ማሪያ አውሎ-ንፋስ ፖርቶ ሪኮና ቨርጅን ደሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

ፖርተ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በባህር ዳርቻ አካባቢ የሚገኙ ከተሞችን ሃይለኛ ንፋስ ዛፎችን ሲነቀንቅ ነበር

ማሪያ ተብሎ የተሰየመው አውሎ-ንፋስ ፖርታ ሪኮና ቨርጅን ደሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

መድብ አምስት የተባለው ከባድ አውሎ-ንፋስ በካረቢያን ዶሚኒካ ደሴት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ነው ወደ ፖርቶ ሪኮና ቨርጅን ደሴቶች የተሻገረው።

ከባድ አውሎ-ንፋሱ በሰዓት 280 ኪ.ሜ እየነፈሰ ይገኛል።

የማሪያ አቅጣጫ ኤርማ የተባለው አውሎ-ንፋስ የነፈሰበትን አቅጣጫ ይዞ እየተጓዘ ነው።

የአሜሪካ ግዛት የሆነችው የፖርታ ሪኮ አስተዳዳሪ 3.5 ሚሊዮን ለሚሆኑት የግዛቷ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የቀደመው ኤርማ አውሎ-ንፋስ ትቶት የሄደውን ስብርባሪ ማሪያ የተባለው ከባድ ነፋስ አንስቶት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት አለ።

ከዚህ በተጨማሪም እየጣለ ያለው ከፍተኛ ዘናብ የመሬት መንሸራተት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ።

Image copyright AFP

የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት በነበረችውና 72 ሺህ ህዝብ እንዳላት በሚነገርላት ዶሚኒካ በአውሎ-ንፋሱ ምክንያት ሰባት ሰዎች ሞተዋል፤ የመሬት ናዳም ተከስቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሩዝቨልት ስኬሪት ''እስካሁን ያናገርኳቸው ሰዎች በጠቅላላ የቤታቸው ጣሪያ በንፋስ እንደተወሰደ ነግረውኛል'' ብለዋል። የጠቅላይ ሚንስትሩም የቤት ጣሪያ በአውሎ-ንፋሱ መወሰዱ ይታወሳል።

በዶሚኒካ የመገናኛ ዘዴዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ