ቻይና በኮሚኒስት ፓርቲው ስብስባ መባቻ ላይ 'ዋትስአፕን' ዘጋች

ዋትስአፕ በፌስቡክ የሚተዳደር መተግበሪያ ነው Image copyright Getty Images

የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው 'ዋትስአፕ' በቀጣይ ወር ከሚካሄደው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ስብሰባ በፊት ሀገሪቱ ላይ እንዳይሰራ ተደረገ።

ቻይናያውያን ተጠቃሚዎች ላለፉት ጥቂት ሳምንታት መተገብረያውን ለመጠቀም እጅጉን መቸገራቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል።

መተግበሪያው ከዚህ በፊት በቻይና ተመሳሳይ እክል ሲያጋጥመው 'ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ' (ቪፒኤን) የተሰኘን ስውር ማቋረጫ በመጠቀም ቻይናውያን ሲገለገሉ እንደነበረ ይታዋሳል።

'ዋትስአፕ' ከፌስቡክ ምርቶች ውስጥ ቻይና ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ የተፈቀደለት ብቸኛው መተግበሪያ ነው።

የቢቢሲ የቻይና ዘጋቢ እንደገለፀው ችግሩ መከሰት ከጀመረ ሳምንት ሆኖታል። ተጠቃሚዎች ተንቀሳቃሽ ምስልም ሆነ ፎቶግራፍ ወደሌላ ሀገር መላክ ተስኗቸው ቆይቷል።

ቻይና በቀጣይ ወር ከሚካሄደው የኮሚኒስት ፓርቲው ስበሰባ በፊት የፀጥታ ኃይሏን በተለያየ መልኩ እያጠናከረች ትገኛለች። 'ዋትስአፕ' የተሰኘውን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያን መዝጋትም የዚህ ሂደት አንድ አካል እንደሆነ እየተዘገበ ነው።

የቻይና መንግስት አንድ አማካሪ እንደገለፁት "ስብሰባው ፀጥታ በሰፈነበት መልኩ እንዲከናወንና ሕብረተሰባዊ ሰላም እንዲፈጠር መሰል ሂደቶች የግድ ናቸው" ብለዋል። ነገር ግን ሁኔታው እስከመቼ ሊዘልቅ እንደሚችል ግልፅ እንዳልሆነ ታውቋል።

የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የቻይና መንግስት በ'ዋትስአፕ በኩል ሀሳብ የገባው፤ መተግበሪያው ከላኪው እና ከተቀባዩ ውጭ ሌሎች መልዕክቱን እንዳያዩት ስለሚያደርግ ነው።

በቻይና መሰል ድርጊቶች የተለመዱ ናቸው። የቻይና መንግስት በይነ-መረብ እና የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችን በየጊዜው እንዳይሰሩ በማድረግ ይታወቃል።

ሰኞ ዕለት የቻይና መንግስት የሳይበር ደህንነት መስሪያ ቤት በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ቴንሴንት፣ ባይዱ እና ዌይቦ የመሳሰሉ የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች በሕጉ መሰረት የማይንቀሳቀሱ ከሆነ ከፍተኛ ቅጣት ሊተላልፋባቸው እንደሚችል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

መተግበሪያዎቹ የሀሰት ዜናና ወሲብ ቀስቃሽ እንዲሁም የጎሳ እና የድንበር ግጭት የሚያስነሱ ይዘቶች ላይ ጥንቃቄ የማያደርጉ ከሆነ ዕገዳው ሊጣልባቸው እንደሚችል ተዘግቧል።

ተያያዥ ርዕሶች