ከአየር ላይ የወደቀ የአውሮፕላን ክንፍ ጉዳት አደረሰ

ኬኤልኤም

ጃፓን ኦሳካ ውስጥ አየር ላይ የነበረ አውሮፕላን የክንፉ ከፊል አካል ተቆርጦ በመውደቁ መንገድ ላይ በነበረ መኪና ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰ።

አራት ኪሎ ግራም የሚመዝነው የአውሮፕላኑ ክንፍ አካል የወደቀው፤ ቅዳሜ ዕለት ከካነሳይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ መብረር ከጀመረው ኬልኤም ከተባለው የሮያል ደች አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ነው።

የክንፉ አካል ከ2ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ ተምዘግዝጎ ሲወድቅ የአንዲት መኪናን ጣሪያ ሲጠረምስ የኋላ መስታወቷን ደግሞ አድቅቆታል።

በክስተቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም፤ አየር መንገዱ አደጋው እንዴት እንደደረሰ ለማወቅ ምርመራ ጀምሯል።

የክንፉ አካል ተሰብሮ የወደቀበት ቦይንግ 777 አውሮፕላን ከ300 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ነበር ከማኮብኮቢያው የተነሳው። አውሮፕላኑ ግን ምንም ችግር ሳይገጥመው በሰላም አምስተርዳም ስኪፖል አየር ማረፊያ በዚያው ዕለት ደርሷል።

የደች አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ኬኤልኤም በክስተቱ ማዘኑንና የደረሰውን አደጋ መንስኤ ለመለየት ምርመራ መጀመሩን አሳውቋል።

መግለጫው ጨምሮም ''ለምርመራው ከጃፓን ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው።'' ብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች