የተማሪዎች ቅሬታና ትምህርት ሚኒስቴር ''ጥያቄ ተነሳ ብለን የሚቀየር ነገር የለም'' ሲል የሰጠው ምላሽ

ተመራቂ ተማሪ ጋዋን ለብሶ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች ተምረው የተመረቁ ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዳይቀጠሩ ተከለከሉ።

ትምሀርት ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ ምክንያት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቀጥረን እንዳንሰራ ተከለከልን ይላሉ መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች ተምረው የተመረቁ ተማሪዎች።

ትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ዲግሪ በማታ፣ ቅዳሜና እሁድ፣ በክረምት እና በርቀት ተምረው የተመረቁ ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ተቀጥረው እንዳይሰሩ ከከለከለ ሰንበትበት ብሏል።

አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች መመሪያውን ወደ ጎን በመተው መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች የተማሩ ተማሪዎችን በመምህርነት ለመቅጠር ምዝገባ ቢጀምሩም፤ ትምህርት ሚኒስቴር የዕግድ ደብዳቤ ለዩኒቨርሲቲዎቹ ልኳል።

ዮሴፍ ተስፋዬ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም መደበኛ ባልሆነ ፕሮግራም በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቋል። ዮሴፍ እንደሚለው ''ይህ መመሪያ እኛን ላለመቅጥር በቂ ምክንያት አይሆንም፤ መስፈርት መሆን ያለበት ችሎታ እንጂ የትምህርት ፕሮግራም አልነበረም።''

መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች ተምረው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቁ ተማሪዎች እያሉ በመደበኛ ፕሮግራም ስለተማሩ ብቻ አነ

ስተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ይላል ዮሴፍ።

በተመሳሳይ አብረሃም ጌታቸው መደበኛ ባልሆነ ፕሮግራም የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ ነው። አብረሃም እንደሚለው ''የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ መደበኛ ያልሆነ የትምህርት ፕሮግራምን ዋጋ የሚያሳጣ ነው'' ሲል ይተቻል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታ የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ይህ ውሳኔ በጥናት የተደገፈና በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሚንስትር ድኤታው እንደ ምክንያት የሚያነሱት፤ መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች ለመማር የሚያስፈልገው የመግቢያ ነጥብ ከመደበኛው ጋር ሲነጻጸር አናሳ መሆኑ እና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች አነስተኛ የትምህርት ሰዓት መኖሩን ነው።

ዶ/ር ሳሙኤል ተመራቂዎቹ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ ''ጥያቄ ተነሳ ብለን የሚቀየር ነገር የለም'' ብለዋል።

አጭር የምስል መግለጫ ዶ/ር ሳሙኤል ተመራቂዎቹ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ ''ጥያቄ ተነሳ ብለን የሚቀየር ነገር የለም'' ብለዋል።

ጥራት ወይስ ብዛት?

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ በተጨማሪ ከሌሎች ሃገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የትምህርት መስኩን ለመደገፍ በርካታ ድጋፍ የምታገኝ ሃገር ናት።

ይሁን እንጂ በሃገሪቷ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ቢጨምርም የትምሀርት ጥራቱ ግን እጅግ አናሳ ስለመሆኑ ከድጋፍ ሰጪዎቹ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ሰማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምሀር ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ሚኒስቴር መደበኛ ባልሆነው የትምህርት ፕሮግራሞች የተመረቁ ተማሪዎችን ላለመቅጠር የወሰነው ፕሮግራሙ ካለበት የጥራት ችግር ጋር ተያይዞ እንደሆነ አስረድተዋል።

''መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ውስጥ የሚሰሩት መምህራን በትርፍ ጊዜያቸው የሚያስተምሩ ሲሆን፤ ይህም በቂ ትኩረት እንዳያገኝ ያደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎቹ ቀን በሥራ ደክመው ማታ በድካም ስሜት ውስጥ ሆነው ነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉት'' ሲሉ አብራርተዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል 43 በመቶ የሚሆኑት መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ውስጥ የሚማሩ ነበሩ።

ትምህርት ሚኒስቴር ራሱ በቀረጸው ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ያለፉትን መቅጠር ካልፈለገ የትኛው ተቋም ሊቀጥራቸው ይችላል?

ተያያዥ ርዕሶች