በሜክሲኮ የመሬት መንቀጥቀጥ በፈረሰው ትምህርት ቤት የነፍስ አድን ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል

የነፍስ አድን ሰራተኞች Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የነፍስ አድን ሰራተኞች ሰዎችን ከፍርስራሾች ስር ለማውጣት እየሰሩ ነው

በሜክሲኮ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በፈረሰው ትምህርት ቤት በፍርስራሽ ስር የሚገኙ ተማሪዎችን ለማዳን የነፍስ አድን ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አንዲት የ 13 ዓመት ተማሪ ህይወቷን ለማቆየት ጠረጴዛ ስር ተከልላ እንደምትገኝ ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል በትንሹ 21 የሚሆኑት ሲሞቱ ሌሎች ደግሞ እስካሁን አለመገኘታቸው ታውቋል።

እስካሁን ባለው መረጃ የመሬት መንቀጥቀጡ 230 ሰዎችን ነፍስ የነጠቀ ሲሆን ትምህርት ቤቱን ጨምሮ ከ10 በላይ ህንጻዎችንም አፈራርሷል።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ኤንሪኬ ፔና ኒቶ አደጋውን ተከትሎ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የብሔራዊ ሃዘን ቀን አውጀዋል።

የነፍስ አድን ስራው ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በደቡባዊ የሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት ተደርጓል።

የተማሪዎቹ ወላጆች በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ሆነው ልጆቻቸውን ዕጣ ፈንታ ለማወቅ እየጠበቁ ሲሆን የበጎ ፈቃድ ሠራተኛው ኤንሪኬ ጋርዲያ መፈተሽያ መሳሪያው ተጠቅሞ ተማሪዎቹ በህንጻዎቹ ፍርስራሾች ውስጥ መሆናቸውን ጠቁሟል።

"በህይወት አሉ" ሲልም ውጤቱን ለወላጆቹ አስታውቋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች በከተማዋ ተሰማርተዋል

የሰባት ዓመት ልጇን ዜና ለመከታተል በትምህርት ቤቱ የተገነች አንዲት እናት "ያለሁበትን ህመም ማንም የሚያውቀው አይመስለኝም" ብላለች።

ትላንት አንዲት ልጅ በፍርስራሹ ውስጥ ሆና እጇን ስታንቀሳቅስ በመመርመሪያ መሳሪያ በመታየቷ ምግብና ውሃ ተላከላት ሲሆን ያለችብት ሁኔታ ግን አልታወቀም።

እንደሜክሲኮ ሲቲ ባለስልጣናት ከሆነ ከመሬት መንቀጥቀቱ በኋላ 52 ሰዎችን በህይወት ከፍርስራሾች ስር ማውታታቸውን አስታውቀዋል።

ሜክሲኮ በተደጋጋሚ በመሬት መንቀጠቀት ተመታች ሲሆን በዚህ ወር ብቻ በደቡባዊ ሃገሪቱ ክፍል 8.1 ተመዘገበው መሬት መንቀጥቀጥ 90 ሰዎችን ህይወት ነጥቋል። ል።