የኒውክለር ጦርነትን የቀለበሰው ስታኒስላቭ ፔትሮቭ

ስታኒስላቭ ፔትሮቭ
አጭር የምስል መግለጫ ስታኒስላቭ ፔትሮቭ

የቀዝቃዛው ጦርነት በተፋፋመበት ወቀት የኒውክለር ጦርነትን የቀለበሰው የቀድሞው የሶቪየት ህብረት ወታደር በ 77 ዓመቱ ሞቷል።

ስታንሲላቭ ፔትሮቭ በ1983 በሩሲያ የኒውክለር ቅድመ ማስጠንቀቂያ ማዕከል ውስጥ በስራ ላይ እያለ ነበር ኮምፒዩተሮች በስህተት የአሜሪካ ሚሳኤሎች እየመጡ እንደሆነ የሚገልጽ ምልክት ማሳየት የጀመሩት።

እሱ ግን ይህ ማስጠንቀቂያ ሃሰተኛ ማንቂያ ነው በሚል ለአለቆቹ ሪፖርት ሳያደርግ ቀረ።

ይህ ከዓመታት በኋላ የታወቀው ውሳኔው ምናልባትም ዓለምን ከኒውክለር ጦርነት ታድጓል።

ፔትሮቭ በአውሮፓውያኑ 2013 ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ መስከረም 26, 1983 ጠዋት የኮምፒዩተሮቹ ማስጠንቀቂያዎ እንዴት እንደደረሱት አብራርቶ ነበር።

በንግግሩም '' መረጃዎቹ ሁሉ እየተካሄደ ያለ የሚሳዔል ጥቃት እንዳለ የሚያሳዩ ነበሩ፤ ሪፖርቱን ለዋና አዛዡ ብልክለት ማንም ምንም መናገር አይችልም ነበር፤ ስህተቱን አንድ ጊዜ ከሰራሁ ደግሞ ማንም ሊያርመው እንደማይችል አውቅ ነበር፤ የሚጠበቀብኝም ስልክ መደወል ብቻ ነው፤ ነገር ግን መንቀሳቀስ አልቻልኩም ፤በትኩስ መጥበሻ ላይ የተቀመጥኩ ያህል ነበር የተሰማኝ'' ብሎ ነበር

ምንም እንኳን የወሰደው ስልጠና እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ወዲያውኑ የሶቪየት ወታደሮችን ማናገር እንዳለበት ቢያዝም ፔትሮቭ ግን በምትኩ በጦሩ ዋና መስሪያ ቤት ተረኛ የሆነው ሰው ጋር ደውሎ ኮምፒዮተሮቹ ችግር እንደገጠማቸው መናገርን መረጠ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሶቪየት ህብረትና አሜሪካ አንዳቸው ሌላኛውን ለመምታት የተዘጋጁ ግዙፍ የነውክለር ጦር መሳሪያዎች ነበሯቸው

ፔትሮቭ ተሳስቶ ቢሆን ኖሮ ከደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያው የኒውክለር ፍንዳታ ይሰማ ነበር።

" ከ 33 ደቂቃዎች በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ አወቅኩ፤ ትክክለኛ ጥቃት ቢኖር ኖሮ አውቅ ነበር፤ ያኔ ትልቅ እረፍት ነበር የተሰማኝ'' በማለት ትውስታውን አጋርቷል።

ከዚያ በኃላ የተካሄዱ ምርመራዎችም የሶቪየት ሳተላይቶች በደመና ውስጥ የሚታዩ የጸኃይ ነጸብራቆችን ከአህጉር አቋራጭ ተመዘግዛጊ ሚሳኤሎች ጋር አመሳስለዋቸው እንደነበረ አረጋገጡ።