምምነት ውስጥ ላይ የደረሰችው ከብዙ ዓመታት ጥረት በኋላ ነው።

በድርቅ ወቅቶች ቻይና የብራሕማፑትራን ውሃ ወደ ደረቅ ክልሎችዋ ታዛውራለች ብለው ስለሚጠረጥሩ ዴልሂ የወንዙን ውሃ ፍሰት መረጃ ዝናብ በሌለበት ወቅትም እንዲሰጣት ጥያቄ አቅርባለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ወንዙ ወደ ባንግላዴሽ ከመውረዱ በፊት ወደ ሕንድ ይፈሳል።

ቤይጂንግ በወንዙ ላይ ብዛት ያላቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ግድቦችን ገንብታለች።

በመቀጠልም ውሃውን እንደማይገድቡ ወይም አቅጣጫ እንደማያስቀይሩና ከወንዙ በታች በኩል ያሉ አገራትን ፍላጎቶች እንደማይጻረሩ ተናግረዋል።

በቅርብ ዓመታት በተለይም በሰሜን ምሥራቅ ሕንድ ውስጥ ቻይና በአንድ ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ትለቃለች የሚል ፍራቻ አለ።

ወንዙ ሰፊ ቦታን ለሚሸፍንባቸው አካባቢዎች አንዱ በኣሳም ሲሆን የዲበሩጋር ነዋሪዎችም የብራሕማፑትራ ውሃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምርና ሲቀንስ እንዳዩ መስክረዋል።