በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከሃምሳ ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

ተፈናቃዮች ያረፉባቸው ድንኳኖች
የምስሉ መግለጫ,

ተፈናቃዮች ያረፉባቸው ድንኳኖች

ሳምንት በፊት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በአስር ዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እየተፈናቀሉ ነው።

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከሃምሳ ሺህ በላይ መድረሱንና ለተፈናቃዮቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስታውቋል።

ለነዋሪዎቹ መፈናቀል ምክንያት በሆነው በምሥራቅ ሐረርጌ በሚገኙ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፤ አስራ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከሞቱት ሰዎች መካከል አስራ ሁለቱ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ስድስቱ ደግሞ ኦሮሞዎች ናቸው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ግን የሞቱት ሰዎች ቁጥሩ ከሰላሳ በላይ መሆኑን በመግለፅ፤ ባለፈው ሳምንት በክልል ደረጃ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፅሟል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት ግጭቱ የጀመረው የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የቀድሞውን ጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪን፣ አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባልንና የኦሮሚያ ክልል ሰራተኛን ይዘው ካሰሩ በኋላ ነበር።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት የተያዙት ሰዎች ሌሊቱን በተፈፀመባቸው ድብደባ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ፤ በምሥራቅ ሃረርጌ ከተሞች ውስጥ የተካሄደው የጎዳና ላይ ተቃውሞ በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ግጭት እንዲነሳ አድርጓል።

ግድያውን ያወገዙት አቶ አዲሱ ''ወንጀለኞቹን ለፍርድ ለማቅረብ አስፈላጊው ነገር እየተከናወነ ነው'' ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ኦሮሚያንና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎችን በሚያዋስኑ በርካታ አጎራባች መንደሮች ግጭቶች ተከስተዋል። የኦሮሚያ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስና የክልሉ የሚሊሻ ኃይል እንዲሁም ከሶማሊያ ሪፐብሊክ የመጡ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ኦሮሚያ ክልል ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈፅመው ሰዎችን ገድለዋል።

በተጨማሪም አቶ አዲሱ እንዳሉት በጥቃቱ ከተሳተፉት መካከል አንድ ከሶማሊያ ሪፐብሊክ የመጣ ወታደር እንደተያዘና በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ፀጥታ ኃይል ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ በኩል ያሉ ባለሥልጣናት ግን ስለግጭቱ የተለየ ምላሽ ነው የሰጡት። የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አማካሪ የሆኑት አቶ ሞሃመድ ቢሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ ክልሎች መካከል በሚገኙ አጎራባች አካባቢዎች በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቱን የፈፀመው የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ነው ብለዋል።

''በአካባቢዎቹ በሚኖሩ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሶማሌዎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ፈፅመዋል'' ሲሉ አክለዋል።

በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ከሶማሌ ክልል የሚመጡ ሰዎችን የያዙ የጭነት መኪናዎችን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ነው።

ልጁንና ሚስቱን ይዞ ከጅጅጋ ከተማ የሸሸው ሃብዱልሃኪም ሞሃመድ ካሚል ትናንት ባቢሌ ከተማ ገብቷል። ሃብዱልሃኪም ለቢቢሲ እንደተናገረው ''የሶማሌ ክልል ፖሊሶች በከተማዋ የሚኖሩ ኦሮሞዎችን እያጉላሉ ሲሆን ጎረቤቶቻችን ሳይቀሩ ለጥቃት ተነስተውብናል።''

ጅጅጋ ውስጥና በሌሎች የሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኦሮሞዎች ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነም ተናግሯል።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይም ባልደረቦቻቸው ከፌደራል መንግሥትና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን፤ በሶማሌ ክልል የቀሩ ሰዎችን ችግር ሳይገጥማቸው ለማስወጣት እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ይህ ግጭት ከኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ በሶማሌላንድ ዋና ከተማ ውስጥም ተፅፅኖ እንደፈጠረ በሃርጌሳ ከተማ ነዋሪ የሆነው ካሊድ ኢማም ለቢቢሲ በስልክ ተናግሯል። በውጤቱም በከተማዋ የሚኖሩ ኦሮሞዎች ኢላማ በመሆናቸው ሥጋት ላይ መውደቁን ተናግሯል።