ማሪያ አውሎ-ንፋስ ዶሚኒካንን ከመታ በኋላ ሀይሉን ጨምሮ እየገሰገሰ ነው

የማሪያ ማዕበል አዘል አውሎ ንፋስ ጥፋት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ማሪያ የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሎ-ንፋስ በሰዓት 260 ኪሜ እየተጓዘ የካሪቢያን ደሴቷን ዶሚኒካ ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ወደ ደረጃ አምስት ከባድ አውሎ ንፋስ ከፍ ብሎ የብሪታንያ ቨርጅን ደሴቶችን እና ፖርታሪኮን በማቅናት ላይ ይገኛል።

አውሎ-ንፋሱ በሰው ህይወትና ንብረት አደጋ በሚያስከትለው ምድብ አምስት ውስጥ ተመድቧል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሩዝቨልት ስኬሪት በፌስቡክ ገጻቸው አውሎ-ንፋሱ የቤታቸውን ጣራ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ቤታቸው በጎርፍ መጥለቅለቁን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ በኋላ ላይ በነፍስ አድን ሠራተኞች ከአደጋው መትረፋቸውን ጽፈዋል።

አውሎ-ንፋሱን ተከትሎ የዶምኒካን አውሮፕላን ማረፊያና ወደቦች ዝግ ሆነዋል።

ማሪያ አውሎ-ንፋስ ከቀናት በፊት በተከሰተውና ኢርማ የተሰኘው አውሎ-ንፋስ በሄደበት አቅጣጫ በመጓዝ ላይ ይገኛል።

በማርቲኒክ ደሴት ከፍተኛ ደረጃ ያለው ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ በጉዋደሉፕ ደግሞ ሰዎችን ከአደጋ ቀጠና ማውጣት ተጀምሯል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ሀሪኬይን ማሪያ የሚያደርሰውን ጥፋት እያጠናከረ ይገኛል

የአውሎ-ንፋስ ማስጠንቀቂያ የተሰጠባቸው አካባቢዎች

  • ፖርቶሪኮ፡ የኢርማ አውሎ-ንፋስ ከፍተኛ ጉዳት ባያደርስባትም ፖርቶሪኮ ዜጎቿ ከማሪያ አውሎ-ንፋስ ራሳቸውን እንዲተብቁ አስጠንቅቃለች
  • የአሜሪካ ቨርጂን ደሴትና የብሪታንያ ቨርጂን ደሴት፡ ሁለቱም አካባቢዎች በኢርማ አውሎ-ንፋስ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካዋ ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል። የእንግሊዝ ባለስልጣናት አሁኑ አውሎ-ንፋስ ከቀደሙ ጋር ተጨምሮ አደጋው ከፋ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

ለሴንት ኪትስና ኔቪስ፣ ሞንትሴራት እና ሴንት ሉሲያ የአደጋ ማስጠንቀቂያ የተላለፈባቸው ሲሆን በሴንት ማርቲን፣ሳባ፣ ሴንት ኢዩስታቲየስና አንጉይላ ደግሞ የቁጥጥር ሥራ ተጀምሯል።

እነዚህ አካባቢዎች ከወር በፊት 37 ሰዎችን በገደለውና በቢሊዮን ዶላር ንብረት ባወደመው በኢርማ አውሎ-ንፋስ የተመቱ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚንስትር ሩዝቨልት ስኬሪት በፌስቡክ ገጻቸው አውሎ-ንፋሱ የቤታቸውን ጣራ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን አስታውቀዋል

የአሜሪካ ብሔራዊ አውሎ-ንፋስ ማዕከል የአሁኑን አውሎ-ንፋስ ከምድብ ሁለት ወደ ምድብ አምስት በማሳደግ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በማለት ትንበያውን ማስቀመጡ ይታወሳል።

እንደትንበያው ከሆነ አውሎ-ንፋሱን ተከትሎ ሊኖር የሚችለው ከባድ ዝናብ ጎርፍና መሬት መንሸራተት ሊያስከትል ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

72 ሺህ ህዝብ እንዳላት በሚነገርላት ዶሚኒካ በአውሎ-ንፋሱ ምክንያት መሬት ናዳም ተከስቷል።

የፎቶው ባለመብት, NASA

የምስሉ መግለጫ,

ማሪያ አውሎ-ንፋስ ከቀናት በፊት በተከሰተውና ኢርማ የተሰኘው አውሎ-ንፋስ በሄደበት አቅጣጫ በመጓዝ ላይ ይገኛል

በሁሉም አሃገሪቱ ወደቦችና አውሮፕላን ማረፊያዎች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን ሰዎችም ወደ መጠለያዎች እንዲሄዱ ጥሪ ቀርቧል።

መቀመጫውን በመዲናዋ ሮሴዩ በማድረግ የሚሰራው ከርቲስ ማቲው የተባለ ጋዜጠኛ ሁኔታው በፍጥነት ወደ መጥፎ ደረጃ ተሸጋግሯል ሲል ለቢቢሲ ዘግቧል።

"መንገድ ላይ ምን እየተፈጠረ መሆኑን እንኳን ለማየት አልቻልንም። ንፋሱ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ከውጭ ያለውን ድምጹን እየሰማን ነው። ጉዳቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አላወቅንም። ሳስበው ግን ለዶሚኒካን ጥሩ አይመስልም" ሲል ሃሳቡን አካፍሏል።

ማርቲኒክ አደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያዋን ወደ 'አደገኛ' ከፍ በማድረግ ዜጎቿ ወደ መጠለያዎች እንዲያቀኑ ጠይቃለች።

በጉዋዴሉፕ ደግሞ ትምህርት ቤቶችና የህዝብ መገልገያ ቦታዎች የተዘጉ ሲሆን አደገኛ ጎርፍ ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል። በዝቅተኛ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የፈረንሳይ መንገሥት ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በኢርማ አውሎ-ንፋስ ጉዳት በደረሰባት የብሪታንያ ቨርጂን ደሴት 1300 የሚሆኑ የእንግሊዝ ወታደሮች በተጠንቀቅ የቆሙ ሲሆን ተጨማሪ ሃይልም ወደ አካባቢው ተሰማርቷል።

ኢርማ የተሰኘው አውሎ-ንፋስ አሜሪካን ያጠቃ ሲሆን የሰዎችንም ህይወት ነጥቋል። በፍሎሪዳ፣ ጆርጂያ፣ ሰሜን ካሮላይና፥ ደቡብ ካሮላይናና አላባማ የሚኖሩ 6.9 ሰዎችም ኤሌክትሪክ አገልግሎታቸው ተቋርጦ ነበር።