‘‘ለ16 ዓመታት የታሰረው አባቴ ዘወትር ለማዕድ ስንቀርብ አብሮን እንዳለ አስባለሁ’’

አጭር የምስል መግለጫ አቤ ስዩም በአባቷ እቅፍ ውስጥ

የታዋቂው ኤርትራዊ ጋዜጠኛና ፎቶግራፈር ታጋይ ስዩም ፀሃየ ታፍኖ ተወስዶ እንደወጣ ከቀረ 16 ዓመታት ሆኑት። የበኩር ልጁ አቤ ስዩም፤ የተያዘበትን መስከረም 8ን በማስታወስ "አባቴ ናፍቆኛል፤ እኔና እህቴ እንዲሁም እናቴ ስዩሜ ናፍቆናል። በተለይ በዚች ወር ናፍቆታችን በጣም ይብሳል።'' በማለት ጥልቅ ስሜትዋን ትገልጻለች።

በኤርትራ ሚኒስትሮችና ጀነራሎች የሚገኙበት 11 ከፍተኛ ባለስልጣናት በታሰሩበትና የግል ጋዜጦች በአዋጅ ተዘግተው 11 የጋዜጣ አዘጋጆች ለእስር ሲዳረጉ ታጋይ ፎቶግራፈር በሚል ተቀጥላ ስም የሚጠራ እውቁ ጋዜጠኛ ስዩም ፀሃየ አንዱ ነው።

እርሱም ሆነ አብሮውት የታሰሩት ጋዜጠኞች፣ ሚንስትሮችና ጀነራሎች እስካሁን ድረስ በይፋ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት አልቀረቡም። ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ወዳጆቻቸው እንዲያዩዋቸው አልተፈቀደላቸውም።

የስዩም ልጅ አቤ፤ አባቷ ሲታሰር የሁለት ዓመት ህፃን ነበረች።

አጭር የምስል መግለጫ አቤና በይሉላ

የስዩም ባለቤት ሳባ ገብረመስቀል ባለቤቷ ''በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት መካከል የተፈጠረው ልዩነት ለዴሞክራሲያዊ ጉዞኣችን መነሻ ሊሆን ስለሚችል፤ መሪዎቻችንም ስለሚቀራረቡ ብዙ መጨንነቅ አያስፈልግም።'' ሲል ለግል ጋዜጦች በፃፈው አስተያየት ምክንያት በቁጥጥር ሥር ሲውል የአቤን ታናሽ እህት በይሉላን እርጉዝ ነበር።

በልጅነቷም ሆነ ካደገች በኋላ የአባቷን ፍቅር ያጣችው ኣቤ "ስዩምን ቀንና ሌሊት እናስበዋለን፤ ሲታሰር ልጅ ስለነበርኩ በትንሹ ነው የማስታውሰው። በፎቶ ብቻ የምታውቀው ታናሽ እህቴ በይሉላ ግን የእኔን ያህል ዕድል ስላላጋጠማት አዝንላታለሁ። ስዩምን አንድ ቀን ከነሙሉ ጤንነቱ አግኝተን እንዴት እንደምንወደው ለመንገር ሁሌም እመኛለሁ" ትላለች በናፍቆት ተውጣ።

መስከረም 18 2001 (እአአ) የኤርትራ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተቀየረበት ቀን ነው።

መነሻ ሁኔታዎች

ከ1998 እስከ 2000 (እአአ) ከተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ በ2001 ላይ የጦርነቱ አጀማመርና አያያዝን በተመለከተ በኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ።

ትንሽ ቆይቶም ጂ-15 እየተባሉ የሚታወቁት 15 ሚንስትሮችና ጀነራሎች የሚገኙበት ከፍተኛ የመንግሥትና የሕዝባዊ ግንባር ባለሥልጣናት፤ በጉዳዩ ላይ ቅሬታቸውን በመግለፅ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኣፈወርቂ ስብሰባ እንዲጠሩ ጥያቄ አቅርበው ነበረ።

ቢሆንም ግን ፕሬዝዳንቱ "እየተሳሳታችሁ ነው" በማለት ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት። ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣናቱ ለሕዝቡና ለግምባሩ ይፋዊ ደብዳቤ ፅፈው በተለያዩ የግል ጋዜጦችም ላይ ስለጉዳዩ ቃለ-ምልልስ አደረጉ።

ከጊዜ በኋላም አለመግባባቱ እየከረረ በመምጣቱ መስከረም 18/2001 (እአአ) ላይ መንግሥት የግል ጋዜጦች መዘጋታቸውን በይፋ በማወጅ ሃገር ውስጥ የተገኙትን 11 ጋዜጠኞችና በርካታ የጂ-15 ቡድን ሃሳብ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ። ከታሰሩም እነሆ 16 ዓመታት ተቆተሩ። ነገር ግን እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም፤ ጥፋታቸውም ምን እነደሆነ ለሕዝብ በይፋ አልተገለፀም። ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ ወዳጆቻቸው እንዲያዩቸውም አልተፈቀደላቸውም።

አጭር የምስል መግለጫ ለ16 ዓመታት እስር ላይ የሚገኘው ታጋይና ፎቶግራፈር ስዩም ፀሃየ

አቤ እድሜዋ አሁን 18 ዓመቷ ሲሆን አባቷ በሙያው የበኩሉን በመወጣቱ፣ አመለካከቱን እና ሐሳቡን በጋዜጣ ላይ በመፃፉ ብቻ ያለፍትህና ፍርድ ለ16 ዓመታት በዘብጥያ ውስጥ ማሳለፉ ሁሌም ያሳስባታል።

በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት ጄነቭ በሚገኘው በዓለም-አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት በመቅረብ ኣባቷ ፍትህ እንዲያገኝ ስታመለክት ቆይታለች።

"አባቴን የሚያውቁ ሰዎች፤ አባቴ የተቸገሩን የሚረዳ፣ ታታሪና ጠንካራ፤ እንዲሁም ለፈተና እጁን የማይሰጥ ሃቅን የሚወድ እንደነበረ ይነግሩኛል። በዚህም እኮራለሁ። ካደግኩ ወዲህ አባቴ የታሰረበትን ምክንያት ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ለመረዳት እንደቻልኩት፤ በተወሰኑ የኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር "ጉዳዩን በመግባባት መፍታት ኣለባችሁ" ብሎ በመፃፉ ነው።''

''አባቴ ባለፉት 16 ዓመታት በመካከላችን ባይኖርም፤ በምናቀርበዉ ማዕድ መካከል በፀሎት ስለምናስታውሰው በመንፈስ ሁሌም ከኛ ጋር ነው።'' ትላለች።

ወደፊት አንድ ቀን አባቷን እንደምታገኘው ተስፋ የምታደርገው አቤ ''ሳገኘው እንደምትመኘው ጎበዝ ተማሪ ሆኜልሃለው ብዬ ላስደስተው ስለምፈልግ ትምህርቴን በጥንካሬ እየተከታተልኩኝ ነው። እህቴንም በዚሁ መንፈስ እያነፅኳት ነው።''

በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደምትናገረው አሁንም ደግማ እንደምትለው የኤርትራ መንግሥት መሪዎችን ''እባካችሁ! ልጆቻችሁን በእኛ ቦታ አስቀምጡና ለማየት ሞክሩ። ልጆቻችሁ የወላጅን ፍቅር ተጠምተው እንዲያድጉ ተፈቅዱ ነበር? እባካችሁ ልባችሁ ይራራ'' በማለት አባቷ እንዲፈታላት ትማፀናለች።