ለከባድ አውሎ ነፋሶች ማነው ስም የሚያወጣው?

መብረቅ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ

የፎቶው ባለመብት, Stuart Edwards

ስለከባድ አውሎ ነፋሶች ብዙ ጊዜ ዜና ላይ ይነገራል፤ ነገር ግን ለምን ስም እንደሚሰጣቸውና ስያሜው እንዴት እንደሚወሰን ጠይቀዉ ያውቃሉ?

ለምን ስም እንዲኖራቸው አስፈለገ?

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ,

ለከባድ አውሎ ነፋሶች ስያሜ መስጠት ሰዎች የበለጠ እንዲያውቋቸውና የአደገኝነት መጠናቸውንም እንዲረዱት ያደርጋል

በትሮፒካል አካባቢ የሚከሰቱ ሄሪኬን፣ ሳይክሎን ወይም ታይፉንን የመሳሰሉ ከባድ አውሎ ነፋሶች ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ በመሆናቸው ተመራማሪዎች ለሚያደርጉት ክትትል እንዲረዳ ስም ይሰጣቸዋል።

ቀደም ሲል አውሎ ነፋሶቹ የተከሰቱበትን ዓመት መሰረት በማድረግ ይከታተሏቸው ነበር። ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች በዓመት ውስጥ 100 የሚደርሱ አውሎ ነፋሶች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ስም መስጠቱ ለአጥኚዎቹ አንዱን ከአንዱ ለመለየት በጣም ቀላል አድርጎላቸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የሚትዮሮሎጂ መሥሪያ ቤት እንደሚለው ለከባድ አውሎ ነፋሶች ስያሜ በመስጠት ሰዎች የበለጠ እንዲያውቋቸው ከማድረጉ በተጨማሪ የአደገኝነት መጠናቸውንም እንዲረዱት ያደርጋል።

ማነው የአውሎ ነፋሶቹን ስም የሚወስነው?

የፎቶው ባለመብት, PA

በቀጣይ ዓመት ሊከሰቱ ለሚችሉ አዳዲስ ከባድ አውሎ ነፋሶች ስያሜ ለመስጠት ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ የአየር ሁኔታ ሳይንቲስቶች መደበኛ ስብሰባዎችን ያካሂዳሉ።

በርካታ ውድመትን ያስከተሉ የከባድ አውሎ ነፋሶች ስም ፈፅሞ በድጋሚ ለስያሜነት ጥቅም ላይ አይውሉም።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሕዝቡ አማራጭ ስሞችን እንዲጠቁም በሚትዮሮሎጂ መሥሪያ ቤት በኩል ጥያቄ ይቀርባል።

አውሎ ነፋሱ ስም እንዲያገኝ ምን ያህል ከባድ መሆን አለበት?

ሁሉም አውሎ ነፋሶች ስም ለማግኘት የሚያስችል ጉልበት የላቸውም፤ ከባድ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱት ብቻ ናቸው ስያሜን የሚያገኙት።

የትኛው የአውሎ ነፋስ ስያሜ በመጀመሪያ ይመረጣል?

የፎቶው ባለመብት, NASA

አውሎ ነፋሶች ስያሜን የሚያገኙት በእንግሊዝኛ ፊደላት ቅደም ተከተል ነው።

ስለዚህም የዓመቱ የመጀመሪያዎቹ አውሎ ነፋሶች በ'ኤ' የሚጀምር ስያሜ ሲሰጣቸው፤ ሃሪኬን አሊስ ወይም ታይፉን አንድሩ ይባላሉ። ቀጣዮቹ ደግሞ በ'ቢ' የሚጀምር ስም ሲያገኙ ሌሎቹ በዚሁ መሰረት ቀጣዮቹን ፊደላት እየተጋሩ ይሄዳሉ።

በእያንዳንዱ የእንግሊዝኛ ፊደላት የሚጀምሩ ስሞች ሲኖሩ 'ኪው'፣ ዩ፣ ኤክስ፣ ዋይ እና ዜድ ግን አልተካተቱም።

ስያሜው የሴት ወይም የወንድ ስም እንዲሆን ማነው የሚወስነው?

የፎቶው ባለመብት, PA

አውሎ ነፋሶች የሴት ወይም የወንድ ስም በየተራ እየተፈራረቀ ይሰጣቸዋል።

ለአውሎ ነፋሶች መጀመሪያ ላይ የሴት ስም ብቻ ነበር የሚሰጣቸው። የወንድ ስም መስጠት የተጀመረው ከ1979 (እአአ) ጀምሮ ነው።