በሜክሲኮ የመሬት መንቀጥቀጥ ህንጻዎች ሲደረመሱ ከ220 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል

ሰዎች ከፍርስራሽ ስር ሰዎች ሲፈልጉ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በመሬት መንቀጥቀ የፈረሰ ህንጻ

ማዕከላዊ ሜክሲኮ በከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ መመታቷን ተከትሎ ከ250 በላይ ሰዎች የህይወት አልፏል።

በርዕደ መሬት መለኪያ 7.1 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ ህንጻዎችን ያፈራረሰ ሲሆን ትምህርት ቤቶች ፈርሰው የተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል።

ከሜክሲኮ ሲቲ ደቡባዊ አቅጣጫ በምትገኘው ሞሬሎስ ግዛት በትንሹ 55 ሰዎች ሞተዋል። ፑዬብላ በተሰኘችው ግዛት ደግሞ የሟቾች ቁጥር 32 ደርሷል። በዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ 49 ሰዎች ሲሞቱ፤ 10 ሰዎች በሜክሲኮ ግዛት እንዲሁም 3 ሰዎች በጉይሬሮ መሞታቸው ተዘግቧል።

ሜክሲኮ ለርዕደ መሬት የተጋለጠች ሲሆን ከወር በፊት በርዕደ መሬት መለኪያ 8.1 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 90 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

አደጋውን ተከትሎ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ የሜክሲኮ ሲቲ ነዋሪዎች የመብራትና የስልክ አገልግሎታቸው ተቋርጧል። የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ተሰብረው ሊሆን ስለሚችል ሰዎች በመንገዶች ላይ ሲጋራ እንዳያጨሱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው 44 ቦታዎች የአደጋ ሰራተኞች መሰማራታቸውን የከተማዋ ከንቲባ ሚጉዌል አንጄል ማንሴራ ገልጸዋል።

በደቡባዊ ሜክሲኮ ሲቲ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት በትንሹ ስምንት ተማሪዎችና አንድ መምህር ህይወታቸው አልፏል። በህንጻ ፍርስራሾች ስር የሚገኙ ተማሪዎችን ለማዳን የነፍስ አድን ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። በፍርስራሾች ስር ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ የድረሱልን ጥሪ የሚያስተላልፉ ተማሪዎች መኖራቸውም ተዘግቧል።

ከፈረሱት ህንጻዎች መካከል የገበያ ማዕከልና ፋብሪካ የሚገኝበት አንድ ባለስድስት ወለል ህንጻ ይገኝበታል።

የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኤንሪኬ ፔና ኒቶ እንዳሉት ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ የሃገሪቱ ጦር ወደ አካባቢው ተሰማርቷል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ከአደጋው በኋላ ሰዎች ወደ አደባባዮች ወጥተዋል

"ሰዎችን በፍርስራሾች ስር እናገኛለን። መረጃ ስለምናስተላልፍ ሁሉም እንዲከታተል እንፈልጋለን" ብለዋል።

በሜክሲኮ ሲቲ የነፍስ አድን ሠራተኞችና በጎ ፍቃደኖች በፍርስራሾች ስር የሚገኙ ሰዎችን ለመታደግ ስራ ጀምረዋል።

"ሚስቴ እዚህ ናት። መረጃ ለመቀባበል አልቻልንም" ሲል ሁዋን የሱስ ጋርሲያ የተባለ ግለሰብ ከፈረሰ ህንጻ አጠገብ ሆኖ ተናግሯል።

"ስልክ ብደውልም አታነሳም። አሁን ደግሞ የጋዝ ቱቦ መሰበር ሊኖር ስለሚችል ስልክ አትደውሉ ተብለናል" ሲል ገልጿል።

ሜክሲኮ ሲቲ ብዙ ነዋሪ ካላቸው የዓለማችን ከተሞች አንዷ ስትሆን የህዝብ ብዛቷ ከ20 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይገመታል። ል።