የነዳጅ ዘይት ዋጋ በዓለም አቀፍ በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ

የነዳጅ ዘይት ማምረቻ Image copyright Reuters

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከታየው ሁሉ በተለየ ሁኔታ ከፍተኛውን ጭማሪ በዚህ ሳምንት አሳይቷል።

የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ዋጋው እንዲያንሰራራ የምርት መጠን ለመቀነስ የወሰዱት እርምጃ የሚያስከትለው ተፅዕኖ መታየት መጀመሩ እንዲሁም የነዳጅ ዘይት ፍላጎት እየጨመረ መምጣትና አሳሳቢ የፖለቲካ ሁኔታዎች ለዋጋው መጨመር ምክንያት ሆነዋል።

በዓለም ገበያ በዚህ ሳምንት የታየው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ 3.8 በመቶ ሲሆን ዋጋው ከ59 ዶላር በላይ ከፍ ብሏል። ይህም ከ2015 (እአአ) ወዲህ ከፍተኛው ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የነዳጅ ዘይት ገበያው የዋጋ በከፍትኛ ደረጃ ማሽቆልቆል አሳይቶ ነበረ።

በተለይ ከቻይና በኩል የታየው የፍላጎት ከፍ ማለትና ቱርክ ከኢራቅ የኩርዲስታን ክልል የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት እንዲቋረጥ አደርጋለሁ ብላ መዛቷ፤ ሰኞ ዕለት ለተመዘገበው የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር ምክንያት ሆኗል።

በኩርድ ራስ-ገዝ አስተዳደር ውስጥ በሚደረገው ሕዝበ-ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፤ ቱርክ ከሰሜናዊ ኢራቅ ተመርቶ ወደ ዓለም ገበያ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት ማስተላለፊያ የቧንቧ መስመርን ልታቋርጠው እንደምትችል አስጠንቅቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአውሮፓውያኑ 2017 መጀመሪያ አንስቶ የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር፣ ሩሲያና ሌሎች በርካታ ነዳጅ አምራቾች የነዳጅ ምርታቸውን በቀን በ1.8 ሚሊዮን በርሜል ቀንሰዋል።

ይህም ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የነዳጅ ዋጋን በ15 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ባለፈው አርብ በተደረገው የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር (ኦፔክ) ስብሰባ ላይ በርካታ ሃገራት እንዳሉት የምርት መቀነስ በነዳጅ ገበያና በዋጋ ላይ የሚፈለገውን ውጤት እያሳየ ነው ብለዋል።