ከምድረ-ገጽ የመጥፋት ሥጋት በሰውነት መጠን ይወሰናል

ዝሆንና ወፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለማችን ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ በመጠን ግዙፎቹና ትናንሾቹ እንስሳት ከምደረ ገጽ የመጥፋት ስጋት ይበልጥ ተጋርጦባቸዋል ይላል- አዲስ የወጣ ጥናት

እንደጥናቱ የጀርባ እጥንት ያላቸው እንስሳት የመጥፋት ተጋላጭነታቸው በሰውነታቸው መጠን ይወሰናል፤ በጣም ትልቅ ወይም ትናንሽ ካልሆኑት ይልቅ በሁለቱም ጫፍ ያሉት ለሞት የተጋለጡ ናቸው።

ከፍተኛ ክብደት ያላቸው በአደን ስጋት ውስጥ ሲወድቁ ትንንሾቹ ደግሞ በአየር መበከልና በማረፊያ ዛፎች መመናመን ምክንያት ህልውናቸው እየተፈተነ ነው።

"ከሁሉም የሚተልቁት የጀርባ አጥንት ያላቸው እንስሳት ከምንም በላይ በቀጥታ በሰዎች ይገደላሉ'' ይላሉ በኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ የአጥኚ ቡድኑ መሪ የሆኑት ፐሮፌሰር ቢል ሪፕል።

"ትንንሾቹ ደግሞ ለእነርሱ ምቹ የሆኑ መኖሪያዎች በጣም ውሱን እየሆኑ ነው፤ ይሄ ደግሞ የመጥፋት አደጋን የመተንበይ ያክል አደገኛ ነው''

የፎቶው ባለመብት, Jurgen Leckie

የምስሉ መግለጫ,

'ሃመርሄድ' የሚባለው ሻርክ በህገወጥ አጥማጆች ምክንያት አደጋ ላይ ወድቋል

ጥናቱ እንደሚለው የእንስሳቱ የሞት መጠን በሰውሰራሽ ምክንያቶች በርካታ እንስሳት ከምድረገጽ የሚጠፉበት ዘመን እየተቃረበ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ታዲያ ለዚህ ምክንያቶቹ ምንድናቸው ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መፈለጉ አልቀረም።

የተገኘው አንድ ፍንጭ ደግሞ የስውነት መጠናቸው ነው፤ በአጥቢ እንስሳትና በወፎች ላይ የተደረገው ጥናት የሚያሳየው ግዙፍ ሰውነት ያላቸው ለመጥፋት እየተቃረቡ መሆኑን ነው።

አጥኚዎቹ በሺዎች በሚቆጠሩ ወፎች ፣ በአጥቢና ተሳቢ እንስሳት እንዲሁም በየብስና በውሃ በሚኖሩ እንስሳት ዙሪያ መረጃ ሲያጠናቅሩ በግዙፎቹና ትናንሾቹ እንስሳት ከሌሎቹ ጋር ሊነጻጸር የማይችል የሞት መጠን አስተውለዋል።

"በሚያስገርም ሁኔታ የጅርባ እጥንት ካላቸው እንስሳት ግዙፎቹ ብቻ ሳይሆኑ ትንንሾቹም በትልቅ አደጋ ላይ መሆናቸውን ተረዳን '' ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

የፎቶው ባለመብት, Dave Young

የምስሉ መግለጫ,

ይህ እንቁራሪትም ብዛቱ እየተመናመነ መጥቷል

እንደ ዝሆን ፣ አውራሪስና እንበሳ ያሉ ሞገስ ያላቸው እንስሳት ለዘመናት የመከላከያ ጥረቶች ማዕከል ሆነው ቆይተዋል።

ሆኖም እንደ አሳነባሪ፣ የሶማሊያ ሰጎንና የቻይና ግዙፍ እንሽላሊት መሰል ተሳቢዎች እንዲሁም ሌሎች የአሳ፣የወፍና የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች ትኩረት ተነፍጓቸዋል።

በተመሳሳይ የእንቁራሪትና የአይጥ ዝርያዎችም ቸል እየተባሉ ነው።

"እንደሚመስለኝ ስለትንንሾቹ ዝርያዎች ከሁሉ አስቀድመን ግንዛቤ መስጠት አለብን፤ ምክንያቱም ትልልቆቹ ናቸው ሁልጊዜም የሰዎችን ትኩረት የሚስቡት'' ይላሉ ፕሮፌሰር ሪፕል።

ከአሜሪካ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከስዊዘርላንድና ከአውስትራሊያ የተውጣጡት የጥናቱ አዘጋጆች ከ25,000 በላይ የሚሆኑ ዝርያዎችን የክብደትና የሞት መጠናቸውን ግንኙነት አነጻጽረዋል።

ከነዚህ ውስጥ 4000 የሚሆኑት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው አረጋግጠዋል።

የጅርባ አጥንት ያላቸው ግዙፎቹና ትንንሾች እንስሳት ደግሞ በመሬትም ኖሩ በውሃ ውስጥ ከምደረ ገጽ የመጥፋት ስጋት ላይ ናቸው።

ለግዙፎቹ እንስሳት ስጋት የሆኑት

  • ቁጥጥር የሚደረግባቸውና የማይደረግባቸው አሳ አጥማጆች
  • ለአደን፣ ለምግብ፣ ለንግድና ለመድኃኒትነት በሚል መገደላቸው

ትንንሾቹ እንስሳት ላይ የተደቀኑ ስጋቶች

  • የሃይቆች፣ወንዞችና የጅረቶች መበከል
  • እርሻ
  • የደን መመናመን
  • ልማት

የፎቶው ባለመብት, Factcatdog

የምስሉ መግለጫ,

የባራቪያ አይጠ-መጎጦች ከፍተኛ የመጥፋት ስጋት ውስጥ ናቸው

አጥኚዎቹ እንደሚሉት እንስሳቱን ከስጋት ለመጠበቅ የተለያዩ አማራጮች ቢኖሩም በአስቸኳይ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮችም አሉ።

"ከምንም በላይ የዓለምን የዱር እንስሳት ስጋ ፍጆታ መቀነስ አደኑን፣ አሳ ማጥመዱንና፣ የደን መመናመኑን ለመቀነስ ወሳኝ እርምጃ ይሆናል ፤ ያም ሆነ ይህ ግን ሰዎች ለእንስሳቱ ሞት ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ናቸው''