ማሪያ የተባለው አውሎ-ንፋስ ''በዶሚኒካ 15 ሰዎችን ገደለ''

ማሪያ አውሎ-ንፋስ በዶሚኒካ ያደረሰው ጉዳት Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ማሪያ አውሎ-ንፋስ በዶሚኒካ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው ተብሏል

የዶሚኒካ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ማሪያ የተባለው አውሎ-ንፋስ ዶሚኒካን ከመታት በኋላ ቢያንስ 15 ሰዎችን ሲገድል 20 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሮስቬልት ስኬሪት ለሃገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ የሟቾች ቁጥር በመቶዎች አለመሆኑ ''ተአምር'' ሲሉ ገልጸዋል።

በፖርቶ ሪኮ ሙሉ በሙሉ የኤሌትሪክ ሃይል ተቋርጧል

ማሪያ አውሎ-ንፋስ ፖርቶ ሪኮን ከመታ በኋላ ነበር ሃይሉን በማጠናከር ሰኞ አመሻሽ ዶሚኒካን ላይ ጉዳት ያደረሰው።

ይህ ምድብ አራት የተባለው ማሪያ አውሎ-ንፋስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉትን በርካታ ሰዓታት በአየር ሆነው አውሎ-ንፍሱ ያደረሰውን ጉዳት ከቃኙ በኋላ ''እንዲህ አይነት ጥፍት አይተን አናውቅም'' ሲሉ ተናግረዋል።

ቤቶች በንፋስ ተወስደዋል፣ ትምህርት ቤቶች ፈራርሰዋል፣ የመገናኛ ዘዴዎች ተበጣጥሰዋል እንዲሁም በደሴቷ ላይ የሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል የኤሌትሪክ አገልግሎት ተቋርጦበታል።

ከዚህ በፊት ማሪያ የተባለው አውሎ-ንፋስ የ3.5 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነችውን የፖርቶ ሪኮን ደሴት የኤሌትሪክ ሃይል ሙሉ በሙሉ እቋርጦ ነበር።

ማሪያ አውሎ-ንፋስ አሁን ደግሞ አቅጣጫውን ወደ ቱርከስ እና ኪኮስ ደሴቶች አድርጓል።

ማሪያ እስካሁን በካረቢያን አካባቢ ቢያንስ 17 ሰዎችን ሲገድል በርካቶች የደረሱበት አልታወቀም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ