ሟቹ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ጠይቆ ተከልክሎ ነበር

Eyob

በስዋንዚ ሞቶ የተገኘው ኢትዮጵያዊ ለገጠመው ችግር ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘቱና ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ለከፋ ችግር እንዳረገው ጓደኞቹ ይናገራሉ።

የኢዮብ አስስሬን ባለፈው ሃሙስ ከቀትር በኋላ ነበር በስዋንዚ ማሪና ውሃ ውስጥ የተገኘው። የአሟሟቱ ምክንያት እየተጣራ ሲሆን የደቡብ ዌልስ ፖሊስ ግን ግድያ ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ነገሮች እንደሌሉ ገልጿል።

እዮብ ተፈራ በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ የነበረ ሲሆን፤ የዛሬ 2 ዓመታት ገደማ ዌልስ ውስጥ በምትገኝ ስዋንዚ በምትባል ከተማ ጥገኝነት ጠይቆ ነበር። ጓደኞቹ የአዲሱን ዓመት ዋዜማ ለማክበር በተሰባሰቡ ወቅት ነበር ለመጨረሻ ጊዜ ድምጹን የሰሙት።

ሬቸል ማትዩዝ በስዋንዚ ከተማ ለስደተኞች የእርዳታ ቡድን አቋቁማ የምትሠራ ግለሰብ ስትሆን እሷም እዮብን ከመሞቱ በፊት በወላጆቿ ቤት አስጠግታ ታኖረው እንደነበር ለቢቢሲ አማርኛ ተናግራለች።

እዮብ ኢትዮጵያዊ ጓደኛው ሙሐመድ በሰው እጅ ከተገደለ በኋላ አዕምሮው የተረጋጋ እንዳልነበር ሬቸል ተናግራለች። እዮብን ያጋጠመው ችግር በቀላሉ መከላከል ይቻል እነደነበረም ገልጻ፤ ላጋጠመው የአዕምሮ መረበሽ ወደ ጤና ማዕከል አብረው ሄደው የህክምና ድጋፍ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቡን፤ ነገር ግን ለመከልከሉ አጥጋቢ ምክንያት ስላልተሰጠው ማዘኗን ነግራናለች።

''እዮብ ቀናና ጎበዝ የነበረ፤ ጊዜውን ሌሎችን ለመርዳት የበጎፈቃድ ሥራዎችንም ያከናውን ነበር።" በማለት ጨምራ ተናግራለች

ከዚያም አልፎ በስዋንዚ ከተማ የስደተኞች የእግር ኳስ ቡድን አምበል እንደ ነበረና ከ17 እስከ 35 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን የቡድኑን አባላት ያሰለጥን እንደነበርም ሬቸል አጫውታናለች።

በአሁኑ ሰዓት መስፍን* የተሰኘው የእዮብ ኤርትራዊ ጓደኛ አስከሬኑን ወደ ቤተሰቦቹ ለመላክ በስዋንዚ ከተማ ውስጥ ገንዘብ እያሰባሰበ ይገኛል። መስፍን እንደሚለው ሬሳው ከመገኘቱ በፊት በዋለው በዕለተ ቅዳሜ የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ተገናኝተው በነበሩበት ጊዜ፤ ስለወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው መማከራቸውን ለቢቢሲ አማርኛ ተናግሯል።

መስፍን እዮብን ቀልጣፋ፣ ጎበዝና ብልህ ወጣት በማለት ነበር የገለጸው። በመቀጠልም እራሱን ይገድላል ብሎ ለማሰብ እንደሚከብደውም ተናግሯል። እዮብ የመማር እቅድ እንደነበረው ጓደኞቹ ጨምረው አጫውተውናል።

በስም መጠቀስ ያልፈለገው ሌላኛው የእዮብ ጓደኛ ደግሞ "አንዴ ሕይወቱ አለፈ?'' ሲል ይጠይቅና ''እንደ እዮብ የጥገኝነት ፈቃድ ሳያገኙ በመንገድ ላይ የሚወድቁ ብዙ ግለሰቦች አሉ። እዚህ እንደ ሃገር ቤት አይደለም፤ እንኳን አንድ ሌሊት አንድ ደቂቃ እንኳን ውጪ የማያስቀምጥ ብርድ ነው ያለው" በማለት ሐዘኔታውን ገልጿል።