የኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሞት የድጋፍ ጥሪዎችን አስከትሏል

Eyob

በስዋንዚ ሞቶ የተገኘው ኢትዯጵያዊ ኢዮብ በዌልስ ለመቆየት ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ለከፋ ችግር ተጋልጦ እንደነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ።

እናም አሁን በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያሉ ስደተኞች የተሻለ እርዳታ እንዲደረግላቸው እየወተወቱ ነው።

የኢዮብ አስክሬን ባለፈው ሃሙስ ከቀትር በኋላ ነበር በስዋንዚ ማሪና ውሃ ውስጥ የተገኘው።

ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ ባለፈው ሰኞ የመታሰቢያ ዝግጅት ተካሂዷል።

አሟሟቱ እስካሁን እየተጣራ ሲሆን የደቡብ ዌልስ ፖሊስ ግን ግድያ ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ነገሮች እንደሌሉ ገልጿል።

የኢዮብ ህይወት የተመሰቃቀለው የጓደኛውን መሞት ተከትሎ እንደሆነ ስደተኞችን የሚረዳ የእርዳታ ድርጅትን የምታስተዳድረው ሬቸል ማቲው ትናገራለች።

"የማደሪያ ቦታም ሆነ ምንም አይነት ጥቅማ ጥቅም አልነበረውም፤ በጣም ተቸግሮ ነበር"

ራቼል ለቢቢሲ እንደተናገረችው ራሱን የማጥፋት ሙከራ ካደረገ በኋላ እንኳን ተገቢውን የአዕምሮ ጤና ድጋፍ አላገኘም።

"ከቀዶ ጥገና በኋላ ከሃኪም ቤት ወጥተን መንገድ ላይ ቆመን ' እና ማንም አይረዳኝም? ' ብሎ ጠየቀኝ፤ ግን ምንም መልስ አልነበረኝም፤ በእውነት ይረዱታል ብዬ ነበር ያሰብኩት'' ትላለች ሬቸል።

እሷ እንደምትለው የጤናና የማህበራዊ ድጋፍ ሰጪዎችን ብታማክርም ማድረግ የምትችለውን ሁሉ እንዳደረገች ከመቀበል ውጪ አማራጭ እንደሌሏት ነበር የነገሯት።

አጭር የምስል መግለጫ ኢዮብን ለማሰብ በስዋንሲ የህሊና ጸሎት ተካሂዷል

የአበርታው ብሮ ሞርጋንዊግ ዩኒቨርሲቲ የጤና ቦርድ በግለሰባዊ ጉዳዮች ላይ ኃሳብ እንደማይሰጥ ገልጾ ነገር ግን ለጥገኝነት ጠያቂዎችና ተቀባይነት ላላገኙ ስደተኞች የተሟላ የጤና ክብካቤ አቅርቤያለሁ ባይ ነው

"ማንኛውም ጥገኝነት ጠያቂም ሆነ ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኛ ከቀዶ ጥገና በኋላ በሚመለከተው ባለሙያ ክትትል ይደረግለታል ፤ ይህንን አሳዛኝ ሞት ስንሰማም በጣም አዝነናል'' ብለዋል የቦርዱ ኃላፊ።

በዩናይትድ ኪንግደም ህግ መሰረት የጥገኝነት ጥያቅ ውድቅ የተደረገበት ግለሰብ በ 21 ቀናት ውስጥ ሃገሪቱን ለቆ መውጣት አለበት።

ይሁንና ሂደቱ ከዚህ በላይ ጊዜ ይፈጃል ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ በሳምንት የ35 ዩሮ (986 ብር) የምግብና የልብስ ክፍያ እንዲሁም የማደሪያ ቦታ ይቀርብላቸዋል።

የመኖሪያ ቦታ ያልነበረው ኢዮብ ግን ለዚህ ክፍያም ብቁ አልነበረም።

የዌልስ የስደተኞች ምክርቤት በስኮትላንድና በሰሜን አየርላንድ ተቀባይነት ላላገኙ ስደተኞች የተሻለ ድጎማ ለማድረግ የተሻለ ጥረት እንደሚያደርግ ግልጿል።