አደገኛ ነው የተባለለት የወባ በሽታ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ተስፋፍቷል

የወባ ትንኝ Image copyright Science Photo Library
አጭር የምስል መግለጫ የወባ በሽታን የምታስተላልፈው ትንኝ

አደገኛ እንደሆነ የተነገረለት የወባ ዓይነት በደቡብ ምሥራቅ እስያ በፍጥነት መዛመቱ ለአፍሪካ አስጊ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ።

ይህን መሰሉ የወባ ዓይነት በመደበኛው የወባ መከላከያ መድኃኒት በቁጥጠር ሥር አይውልም ተብሏል።

ይህ የወባ ዓይነት መጀመሪያ በካምቦዲያ የታየ ቢሆንም ወደ ደቡብ እስያ ሃገራት ተስፋፍቷል።

በባንኮክ የሚገኘው ኦክስፎርድ ትሮፒካል ሜድሲን የምርምር ተቋም ባልደረቦች እንደሚሉት ይህን የወባ ዓይነት ለመዳን አስቸጋሪ ይሆናል።

የምርምር ቡድኑ የበላይ የሆኑት ፕሮፌሰር አሪየን ዶንድሮፕ በሽታው በፍጥነት ከመዛመቱም በላይ አፍሪካ ሊደረስ ይችላል የሚል ስጋት አለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ተሞክሮ

በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የወባ ፕሮግራም ባለሙያ ሆኑት አቶ ደረጀ ድሉ እንደሚሉት መስሪያ ቤቱ ስለስጋቱ መረጃው አለው።

ወባ በሽታን በመከላከል አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው እ.አ.አ በ2013 ላይ 3.31 ሚልዮን የነበረው የህሙማን ቁጥር በ2016 ወደ 1.8 ሚሊዮን መቀነሱን ጠቁመዋል።

እስካሁን ባለው አሰራር ፕላስሞዲየም ፋልሲፓረም እና ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ ለተየባሉት የወባ ዓይነቶች መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ብለዋል።

እንደባለሙያው ከሆነ የመድኃኒቶቹን ውጤታማነት ለመከታተልም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት በየሁለት ዓመቱ ጥናት ያካሂዳል።

የጨነገፉ መድኃኒቶች

በወባ ትንኝ በሚዛመተው በዚህ በሽታ 212 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በየዓመቱ የሚያዙ ሲሆን ህጻናትን በመግደል ቀዳሚ ከሆኑት መካከልም ተጠቃሽ ነው።

በሽታውን ለመቆጣጠር አርትሚሲኒንን ከፒፐራኩይን ጋር በማሃዋድ መጠቀም ተቀዳሚ ምርጫ ነው።

አርትሚሲኒን ያለው ውጤታማነት እየቀነሰ ሲሆን በሽታው ደግሞ ፒፐራኩይንን እየተላመደ ይገኛል።

በውህድ መድሃኒቶቹ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በአንዳንድ ቦታዎች እስከ 60 በመቶ ድረስ መቀነሱን ፕሮፌሰር ዶንድሮፕ አስታውቀዋል።

መድኃኒቱን የተላመደ ወባ መስፋፋቱ እስከ 92 በመቶ የሚሆነው የወባ በሽታ በሚከሰትበት የአፍሪካ አህጉር የከፋ ችግር ሊያስከትል ይችላል።

በአፋጣኝ የሚቀርብ መፍትሔ

"በሽታው መዳን ከማይቻልበት ደረጃ ደርሶ የሰዎችን ህይወት ከመቅጠፉ በፊት በፍጥነት መስራት ይኖርብናል" ብለዋል።

"እውነቱን ለመናገር በጣም ሰግቻለሁ" ሲሉ ፕሮፌሰሩ የክስተቱን አሳሳቢነት ይናገራሉ።

የዌልካም ትረስት ሜዲካል ሪሰርች ባልደረባ ሆኑት ማይክል ቼው እንደሚሉት፤ መድኃኒት የተላመደ የወባ በሽታ መስፋፋቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማህበረሰብ ጤና አስጊ ነው ብለዋል።

እስካሁን በዓመት የ700 ሺህ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ የነበረው መድኃኒት የተላመደ የወባ በሽታ፤ ምንም ካልተሰራበት የሟቾች ቁጥር እ.አ.አ በ2050 በሚሊዮኖች ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአዲሱ የወባ በሽታ ዓይነት አለመከሰቱን አቶ ደረጀ ጠቅሰው፤ መድኃኒት የተላመደ ወባን ለመከላከል እና የመድኃኒቶችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት ጋር የሚደረገው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች