አፍሪካ ውስጥ ጥሬ ገንዘብ ሊቀር የሚችልበት ሀገር የት ይመስልዎታል? ሶማሊላንድ?

በሶማሌላንድ ሀርጌሳ የተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም ግብይት ሲያደርጉ Image copyright Matthew Vickery
አጭር የምስል መግለጫ በሶማሌላንድ ሀርጌሳ የተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም ግብይት ሲያደርጉ

ከሶማሊያ እአአ በ 1991 ተለይታ የራሷን ነፃ ሀገር የመሰረተች ቢሆንም በኣለም አቀፉ ማህበረሰብ ችላ ተብላ ቆይታለች። ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ መድረክ የምትታወቅበት ነገር ባይኖራትም በጥሬ ገንዘብን መገበያየትን ለመቀየር በዝግጅት ላይ ነች።

በዋና ከተማዋ ሀርጌሳ በሰፈር ሱቆችም ውስጥ፣ በመንገድ ዳር ወይም በትልልቅ መደብሮች በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚደረጉ ክፍያዎች የአገሪቷ መደበኛ መገበያያ መንገድ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። በሶማሊላንድ ውስጥ ያሉ የሱቅ በደረቴዎችና ሸማቾች ኢንተርኔት በማያስፈልገው ቀላል ፕሮግራም ይገበያያሉ።

"በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ የሚከፍሉት የተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም ነው።" በማለት የሚናገረው ኡመር በአንደኛው እጁ ክፍያ ለመፈፀም እየሞከረ "በጣም ቀላል ሂደት ነው።" በማለትም በተጨማሪ ይናገራል። በቴክኖሎጂ ያደጉ ሀገራትም ሆነ ያላደጉ ሀገራትን ግብይትን ጥሬ ገንዘብን በማያካትት መንገድ ለማድረግ በሂደት ላይ ቢሆኑም፤ የሶማሊላንድ ከፍተኛ ለውጥ ለየት ተብሎ የሚታይ ክስተት ነው።

ሶማሊላንድ ጥሬ ገንዘብ ከሌለበት ግብይት ግር የተዋወቀችው፤ የመገበያያዋ ሽልንግ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ስለመጣ ነው። አሁን ባለው ምንዛሬም 1 የአሜሪካን ዶላር በ 9 ሺህ የሶማሊያ ሽልንግ ይመነዘራል። ከጥቂት አመታት በፊት ይህ የምንዛሬ በግማሽ ያነሰ ነበር። የመገበያያ ሽልንግዋን እአአ በ1994 ያስተዋወቀችው ሶማሊላንድ፤ በዚያን ጊዜ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር በነበረው ጦርነት የጦር መሳሪያን ለመግዛት አገልግሎት ላይ ውሏል።

ከጊዜም በኋላ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ፖለቲከኞችም በመጣ ከፍተኛ ፍላጎት ሽልንግ የሀገሪቷ መገበያያ ሆኗል። በዓመታት ውስጥ ሽልንግ በማሽቆልቆል ላይ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ እቃ ለመግዛት በሻንጣ ብር ይዞ መሄድ የሚጠይቅ ሆኗል። በተለይም በመንገድ ላይ ዶላርና ዩሮን በመቀየር የሚተዳደሩት ነጋዴዎች ብዙ ብር ለማንቀሳቀስ ቀለል ያለ ጋሪን መጠቀም ይኖርባቸዋል። ከዚህ ሸክምና ውጣ ውረድ ለመውጣት ብዙዎች በዲጂታል መንገድ መክፈልን ይመርጣሉ።

Image copyright Matthew Vickery
አጭር የምስል መግለጫ በሀርጌሳ ሽልንግ በማሽቆልቆሉ ሁኔታ ብዙዎች ግብይታቸውን በዲጂታል መንገድ እያደረጉ ነው።

ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ ባንክ ባይኖራትም ሁለት የግል ባንኮች አሉዋት። ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረው ዛድ እንዲሁም በቅርብ የተጀመረው ኢዳሀብ የተንቀሳቃሽ ስልክ ባንክ አገልግሎትን በማጠናከር ገንዘብን በቀላሉ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚዘዋወርበትን የመገበያያ ሁኔታን ፈጥሯል። በጌጣጌጥ መሸጫ ውስጥ በአስተባባሪነት ተቀጥሮ የሚሰራው የ18ቱ ዓመቱ ኢብራሂም አብዱልራህማን በሽልንግ ወርቅ ለመግዛት የመጣን ሰው እየጠቆመ "ይሄንን ወርቅ ለመግዛት በትንሹ አንድ ወይም ሁለት ሚሊዮን ያስፈልገዋል። ያንን ያህል ገንዘብ ደግሞ ተሸክሞ መምጣት ለአንድ ሰው ከባድ ነው"ይላል።

ብዙ ገንዘብ ለመያዝ ከባድ በሆነበት ሁኔታ ያለ ጥሬ ገንዘብ መገበያየት ህይወትን ቀለል እንዳደረገው ሳይታለም የተፈታ ነው። ክፍያን ለመፈፀም ቁጥሮችን የሚያስገቡ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከሻጩ ለየት ያለ ኮድ ያገኛሉ። ለዚህ ግብይት ኢንተርኔት ካለማስፈለጉም በላይ ቀለል ባሉ ስልኮችም ካርድ የመሙላትን ያህል ቀለል ብሎ ይከናወናል።

ይህ የክፍያ ሁኔታ የብዙዎችን የግብይት የቀየረ ሲሆን ከነዚህም አንዷ የ50 አመት እድሜ ያላት ኤማን አኒስ ናት። በሁለት አመታት ብቻ ከ5% ወደ 40% ሽያጭ ያደገላት ሲሆን የቀን ሽያጯም ወደ 50 ሺ ብር ደርሷል። ገንቧንም እየቆጠረች "የዛሬ ብቻ ነው"ትላለች። "ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም የግብይት ሂደቶችን ቀለል አድርጓቸዋል። ገንዘብ ወደ ዶላር ወይም ዩሮ ከመቀየር ይልቅ በሞባይል በኩል በቀላሉ ክፍያዎችን መፈፀም ይቻላል።" በማለት የምትናገረው አኒስ "በአሁኑ ወቅት የሚለምኑ ሰዎችም የሞባይል ግብይት አካውንት አላቸው።" ብላለች።

ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ለተገበያዮች ብቻ ሳይሆን በድህነት ውስጥ ላሉት አዲስ እድል እንደፈጠረ ነው። በተለይም ሶማሌላንድ ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ድርቅ በተመታችበት ወቅት ከተማ ያሉት በገጠር ላሉ ዘመዶቻቸው በቀላሉ ገንዘብ ለመላክ አስችሏቸዋል። "በድርቁ ምክንያት የምንሸጠው አልነበረንም፤ ይሄም ሁኔታ የገቢ ምንጫችንን አድርቆት ነበር። ነገር ግን ዘመዶቻችን ገንዘብ በመላክ ረድተውናል።" በማለት የሚናገረው የግመል እረኛው ማህሙድ አበዱሰላም በድርቁም ምክንያት ከአካባቢው ተፈናቅሏል። "በገጠርም የተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ አገልግሎት እንጠቀማለን" በማለትም ይናገራል።

ሻጮች በአንድ ዓመት ውስጥ የተንቀሳቃሽ ስልክ ክፍያ ከ 10-20% ወደ 50% እንዳደገ መናገራቸው ምን ያህልም ተፈላጊነቱ እየጨመረ ያሳያል። ሻጮች ብቻ ሳይሆኑ ቀጣሪዎችም በተንቀሳቃሽ ስልክ የደሞዝ ክፍያን እያከናወኑ ነው። ባለፈው ዓመት የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው 88በመቶው የሚደርሱ እድሜያቸው ከ16 ዓመት የሆኑ ሰዎች ከ 1 ሲምካርድ በላይ እንዳላቸው አመልክቷል። ጥናቱም ጨምሮ እንደሚያሳየው 81% ከተሜዎች እንዲሁም 62% የገጠር ነዋሪዎች የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ናቸው።

በዚህ ከፍተኛ ለውጥ ሁሉም ደስተኛ አይደሉም። ከሙስናም ጋር ተያይዞ የተለያዩ ማጉረምረሞች ይሰማሉ። በተለይም ሁለቱ የግል ባንኮች ያለምንም ተቆጣጣሪ በበላይነት እየመሩት በመሆናቸው መረጋጋት በሌለው ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ እንደሆነ ይነገራል። በተለያዩ ሀገራት የተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ አገልግሎት በሀገሪቷ የመገበያያ ገንዘብ ሲሆን በሶማሊላንድ ያሉት ሁለት ባንኮች የሚገበያዩት በዶላር ነው።

Image copyright AFP/Simon Maina
አጭር የምስል መግለጫ ገንዘብ በማሽቆልቆሉ ምክንያት እቃ ለመግዛትከተፈለገ በሻንጣ ብር ይዞ መሄድ ግድ እየሆነ ነው

በብዙ ክምር ሽልንግ የተከበቡት እንደነ ሙስጠፋ ሀሰን ያሉ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች "በሙስና በተዘፈቀው" የተንቀሳቃሽ ስልክ ግብይት ምክንያት፤ ከፍተኛ የሆነ ግሽበትን እየፈጠረ በአጠቃላይ ደግሞ ህገወጥ ኢኮኖሚን እያንሰራፋ ነው በማለት ይወነጅላሉ። "መንግሥት በተቻለ መጠን ይህንን የግብይትና የገንዘብ ልውውጥ እንዲቆጣጠረው ወይም እንዲያቆመው ጠብቀን ነበር።

ከተንቀሳቃሽ ስልክ ግብይት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግሮች አሉ። በሁለት ባንኮች ቁጥጥር ሥር መሆኑ ገንዘብ እያመረቱ ይመስላል። " በማለት ሀሰን ሲናገር በአካባቢው የተገኙትም ነጋዴዎች በንግግሩ ራሳቸውን በመነቅነቅ መስማማታቸውን ያሳዩ ነበር። "ትንሽም ሆነ ትልቅ ነገር ለመግዛት ብዙዎች የተንቀሳቀሽ ስልኮቻቸውን ስለሚጠቀሙ ለገንዘብ ለግሽበት ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ነው። ይሄም የሚከናወነው በሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ላይ ሳይሆን በዶላር ነው። " ይላል።

ምንም እንኳን ሀሰን በከፍተኛ ሁኔታ ቢያማርርም እርሱም ከሸማቾች በዶላር ገንዘብ ለመቀበል የተንቀሳቃሽ ስልክን ይጠቀማል። "በእውነቱ ከሆነ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ግብይትን ቀለል አድርገውታል። ሰዎች በቀላሉ ገንዘብ እንዲልኩልኝም አስችሎኛል። "በማለት እውነቱን የሚናገረው ሀሰን "ይህ ሁኔታ ግን እንደእኔ ላሉ ገንዘብ በመቀየር ለሚተዳደሩ ሰዎች ምን ማለት ነው? አላውቅም"።